2010-11-29 15:59:44

ዘመነ ምፅአት የሕያው ተስፋ ግዜ


የላቲን ሥርዓተ ኣምልኮ ግፃዌ በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን የሥርዓተ ኣምልኮ ኣዲስ ዓመት ትናንትና ተጀምሮአል። ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ዘመነ ምፅአት፣ ጌታ ኢየሱስን ለመቀበል በጉጕት የምንጠባበቅበት ግዜ፣ የሕያው ተስፋ ግዜ፣ የዕሴትና የአዲስ ሕይወት ግዜ ነው፣ ሲሉ ገልጠውታል።
ቅዱስነታቸው ቅዳሜ ማታ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ከብፁዓን ካርዲናላትና ጳጳሳት ካህናትና ምእመናን ጋር በመሆን የዘመኑ መግቢያ ሥርዓተ ፀሎት ዘሰርክ ኣሳርገዋል።
በሥርዓቱ መሠረት ፀሎተ ሰርክን ከፈፀሙ በኋላ ባደረጉት ስብከት፣ ‘በዚሁ ሥርዓተ ዋዜማ ኣዲሱን የሥርዓተ ኣምልኮ ዓመትን ለመክፈት ጌታ ፀጋና ደስታ ይሰጠናል፣ ዘመነ ምፅአት እግዚአብሔር በመሀከላችን መምጣቱን የምናስታውስበት ግዜ ነው፣ ኣንድን ነገር ስትጀምር እግዚአብሔር ስለሚባርከው ልዩ ፀጋ ይሰጣል፣ በዚሁ ዘመነ ምፅአትም ዓለምን ወደ ፈጠረና እንደ እኛ ሰው በመሆን ታርካችንን ወደ ሚመራ አምላክ ለመቅረብ ፀጋ እንደሚሰጠን እርግጠኛ ነኝ፣ በዓል ልደትን ለማክበር ለመዘጋጀት በምናደርገው ጉዞ፣ ትልቁ የጌታ ምሥጢር እንደኛ ኣንድ ሰው መሆን ሳይሆን ኣማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑ ነው፣ እናታችን ቤተ ክርስትያን በቅድስት ድንግል ማርያም ኣምሳል፣ እያንዳንዳችንን በዚሁ ምርጥ ግዜ በእጃችን ይዛ በአዳኙና አፅናኝ ፍቅሩ ወደሚቀበለን ጌታ ትሸኘናለች፣ልባችን ዓመታዊ በዓለ ልደት ሲጠባበቅ የቤተ ክርስትያን ሥርዓተ ኣምልኮ ሁል ግዜ በአኰቴተ ቍርባን የምንደግመውን ንዜኑ ሞተከ ሞቱንና ትንሣኤውን እንዲሁም እንደገና በክብር መምጣቱን እንነግራለን ብሎ በማወጅ የጌታን በክብር ዳግም መምጣትን እንድናስብ ጥሪ ታቀርብናለች፣ የጌታን መምጣት በፀሎትና በትጋት እንድንጠባበቅ አደራ ትላለች፣ በራእዩ ለዮሓንስ ፍፃሜ ላይ ተመልክቶ እንዳለው ሁል ግዜ አሜን ማራን ኣታ! ጌታ ኢየሱስ ና ብሎ ጌታን በልበ ምሉነት ለመጥራ ቤተ ክርስትያን እያንዳንዳችንን በማበራታታት ትደግፋለች። በዚሁ ሥርዓተ ፀሎት ተሰብስበን የምንጠባበቀው ለሚወለደው ኣዲስ ሕይወት ነው፣ ምሥጢረ ሥጋዌ የእያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወት ወደር የሌለበት ትልቅ ክብር እንዳለው ይገልጥለናል’ በማለት የዘመነ ምፅአት ትርጉም ኣስተምረዋል።
ቅዱስነታቸው ኣያይዘው፣“በኢየሱስ ማመን ማለት በሰው ልጅ ላይ ኣዲስ ኣመለካከት ማኖር ነው፣ በዚህ ዓይነት እምነት ወደ እግዚአብሔር የቀረብን እንደሆነ በመለኮታዊ ሕይወቱ እንድንሳተፍ ያደርገናል። የሕይወት ተመኵሮና ቅኑ ሕልና እንደሚገልፁልን፣ ሰው መሆን ማለት ራስን ማወቅ የምትመርጠውን አውቀህ በነፃ መምረጥ የፍጥረት ሁሉ መገናኛ ልዩና ሊደገም የማይችል በክብርና በፍቅር ልትቀበለው የሚገባ ፍጥረት መሆኑን ያስተምሩናል፣ ስለዚህ የሰው ልጅ እንደ ማንኛውም ነገር ሊሸጥ ሊለወጥ የሚችል ወይም ግላዊ ፍላጎትን ለማርካት እንደምትጠቀምበት ዕቃ ወይም መሣርያ እንዳታደርገው የሚከለክል መብት ኣለው። የሰው ልጅ ራሱ የቻለ በጎ ነገር ስለሆነ ሁሉን ያካተተ ብልፅግና ያስፈልገዋል። የጌታ ቃልን በመከተል ሁሉን ያፈቀርን እንደሆነ ይህ ፍቅር ብዙ ግዜ ለደካሞችና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እንድናደላ ይገፋፋል። ለዚህም ነው ቤተ ክርስትያን ሊወልድ ባለ ሕይወት ላይ በማትኰር በእናት ማኅፀን ያለው ሕፃን ብዙ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ስለሆነ እርሱን ለመከላከል የሰው ልጆች ኅሊና ይኑራችሁ፣ በማለት ፅንስ ማስወረድ የሰው ሕይወት ማሳለፍ መሆኑን በይፋ የምታስተምረው። ልደቱን ለማክበር የምንዘጋጀው መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእመቤታችን ድንግል ማርያም ማኅፀን በዚህ ሁኔታ ነው የተወለደው፣ እኛም ሁላችን በእናቶቻችን ማኅፀን እንዲሁ ነበርን፣ በማለት የሚወለደው ኣዲስ ሕይወት መንከባከብና መከላከል እንደሚያስፈልገው ገልጠዋል። በመጨርሻም “የሕይወት ምንጭና ኣፍቃሪ የሆነው ጌታ ኢየሱስ በኅሊናችን ለእያንዳንዱ የሚወለደው የሰው ልጅ ሕይወት ክብር እንድንሰጥ ኅሊናችን ያብራልን” ካሉ በኋላ በሥርዓተ ፀሎቱ ለተሳተፉት ሁሉ በማመስገን ስብከታቸውን ፈፅመዋል።
ትናንትና እሁድ እኩለ ቀን የመልአከ እግዚአብሔር ፀሎት ከማሳረጋቸው በፊት ባቀረቡት ጉባኤ አስተምህሮ ደግሞ ‘መንፈሳዊና ሞራላዊ ሕይወታችን በምንጠባበቀውና ተስፋ በምናደርገው ሊለካ ይችላል’ እንደገና ስለዘመነ ምፅአት ኣስተምረዋል።
በዚሁ የዘመነ ምፅአት መጀመርያ እሁድ ዘመኑ የመጠባበቅ ግዜ የኃያል እምነት ግዜ ቢሆንም በየዕለቱ ስለሚካሄደው የሰው ልጅ ሕይወት መሆኑንም መዘንጋት እንደሌለብን እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል። ‘መጠባበቅ ማኅበርዊ ቤተ ሰባዊና ግላዊ ኑሮኣችን የሚመለከት ጉዳይ ነው፣ በሕይወት ጉዞ መጠባበቅ ከትናንሹና ብዙ የማይረቡ ነገሮች እስከ ትላልቅና ኣስፈላጊ በሆኑ ነገሮች በብዙ ሁኔታዎች ሊገለጥ ይችላል፣ ለምሳሌ በቤተ ሰብ ሕይወት ውስጥ ሕፃን ሊወልዱ በመጠባበቅ የሚገኙ፣ ከሩቅ አገር እንዳያችሁ እመጣለሁ ያለንን ቤተ ሰብ በመጠባበቅ ሳለን የሚሰማን ስሜት፣ ወይም ደግሞ አንድ ወጣት ትምህርቱን ጨርሾ የመጨረሻ መልቀቂያ ፈተና ለማድረግ በመጠባበቅ ላይ ያለ እንዴት እንደሚሰማው ብናስብ፣ ወይም ሥራ ለማግኘት ተስፋ ኣግኝቶ የሚጠባበቅ ሰው፣ ወይም ሁለት ፍቅራሞች ተቀጣጥረው ለመገናኘት ሲጠባበቁ ወይም መልእክት ፅፈን መልሱን በጉጉት ስንጠባበቅ ወይም ይቅሬታ ጠይቅን የምሕረት መልስን ስንጠባበቅ፣ ይህን ሁሉ በምናስብበት ግዜ የሰው ልጅ በሕይወት እስካለ ድረስ ሕይወቱ የመጠባበቅ ጉዞ እንዲሁም በልቡ ተስፋ እስካለች ድረስ ሕያው መሆኑን እንመለከታለን። ባጭሩ የሰው ልጅ ከሚጠባበቃቸው ነገሮች ሊታወቅ ይችላል። ሲሉ የመጠባበቅ ስሜትና ትርጉም ከገለጡ በኋላ ወደ ዋናው የዘመነ ምፅአት መልእክት በሚከተሉት ቃላት ኣስተምረዋል። ስለዚህ እያንዳንዳችን በዚሁ ልዩ የሆነ የልደት መዘጋጃ ግዜ ወደ ኅሊናችን በመመለስ፣ የምጠባበቀው ምንድር ነው? በዚች የሕይወት ዘመኔ ልቤ በምን ላይ ያተኵራል? በማለት ኅሊናችን እንመርምር። እነኚህን ጥያቄዎች በግለ ሰው ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ በማኅብረሰብ እና በአገር ደረጃ ልንጠይቃቸው ይገባናል። ሁላችን በኅብረት የምንጠባበቀው ምንድር ነው? ፍላጎቶቻችንን ለማስተባበር የሚችል ምንድር ነው? ብለን እስቲ እንጠይቅ። ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት እስራኤላውያን ለመሲህ የነበራቸው ጉጉትና መጠባበቅ ኃይለኛ ነበር፣ ይህ መሲህ የተቀባ ከንጉሥ ዳዊት ዘር በመሆን ሕዝበ እስራኤልን ከነበራቸው ባርነት የሞራልና የፖሎቲካ ባርነት ነፃ እንዲያወጣቸውና የእግዚኣብሔር መንግሥትን እንዲያሰፋ ይጠባበቁት ነበር። ሆኖም ግን መሲሁ ትሕትና ከተሞላባት ልጃገረድ ለፃድቁ ዮሴፍ ከታጨች እመቤታችን ድንግል ማርያም ይወለዳል ብሎ ያሰበ ኣልነበረም። እመቤታችን ራስዋም ከሕዝበ እስራኤል በጋለ መንፈስ መሲሁን ብትጠባበቅም ከእርስዋ ይወለዳል ብላ ኣላሰበችም፣ እግዚአብሔር ግን ተስፋዋ እምነትዋ ትሕትናዋ ኣይቶ ከእርስዋ እንዲወለድ ወሰነ። ከዘመናት በፊትም ለዚህ መርጦዋት ነበር። ፀጋ በሞላት ፍጥረት በእመቤታችን ድንግል ማርያም መጠባበቅና በእግዚአብሔር መሃከል ዘለኣለማዊው የደኅንነት ዕቅድ ምሥጢራዊ ውህደት ይታያል፣ እንግዲህ እንደ ማርያም የዘመነ መጠባበቅ ሰዎች በመሆን በዕለታዊ ኑሮኣችን በጋለ ጉጕት ጌታን እንጠባበቅ፣ ይህንን መጠባበቅ በሙላት ሊያረካ የሚችለው የእግዚአብሔር መምጣት ስለሆነ ኢየሱስ ጌታ ና ብለን እንጥራ፣ ብለዋል።
ከመልአከ እግዚአብሔር ፀሎት በኋላ ባቀረቡት ሰላምታ ለጌታ ልደት በምንዘጋጅበት ግዜ ልክ እመቤታችን ድንግል ማርያም ለኣዲሱ ሕፃን በጉጕት ትጠባበቀው እንደነበር እኛም ለሚወልድ ኣዲስ ሕይወት ሁሉ የሚገባውን ክብር በመስጠት እግዚአብሔር ስለሕይወት ስጦታ እናመስግን፣ የሰው ሕይወት ምንኛ ትልቅ ስጦታና ፀጋ መሆኑን በመገንዘብ ከፅንስ እስከ ሞት መብቱን በመጠበቅ እናክብረው ካሉ በኋላ በተለያዩ ቋንቋዎች ኣመስግነው ሐዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።።








All the contents on this site are copyrighted ©.