2010-12-01 17:25:58

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምህሮ (01.12.2010):


የያዕቆብ ሐዋርያዊ መልእክት ምዕ.4:7-10 ‘ስለዚህ ለእግዚአብሔር ተገዙ ዲያቢሎስን ግን ተቃወሙት፡ ከእናንተም ይሸሻልና። ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ እርሱ ወደ እናንተ ይቀርባል፡ እናንተ ኃጢኣተኞች እጆቻችሁን አጽዱ፡ እናንተ ወላዋዮች ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁ፡ እዘኑ፡ አልቅሱ፡ ሳቃችሁ ወደ ልቅሶ ደስታችሁ ወደ ሐዘን ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ እርሱም ከፍ ያደርጋችኋል።’

‘ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ባለፈው መስከረም ወር በታላቅዋ ብሪጣንያ ያደረግሁትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አሁንም በታላቅ ደስታ አስታውሰዋለው። ታላቅዋ ብሪጣንያ በምስክርነታቸውና በትምህርታቸው የቤተክርስቲያን ታሪክን የሚያሸበርቁ ብዙ ታላላቅ ሰዎችን ያበረከተች አገር ናት።

ከእነዚህም ታላላቅ ሰዎች በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና በአንግሊካዊት ቤተክርስቲያን እጅግ ከተከበሩት ውስጥ አንዷ ባህታዊ ጁልያና ዘኖሪች ናቸው። በዛሬው እለት ስለሷ መናገርን እወዳለሁኝ።

የእኚህ ታላቅ ሴት ታሪክ የምናገኘው ብዙም ባይሆን ከአምላክ የተሰጣቸው ራእይ በጽሑፍ ለማስፈር በደረሱት መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ አርእስት “የመለኮታዊ ፍቅር ራእዮች” ይባላል።

ከ1342 እስከ 1430 አካባቢ በሕይወት እንደኖሩ ሲታወቅ በእነኚህ ዓመታት ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለእግሊዝ አገር ነዋሪዎች በሙሉ የብርቱ ሥቃይ ዓመታት ግዜ ነበር። በዚያን ግዜ የቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከአቪኞን ወደ ሮም በተመለሱበት ግዜ በአቪኞን ሌላ ርእስ ሊቃነ ጳጳሳት በመሰየሙ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፋፍላ ትሰቃይ ነበር። የእንግሊዝ አገር ሕዝብም ለብዙ ዓመታት በእንግሊዝና በፈረንሳይ ኣገሮች መካከል በተካሄደው ረጅም ጦርነት በሥቃይ ዓዘቅት ተውጣ ነበር። ሆኖም ግን እግዚአብሔር በከባድ ግዜም ይሁን የሰው ልጆችን ለሰላም ለፍቅርና ለደስታ ለመጥራት እንደ ጁልያና ዘኖሪች የመሰሉ ታላላቅ ቅዱሳን ሰዎችን አነሳስቷል።

ጁልያና ዘኖሪች በትረካቸው፣ ግንቦት 13 ቀን 1373 ዓ.ም. በብርቱ ሕመም ለ 3 ቀናት ያህል መሰቃየቻቸውና፡ ሁሉም አትድንም ትሞታለች ብለው እንደነበር ይተረካል። ይሁን እንጂ ሊጸልዩላቸው የመጡት ካህን የኢየሱስን መስቀል ባሳይዋቸው ግዜ ከሕመማቸው ወዲያውኑ እንደተፈወሱ ነው።

ይህ ብቻ ሳይሆን 16 ሰማያዊ ራእዮችን እንዳየችና፡ በቶሎ እንደፃፈቻቸው ይነገራል።

የተሰጣትዋትን ራእዮች “የመለኮታዊ ፍቅር ራእዮች” በሚል ርእስ መጽሐፍ በሰፊው ገልጠው አቅርበዋል።

ይህ ክስተት ከተፈጸመ ከ 15 ዓመታት በኋላ ጌታ ራሱ የእነዚህን 16 ሰማያዊ ራእዮች ትርጉም ሲገልፅላት፡ “ጌታ በዚህ ራዕይ ግልፀት ምን እንደፈለገና የዚህ ግልፀት ትርጉም ማወቅ ትፈልጊያለሽን” ብሎ ጠየቃት። በመቀጠልም ጠንቀቅ አድርገሽ እወቂው ጌታ በዚህ ግልፀት ለማለት የፈለገው ፍቅር ነው። ፍቅርን ማንን ይገልጥልሻል? ፍቅር ለምንስ ይገልጥልሻል? በማለት ጠይቆ፡ መልሱ ስለፍቅር ነው ሲል ኣስረዳት፡ ኣያይዞም “በዚህ ፍቅር፡ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን ትማሪያለሽ” አላት።

በዚሁ መለኮታዊ ፍቅር ተነሳስተው ጁልያና ዘኖሪች ሥር ነቀል ውሳኔ ወሰኑ። እንደጥንታውያን ባህታውያን ልማድ በአንድ ትንሽ ክፍል ብቻቸውን መኖርን መረጡ። ዛሬ በኖሪች ከተማ እርሷ በኖረችበት ክፍል አካባቢ ቅድስት ጁልየና ዘኖሪች የሚባል ቤተክርስቲያን አለ። ይህ በለንደን አካባቢ የሚገኘው ከተማ በጊዜው ብዙ ሥልጣኔ የነበረበት ነው።

ቤተክርስቲያኑም ምናልባት በዚች ቅድስት ስም ተጠርቶ ይሆናል። ይህ የብህትውና ሕይወት ሊገርመን ይችላል። በታሪክ የተመለከትን እንደሆነ ግን በዛኛው ዘመን እንደርሷ ብዙ ሴቶች በብሕትውና ከሁሉም ተለይተው ይኖሩ ነበር።

ጁልያናም በዘመንዋ የነበረች ማርጀርይ ዘከምፕ የምትባል ትልቅ ክርስትያን ብ1413 ለመንፈሳዊ ሕይወትዋ የሚረዳት ምክር ለመጠየቅ እርስዋ ጋር ሄዳ እንደነበር በዜና መዋዕልዋ እንደዘገበችው ብዙ ጠያቂዎች እንደነበርዋት እናውቃለን። ለዚህም ነው ጁልያና በመቃብርዋ ድንጋይ ላይ ተፅፎ እንሚገኘው ገና በሕይወትዋ ሳለች ‘እናት ጁልያና’ የሚል ቅፅል የተሰጣት። ለብዙዎች እናት ሆና ነበር።

ከእግዚአብሔር ለመኖር ከሰዎች የሚለዩ ወንዶችና ሴት ልጆች ለምርጫቸው ምስጋና ይግባውና፣ የሌሎች ሰዎች ሥቃይና ድካም ቶሎ ይረዱታል። ከዓለም ቢርቁም ምክራቸውን ፈልገው በራቸውን ለሚያንኳኩ ዓለም ሊሰጠው የማይችል ጥበብ በፍቅር ይሰጣሉ። በዚህ ኣጋጣሚ በዘመናችን ላሉ ከዓለም በመለየት በየገዳማቱ በክላውዙራ የሚኖሩ ኅቡኣንና ኅቡኣት ወንድሞችና እኅቶች ለመላው ቤተ ክርስትያን መዝገብ በመሆን ለዘመናችን ሰዎች በዚሁ በምድረበዳ በሚመሰለው ዓለማችን የሰላምና የተስፋ ገነት በመሆን ሁላችን እግዚአብሔርን ማስቀደም እንዳለብንና ለእምነት ጉዞኣችን በፅናትና በብዛት መፀለይ እንዳለብን ዘወትር ጥሪ ለሚያወርቡልን በማድነቅና በውለታ ለማስታወስ እወዳለሁ።

ጁልያና በብሕትውና በእግዚአብሔር ተሸኝታ ‘የመለኮታዊ ፍቅር ግልፀቶች’ የሚለው መፅሓፍዋን ደረሰች። መፅሓፉ በሁለት መልክ ቀርቦልናል፣ ኣንዱ ኣጭርና ጥንታዊ ሌላው ድርሰት ደግሞ ረዘም ባለ መልክ ነው እኛ ጋር የደረሰው። ይህ መፅሓፍ በእግዚአብሔር የተወደድንና በፍቅሩ የምንጠበቅ መሆናችን በእርግጠኝነት የሚገልፅ መልእክት ኣለው። በመፅሓፉ የሚከተሉትን ኣስደናቂ ቃላት እናንነባለን። ‘እግዚአብሔር ገና ከመፍጠራችን በፊት በምንም ተኣምር በማይጐድል ፍቅር እንዳፈቀረን ጥርት ባለ እርግጠኝነት ኣየሁ፣ በዚህ ፍቅርም ነው ሁሉ ተግባሩን የፈፀመው፣ በዚህም ነው ሁሉ ነገሮች ለእኛ እንደሚጠቅሙ ኣድርጎ የፈጠራቸው፣ በዚህ ፍቅርም ሕይወታችን ለዘለዓለም ትሮራለች፣ እኛም በዚህ ፍቅር ምንጫችን እናገኛለን፣ ይህንን ሁሉ ደግሞ ኣለገደብ በእግዚአብሔር ልናየው ነው።’ ትላለች።

ለጁልያና በተሰጡ ግልፀቶች የዚህ የመልኮታዊ ፍቅር ጉዳይ ተደጋግሞ ይገለጣል፣ ኣንዳንዴም እንደ እናት ፍቅር ልትገልፀው ኣይዳግታትም። በመልእክትዋ በዚህ ዓለም እንደግዝያውያን ነጋድያን ለምናልፍ ለእኛ የሰው ልጆች እግዚአብሔር ያሳየን ፍቅር ፍቅር ታላቅነት ጣዕም ገርነት ስትገልጥ ልክ ኣንዲት እናት ለልጅዋ እንደምታሳየው ፍቅር ትገልጠዋለች። እንደ እውነቱ ከሆነ የመፅሓፍ ቅዱስ ነቢያትም በብዙ ቦታዎች ይህን ምሳሌ ተጠቅመውታል፣ ይህም የእግዚአብሔር ፍቅር ስፋትና ሙላት በፍጥረት በደኅንነት ታሪክ በመጨረሻም በምሥጢረ ሥጋዌ ገልፀውታል። ነቢዩ ኢሳያስ በትንቢቱ 49፤15 ‘እናት የምታጠባውን ልጅዋን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርስዋ ትረሳ ይሆና፣ እኔ ግን አልረሳሽም።’ እንደሚለው የእግዚአብሔር ፍቅር ከሁሉ የሰው ልጅ ፍቅር በላይ ነው። ጁልያና ለመንፈሳዊ ሕይወት የሚያገለግል ዋነኛውን መልእክት ተረዳችው፣ ይህም ማለት፣ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን መገንዘብ፣ ለዚህ ፍቅር ክፍት በመሆን ገዛ ራስን በሙላት መስጠትና በአጠቃላይ በእርሱ በመተማመን ከዚህም ሌላ እርሱ ብቻ የመኖር መሪ እንዲሆን ሁሉን በእጁ በመተው እውነተና ሰላምና እውነተኛ ደስታ በማግኘት በውስጥህ ልታስፋፋው ይቻላል በማለት ታስተምራለች።

ስለ ጁልያና ሌላ ነገርም ለማስታወስ እወዳለሁ፣ በአዲሱ የካቶሊካ ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ከቁ.304-314 ስለ እግዚአብሔር ዕቅድና መለኮታዊ ጥበቃ በሚናገረው ዓምድ ላይ ትምህርትዋ ተጠቅሰዋል፣ እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ በጎና ጥበበኛ ከሆነ ለምድንድር ነው በብዙ ንፁሓን ሰዎች ላይ መጥፎ ነገርና ሥቃይ የሚደርሳባቸው? የሚል ጥያቄ ለብዙ ኣማኞች ፈተና ሆነዋል፣ ቅዱሳን ሳይቀር ይህንን ጥያቄ ኣቅርበዋል፣ ቅዱሳን ግን በእምነት ተገልጦላቸው ልባችንን ለመተማመንና ለተስፋ የሚከፍት መልስ ይሰጡናል፣ ምሥጢራውያን በሆኑ የኣምላክ ኣሳቢነት ዕቅዶች እግዚእብሔር ከመጥፎ ነገር ትልቅ በጎ ነገር ሊያወጣ እንደሚችል ጁልያና እንዲህ ብላ ፃፈች፣ የራእዮች መፅሓፍ’ በሚለው ፅሑፍዋ ምዕራፍ 32 ቍ.173 ላይ ‘እዚህ ላይ በእምነት አጥብቄ መፅናት እንደሚኖርብኝ በእግዚአብሔር ፀጋ ተምሬያለሁ፣ እንግዲህ ጌታ በዘመኑ ሁሉ ለብጎ ፍፃሜ እንደሚሆን ኣቋሜን ማስተካከልና ከልብ ማመን ይገባኛል’ በማለት ሁሉም ነገር ለበጎ መሆኑን ኣስተማረች።

አዎ የተከበራችሁ ወንድሞቼና እኅቶቼ እግዚአብሔር የሚሰጠን ተስፋዎች ዘወትር ከምንጠባበቃቸው ነገሮች በላይ ናቸው። የልቦቻችን ንፁሕና ጥልቅ የሆኑ ፍላጎቻችንን ለእግዚአብሔር ማለትም ለመኮታዊው ፍቅር ያማጠናቸው እንደሆነ አንደለልም፣ ሁሉ በጎ ይሆናል፣ ሁሉ ነገር ለበጎ ይሆናል፣ ጁልያና ዘኖሪች የምታስተላልፍን የመጨረሻ መልእክት ይህ ነው፣ እኔም ዛሬ የማቀብላችሁ ሓሳብ ይህ ነው፣ እግዚአብሔር ይስጥልኝ’ በማለት ትምህርታቸውን ደምድመዋል።

በመጨረሻም ቅዱስነታቸው ስለቻይና ቤተ ክርስትያን ይህንን ጥሪ ኣቅርበዋል፣ ‘በዚሁ ግዜ ለየት ባለ መንገድ ከባድ ችግር ውስጥ ለምትገኝ የቻይና ቤተ ክርስትያን በእናንተና በመላው ዓለም ካቶሊኮች ፀሎት ኣማጥናለሁ፣ እጅግ የማከብራቸው የቻይና ጳጳሳት ተስፋቸውን በምንጠባበቀው መድኃኒታችን በማኖር እምነታቸውን በብርታት እንዲመሰክሩ የክርስትያን ረዳት ለሆነች ብፅዕት ድንግል ማርያም እንድትደግፋቸው እንለምናት፣ ለሁሉም የዚች ተወዳጅ ኣገር ካቶልኪኮች ከኩላዊት ቤተ ክርስትያን ጋር በመተባበር ለውህደትና ለጋራ በጎ የተቻላቸውን በማበርከት ተገቢ የክርስትና ሕይወት እንዲኖራቸው ለድንግል ማርያም እናማጥናቸው።’ በማለት ጥሪ ኣቅርበዋል።

ይህንን ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ትምህርታቸውን ለመስማትና ቡራኬኣቸውን ለመቀብል ከሩቅና ከቅርብ ለመጡ ነጋድያንና ምእመናን በተለያዩ ቋንቋዎች ኣመስግነው አቡነ ዘበሰማያትን በላቲን ቋንቋ በኅብረት በዜማ ኣሳርገው ሐዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።

ቅዱስነታቸው ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ ከፈፀሙ በኋላ በጳውሎስ 6ኛ ኣደራሽል የኤኳቶርያል ጊኒ ፕረሲደንት ተኦዶሮ ኦብያንግ ንጉወማ ምባሶጎ ተቀብለው ኣነጋግረዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.