2010-11-19 16:47:58

የብፁዓን ካርዲናላት ጉባኤ


በላቲን ቋንቋ በኮንቺስቶሪዩም የሚታወቀው በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሰብሳቢነት የሚካሄድ የካርዲናላት ጉባኤ ሕገ ቀኖና እንደሚያዘው መደበና ወይም ልዩ ሊሆን ይችላል። በመደበኛ ጉባኤ በሮማ ያሉ ካርዲናላት ብቻ ሲሳተፉ በልዩ ጉባኤ ግን ሁላቸው ካርዲናላት እንዲሳተፉ ያዝዛል።

ይህ ጉባኤ ኣዳዲስ ካርዲናላት ለመሾምም ይሆናል፤ ባለፉት ዝግጅቶቻችን እንዳመለከትነው ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16 ዘንድሮ 24 ኣዳዲስ ካርዲናላት እንድመረጡና የሹመታቸው ሥነ ሥርዓት ነገ እንደሚካሄድ ኣመልክተን እንደነብር የሚታወስ ነው።

ነገ በቫቲካን ከተማ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በሚካሄደው የካርዲናላት መሾም ሥርዓት ቅዱስ ኣባታችን በመንበረ ሮሜ ሥልጣን ከያዙ ሶስተኛ ጉባኤ ሲሆን፤ የመጀመርያው እ.አ.አ ሚያዝያ 24 2006 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን ያኔ 15 ኣዳዲስ ካርዲናላት ሾመዋል፤ ሁለተኛ ጉባኤ እ.አ.አ ኅዳር 24 ቀን 2007 ዓ.ም ተካሂዶ 23 ካርዲናላት ሲሾሙ ከነዚሁ ኢግናስይ ሉድዊክ ጀዝ የተባሉ ካርዲናል ለመሆን ተመርጠው የነበሩ ከጉባኤው አንድ ቀን በፊት እንዳረፉ የቫቲካን መዛግብት ያመለክታሉ፤ ሦስተኛው ነገ የሚካሄድ ሲሆን በዚሁ ጉባኤ 24 ኣዳዲስ ካርዲናላት ይሾማሉ።

ቅዱስነታቸው ከሾሙዋቸው 62 የሚሆኑ ካርዲናላት 60 ገና በሕይወታቸው ያሉ ሲሆኑ ከእነዚህ ር.ሊ.ጳጳሳት የመምረጥ መብት ያላቸው 50 ካርዲናላት ብቻ ናቸው።

ር.ሊ.ጳጳሳት ካርዲናላት በሚሾሙበት ግዜ በፖሎቲካ ወይም ሌላ ችግር ስማቸውን መጥቀስ ኣዳጋች በሚሆንበት ግዜ በላቲን ቋንቋ ካርዲናለ ኢን ፐክቶሪስ በሚል የሚታወቀው ስም ሳይጠቅሱ እሳቸው ብቻ የሚያውቁት ካርዲናልም ሊሾሙ ይችላሉ።

ካርዲናል ሆነው የተሾሙ ኣባቶች በሮም ሃገረ ስብከት የሲመት ቊምስና ሊኖራቸው ያስፈልጋል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ ካርዲናል በሮም ሃገረ ስብከት ቊምስና ኣለው።

የካርዲናላት ጉባኤ ኣዲስ ር.ሊ.ጳ ለመምረጥ በሚሰበሰቡበት ግዜ በላቲን ቋንቋ ኮንቭላቨ የሚል ስም ይሰጠዋል፤ ጉባኤው የሚመራበት ልዩ ሕግም ኣለ።

ከር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ በፊት የነበሩ ስመ ጥር የእግዚአብሔር ኣገልጋይ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሥልጣን ዘመናቸው 9 የካርዲናላት ጉባኤዎች እንዳካሄዱና ባጠቃላይ 231 ካርዲናላት እንድሾሙ ከእነዚህ ካርዲናላት 139 ገና በሕይወት እንዳሉ ከእነርሱም 71 ብቻ ር.ሊ.ጳ የመምረጥ መብት እንዳላቸው ይመለከታል።

የኣዲስ ብፁዓን ካርዲናላት ሥርዓተ ሲመት ነገ በሮም ሰዓት ኣቆጣጠር 9፡50 በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ይካሄዳል፤ በተመለከተው ሰዓት እያንዳንዱ ካርዲናል ከጸሓፊያቸው በሁለት ወረፋ ተሰልፈው ይጠባበቃሉ፤ ልክ 10፡30 ቅዱስነታቸው በካርዲናላት ተመርተው ‘ቱ ኤስ ፐትሩስ’ ኣንተ ጴጥሮስ ነው የሚለው የላቲን ዜማ እየተዘመረ ወደ መንበረ ታቦት ገብተው ሥር ዓተ ሲመቱን ይጀምራሉ። ከኣዲስ ካርዲናላት የመጀመርያው በካርዲናላት ስም ለር.ሊ.ጳ ሰላምታ ያቀርባሉ፤ ቅዱስነታቸው እንጸሊ ብለው የመባቻ ጸሎት ያሳርጋሉ። ከዛ በላቲን ቋንቋ የመጀመርያው ንባብ ይነበባል፤ መዝሙረ ዳዊት ይዘመራል፤ የወንጌል ሃሌታ ተዘምሮ ቅዱስ ወንጌል ይነበባል፡ ቅዱስነታቸው ስብከት ያሰማሉ፤ ከስብከት በኋላ ቅዱስነታቸው ኣዲስ ካርዲናላት እምነታቸውን ለመግለጥ ጸሎተ ሃይማኖት እንደደግሙ ይጠይቃሉ ካርዲናላቱም ጸሎተ ሃይማኖትን ደግመው እያንዳንዳቸው ለር.ሊ.ጳጳሳትና ተከታዮቹ ታማኝ እንደሚሆኑ ቃለ መሀላ ይፈጽማሉ።

ቅዱስነታቸው ቀይ ቆብ እግዚአብሔርን ለማክበር መሆኑን ገልጠው ለእያንዳንዳቸው ‘እግዚአብሔርን ለማክበር ቀይ ቆብ ተቀበል’ እያሉ ይሾሙዋቸውል፤ ኣዲስ ካርዲናላቱም በቅዱስነታቸው ግራና ቀኝ በመሰለፍ ተንበርክከው ቀይ ቆብ እና ኣክሚም ይቀበላሉ፤ ቅዱስነታቸውም ለእያንዳንዱ የኣገልግሎት ተል እኮውን ይናገራሉ። በመጨረሻም ቅዱስነታቸው የጌታ ሰላም ሁል ግዜ ካንተ ጋር ይሁን ባሉበት ግዜ ከመንፈስህ ጋራ በማለት ሰላምታ ይለዋወጣሉ።

ሥር ዓተ ሲመቱ ከተፈጸመ በኋላ ጸሎተ ስእለታት ይደገማል፤ ቅዱስነታቸውም ‘ኣባታችን በሰማይ የምትኖር’ በማለት ሁላቸውም እንዲያዘሙ ይጠይቃሉ፤ ከዜማው በኋላ ቅዱስነታቸው ሓዋርያዊ ቡራኬ ይሰጣሉ፤ የሥርዓተ ሢመቱ ፍጻሜም ይሆናል።

ኣዳዲስ ካርዲናሎች ማምሻውን በሮም ሰዓት ኣቆጣጠር ከ4፡30 እስከ 6፡30 ከቤተ ሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር እንደሚገናኙም ተመልክተዋል።

የምስጋና ቅዳሴ በነገታው እሁድ እንደ ላቲኒ ሥርዓተ ኣምልኮ ግጻዌ የክርስቶስ ንጉሥ በመሆኑ ከቅዱስ ኣባታችን ጋር ኣብረው በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ መሥዋዕተ ቅዳሴ ያሳርጋሉ። በዚሁ የሥርዓተ ሢመቱ ፍጻሜና ምስጋና ላይ ቅዱስ ኣባታችን ለእያንዳንዱ ኣዲስ ካርዲናል የታማኝነትና የሥልጣን ምልክት የሆነው ቀለቤት ይሰጣሉ።








All the contents on this site are copyrighted ©.