2010-12-01 17:21:36

የቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ ክብረ በዓል በቝስጥንጥንያ


ትናንትና በኢስጣንቡል የቅዱስ እንድርያስ ክብረ በዓል በታልቅ ድምቀት እንደተከበረ ከቦታው የደረሰ ዜና አመልክተዋል።

በካቶሊካዊት ሮማዊት ቤተ ክርስትያንና በቝስጥንጥንያ የውኅደት ኦርቶክሳዊት ቤተ ክርስትያን ባለው የመተባበር መንፈስ በበዓሉ እንዲካፈሉ የክርስትያን ኣንድነት ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ኩርት ኮች የመሩት የቅድስት መንበር ተወካዮች በበዓሉ ተሳትፈዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ኩርት ኮች ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ለቝስጥንጥንያ የውኅደት ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ በርጠለሜዎስ 1ኛ የፃፉት መልእክትም ኣድርሰዋል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው የቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሓዋርያት ትምህርት ያለንን ታማኝነት እንድናሳድስና በክርስቶስ ያለንን እምነት ሳንታክት በቃልና በተግባር በሕይወታችን መመስከርና መስበክ እንዳለብን ኃይለኛ ጥሪ የሚያቀርብልን አጋጣሚ ነው። ዓለማችን ባለነው ግዜ በበለጠ እንድንደጋገፍና እንድንተባበር ስለሚጠይቅ ይህ ጥሪ ኣንገብጋቢ ነው፣ ከሌሎች ግዝያት በበለጠ መንገድ ሁላችን ክርስትያኖች በዚህ መስክ በብርታት እንድንሠራና በታደሰ መንፈስ የወንጌል እውነትን መስበክ እንዳለብን ኃላፊነት ያሸክመናል። በግዝያችን ለሚታዩ የሰው ልጆች ትላልቅና ጥልቅ መንፈሳውያን ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ክርስቶስ መልስ መሆኑን መስበክ ኣለብን። ይህንን በተገባ ለመወጣት በምናደርገው የመወኃኃድ ጉዞ ለሙሉ ኣንድነት ታጥቀን በመነሣት ለዘመናችን ሰዎች የክርስቶስ ወንጌል የተወኃኃደ ምስክርነት መስጠት ኣለብን።’ ሲሉ የክብረ በዓሉ ትርጉም በማስታወስ ለኣንድነትና ውኅደት በብርታት እንዲሰሩና ኣብያተ ክርስትያናቱ ወደ ሙሉ መዋሃሃድ እንዲደርሱ የሚያደርጉትን ጉዞ ኣመጕሰዋል። በተለይ ደግሞ የቝስጥንጥንያ የውኅደት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በርጠለሜዎስ 1ኛ ባለፈው ጥቅምት ወር፣ የኤውሮጳ ካቶሊካውን ጉባኤ ጳጳሳት ተወካዮች እና የኤውሮጳ ኦርቶዶክስ ኣብያተ ክርስትያናት ተወካዮች በሁለተኛው የካቶሊክና ኦርቶዶክስ ፎርም ጉባኤ ስላደረጉት ማስተናገድና ስላበረከቱት ኣመስግነዋል። ጉባኤው ‘በቤተ ክርስትያንና በመንግሥታት ስላለ ግኑኝነት ትምህርተ ንባበ መለኮትና ታሪክ ምን እንደሚል’ የሚያጠና እንደነበር የሚታወስ ነው።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው መዝጊዝያ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ የቝስጥንጥንያ ውኅደታዊ ፓትርያርክ በርጠለሜዎስ 1ኛ ለውኅደትና ለክርስትያን ዕሴቶች የሚያደርጉትን በጎ ነገር በጥንቃቄ እየተከታልውቸው መሆናቸውን በማመልከት መልካም ምኞታቸውን ገልጠዋል።

ይህ መልካም የአንድነት ልማድ በትላልቅ ክብረ በዓሎች ተወካዮች በመላክ የሚደረገው ኣመርቂ ውጤት እያስገኘ መሆኑ ከቅድስት መንበር በየጊዜው የወጡ መግለጫዎች ያመለክታሉ።

በዚህ ልማድ መሠረት በላቲኑ ሥርዓተ ኣምልኮ ግፅው በየዓመቱ ሰኔ 29 ቀን ለሚከበረው የቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ ክብረ በዓል የቝስጥንጥንያ የውኅደት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ተወክዮች እንደምትልክ ሁሉ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያንም በዚሁ ትናንትና በተከበረው የቅዱስ እንድርያስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ተወካዮችዋ እንደምትልክ የሚታወስ ነው።








All the contents on this site are copyrighted ©.