2010-11-22 15:36:52

ለመስቀል በመታዘዝ እምነትን አገልግሉ


ቅዱስነታቸው ትናንትና ከ24 ኣዲስ ካርዲናላት ጋር ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ ባደረጉት ስብከት፤‘የር.ሊ.ጳ አንደኛ አገልግሎት መስቀልን በመታዘዝ እምነትን ማገልገል ነው፤ ካርዲናላትም እንደዚሁ ማድረግ አለባቸው።’ ሲሉ የዕለቱን ቃለ ወንጌል በመጥቀስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሳለ በስተቀኙ ተሰቅሎ የነበረው ያለውን ‘ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ’ ጌታ ሆይ በመንግሥተህ ኣስታውሰኝ ያለው ትርጉሙ በመስቀልም ይሁን በገነት ዋነኛው ነገር ከኢየሱስ ጋር መሆን ነው ሲሉ ዘወትር ከእርሱ እንዳይለዩ ኣደራ ብለዋል።

በተለመደው የእኩለ ቀን የመል አከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮም፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በስደት የሚገኙ ክርስትያኖችን ኣስታውሰው ሶሙኑን በኮሎምብያ በውኃ ማጥለቅለቅ በችግር የሚገኙትን በጸሎት እንደሚያስብዋቸው ገልጠዋል።

ትናንትና በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በተካሄደው የ24 ኣዲስ ካርዲናላት የምሥጋና መሥዋዕተ ቅዳሴ ብዙ ካርዲናላት ጳጳሳት የመንግሥት ባለሥልጣናት አምባሳደሮችና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰበሰቡ ምእመናን በተገኙበት ቅዱስነታቸው መስቀል የታተመበት፤ ከቤተ ክርስትያን ጋር ያላቸውን ቃል ኪዳን የሚያመለክት ቀለበት ለኣዲስ ካርዲናላት ሰጥተዋል።

በላቲን ሥር ዓተ ኣምልኮ የትናንትና እሁድ የክርስቶስ ንጉሥ ትልቅ በዓል ሲሆን ከዚህም ሌላ መደበኛ ዘመን ተፈጽሞ የዘመነ ምጽኣት መባቻም ስለሆነ እፊታችን እሁድ ኣንድ ብሎ የሚጀምረው የልደት መዘጋጃ ዘመነ ምጽኣትን ያውጃል።

ቅዱስነታቸው በዚህ ኣጋጣሚ ሁላችን ስለ ተል እኮኣቸው እንድናስብ በክርስቶስ ንግሥነት ብሎ ከካርዲናላት ጋር ያላቸውን ትሥሥር እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል።

የቅድስ ጴጥሮስ ተከታይ ዋነኛ ተግባር የእምነት ኣገልግሎት ነው፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ልክ ጌታ እንዳለው ኮክሐ ሃይማኖት በመሆን እምነትን ኣስተላለፈልን፤ የቅዱስ ጴጥሮስ እምነት በዚህ ዓለም ኣመለካከት በመጀመርያ ደከም ያለች ነበር፤ ሆኖም ግን ከትንሣኤ በኋላ ቀስ በቀስ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ እያደገችና እየበረታች መጣች፤ ሕይወቱን ስለ ክርስቶስ ኣሳልፎ እስከ መስጠት ጠነከረች፤ ክርስቶስ እውነተኛ ንጉሥ መሆኑን እስከ ማመን ኣደገች፤ ይህም ንጉሥነት በመስቀል ላይ ስለ ሓጢኣተኞች እስከመሞት ዳረገው። ይህ በመስቀል የሚገልጥ የኢየሱስ ድራማ ለሁሉም ሊሆን የሚችል ነው፤ ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር ለሁሉም የሰው ልጆች የሚመለከተው በዚሁ መንገድ ነው። ስለዚህ የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይና ካርዲናላት በእንዲህ ያለ ኣኳሃን ከኢየሱስ ጋር ለመሆን የተጠሩ ናቸው፤ ከመስቀሉ እንዲወርድ ሊጠይቁት ሳይሆን እንደ ማርያም ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ነው የተጠሩት፤ ይህንን ጥሪ ለገዛ ራሳችን ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላዋ ቤተ ክርስትያን ማለትም ለእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ እንድናደርገው ግዳጅ የሚያሽክመን ተል እኮ ነው፤ የመስቀል ጉዳይ ለቅዱስ ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት እጅግ ካስቸገርዋቸው ጉዳዮች ኣንዱ ነው፤ ሰዎች ስለነበሩ በሰው ልጅ ኣስተሳሰብ ያስቡ ነበር፤ ኣዳኝ መሲህ ተብሎ በመስቀል ላይ ይውላል የሚለው ኣሳብ ኣልዋጥ ኣላቸው፤ በዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ ከደብረ ታቦር ግልጸት በኋላ ኢየሱስ ስለ መሰቀሉ ሲነግራቸው ‘ኣይድረስብህ’ በማለት ኢየሱስን ለመከላከል ቅድመ ግንባር እስከ መሆን የተናገረው። ሲሉ ስለ ቅዱስ ጴጥሮስ እምነት ካብራሩ በኋላ ወደ ገዛ ራሳቸው ተለእኮ በመመለስ እንዲህ ብለዋል፤ የእኔም ተልእኮ እንዲሁም የእናንተ ተልእኮ ውድ ወንድሞቼ ባጠቃላይ በእምነት ላይ ነው፤ ኢየሱስ በእኛ ላይ ያችን እውነተኛ እምነት ከመስቀል ልታወርደው የምትፈልግ ሳይሆን ያቺ ትንሣኤ ሙታንን በመመርኰስ በመስቀል ተንጠልጥሎ ባለው ኢየሱስ የምትተማመን እምነትን በእኔና በእናንተ ያገኘ እንደሆነ ኢየሱስ ቤተ ክርስትያኑን በእኛ ላይ ሊገነባት ይችላል፤ የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ የሆነው የክርስቶስ ልኡክ ትክክለኛ ቦታ መስቀል ነው፤ ለመስቀል በመታዘዝም እስከ መጨረሻ መቀጠል ኣልበት። በሰው ኣስተሳሰብ ስለማይሄድ ይህ ተልእኮ ወይም ኣግለግሎት ብርቱ ነው፤ ሆኖም ግን ወደንም ጠልተንም ዋነኛው ተል እኮኣችን ይህ ኣገልግሎት ነው፤ እምነትን ማገልገል፤ ይህ ኣገልግሎት ሕይወትን ሁሉ ይለውጣል፤ ማለትም ኢየሱስ ኣምላክ መሆኑን ማመን፤ እውነተኛ ንጉሥ መሆኑን ማመን፤ ምክያቱም እስከ መጨርሻ ስላፈቀረን፤ ስለዚህ ር.ሊ.ጳ ና ካርዲናላት ከሁሉ ኣስቀድመው በዚህ ኣንድ መሆን ኣለባቸው፤ ካርዲናላት በቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ ተመርተው በመስቀል ቋንቋ እያሰቡና እየሠሩ በኢየሱስ ንግሥነት ሥር መኖር ኣለባቸው፤ ይህም በፍጹም ቀላል ኣይደለም ሆኖም ኣያውቅም፤ በዚህም ነው የክርስቶስ ኣካል መሆን የምንችለው፤ ደስታችንም ይህ ነው፤ መስቀልን በመታዘዝ በክርስቶስ ሙላትና በቤተ ክርስትያን ሕይወት መሳተፍ፤ በቅዱሳን ሕይወት በብርሃኑ መሳተፍ፤ በዚህም ወደ ኣንድያ ልጁ መንግሥት እንሻገራለን። ሲሉ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይና ምስክር ለመሆን መንገዱ የቀራንዮ መንገድ ወይም ፍኖተ መስቀል መሆኑን ኣብራርተዋል።

እኩለ ቀን በመል አከ እግዚአብሔር ጉባኤ ኣስተምህሮ ባስተላለፉት ኣስተምህሮም የክርስቶስ ንጉሥ በዓል በ1925 ዓም በር.ሊ.ጳ ፕዮስ 11ኛ እንደተመሠረተ ኣመልክተዋል፤ ቅዱስ ሉቃስ በዕለቱ ቃለ ወንጌል እንደሚያመለክተው የኢየሱስ መንግሥትና ንጉሥ መሆን በመስቀል በተሰቀለበት ግዜ ‘ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሦሙ ለኣይሁድ’ የሚለው በመስቀሉ የጻፈ ጽሑፍ እንዲሁም በስተቀኝ በኩል ተሰቅሎ የነበረው ፈያታዊ ‘ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ’ ባለበት ግዜ ኢየሱስ ንጉሥ መሆነ ተገለጠ ብለዋል። ከዛ ግዜ ጅምሮ መስቀል የፍቅር ምልክት፤ የድኅነት ምልክት ሆኖ በክርስትያን ሥነ ጥበብ ጌታ ፍቅሩን የገለጠልን ዋና መንገድ ስለሆነ እኛም እንድንከተለው ሲያሳስበን ኖረዋል፤ ካሉ በኋላ የእመቤታችን ወደ ቤተ መቅድስ መግባት የበአታን ሁኔታ ኣስታውሰው ኣዲስ ካርዲናላቱን ለእርሷ በማማጠን የመል አከ እግዚአብሔር ጸሎት ኣሳርገዋል።

ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ በኢራቅ ላይ በክርስትያኖች ላይ የሚካሄደው ስደት እንዲቆም ጥሪ በማቅረብ በሃገረ ኢጣልያ ስለእነርሱ የሚደርገውን ጸሎት ኣመስግነው እሳቸው ስለ እነርሱ እንደሚጸልዩ አመልክተዋል።

በመጨረሻም በኮሎምብያ በውኃ ማጥለቅለቅ ሕይወታቸውን ላጡና ለተጉዱ ወገኖች እግዚአብሔር ጥናቱን እንዲሰጥቸው እንደሚጽልዩ ገልጠዋል።

እንዲሁም በመላው ዓለም ስለክላውዙራ የሚደረገውን ጸሎት ሁሉም እንዲሳተፍ ኣደራ በማለት ሐዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት ኣስተምህሮኣቸውን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.