2010-11-17 16:14:45

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምህሮ (17.11.2010):


ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተለመደው ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምህሮ መክፈቻ ጸሎት ካሳረጉ በኋላ ከአንደኛው የሐዋርያው የጳውሎስ መል እክት ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች 10፡16 ‘እግዚአብሔርን አመስግነን የምንካፈለው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? አብረን የምንቆርሰውስ ኅብስት ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? ኅብስቱ አንድ በመሆኑ፥ እኛ ከዚህ ከአንዱ ኅብስት የምንካፈል ስለሆንን፤ ምንም እንኳ ብዙዎች ብንሆን አንድ አካል ነን። ‘ የሚለው በተለያዩ ቋንቋዎች ከተነበበ በኋላ በጣልያንኛ ቋንቋ ሰፋ ያለ ትምህርት ኣቅርበው የሚከተለውን ኣጭር ኣስተምህሮ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ኣቅርበዋል፤ “ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ የዛሬ ትምህርተ ክርስቶሳችን ስለ ቅድስት ጁልየን ዘኮርኒሎን ይሆናል፤ ቅድስትዋ በበለጠ የምትታወቀው በቅድስት ጁልየን ዘልየጅ በሚል ስም ነው። በ12ኛ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ተወልደዋል፤ በሕጻንነትዋ ወላጅ ኣልባ ጉድፈቻ በመሆን ኣድጋ የአጐስቲንያን ደናንግል ኣባል በመሆን መነኰሰች። ብልኅና በሁሉም የበሰለች ሆና ኣደገች፤ በገዳማዊ ሕይወትዋ በልዩ የምትታወቀው ታዘውትረው በነበረችበት ረዥም ኣስተንትኖና ለጥቀ ቅዱስ ቊርባን ታደርገው በነበረችው ስግደት ነው። ጌታ በገለጠላት መሠረት ቅድስት ጁልየን ለጥቀ ቅዱስ ቊርባን ክብር የሚደርጉ የሥር ዓተ ኣምልኮ በዓላት እንዲዘወተሩ በሙሉ ልብዋና ኃይልዋ ሠርታለች። በዘመናችን ከበዓለ ጰራቅሊጦስ በኋላ በትልቅ ኣክብሮት የምናዘወትረው በዓለ ጥቀ ቅዱስ ቊርባን ኮርፑስ ዶሚኒ ለመጀመርያ ግዜ በልየጅ ሃገረ ስብከት ተከብረዋል፤ ከዛ ጀምሮ በመላው ዓለም ተስፋፋ። ጁልየን ዘልየጅን በቦታው ያውቅዋት የነበሩ ስመ ጥር ር.ሊ.ጳ ኡርባን 4ኛ ይህ ትልቅ በዓለ ቅዱስ ቊርባን በመላዋ እንተ ላዕለ ኩሉ ቤተ ክርስትያን እንዲከበር አውጀዋል፤ ለቅዱስ ቶማስ ዘአኲኖ ደግሞ ለዚሁ ትልቅ በዓል ሥርዓተ ኣምልኮ የሚሆኑ ድርሳናት እንዲያዘጋጅ ት እዛዝ ሰጥተዋል። ር.ሊ.ጳ ኡርባን ያኔ መንበረ ር.ሊ.ጳጳሳዊ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት በነበረችውና ከበዓሉ አንድ ዓመት በፊት የቅዱስ ቊርባን ተኣምር በተካሄደባት እንዲሁም በተኣምሩ ወደ እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም የተለወጠው ኅብስትና ወይን በሚገኝባት በኦርቪየቶ ከተማ ለመጀመርያ ግዜ በዓለም ኣቀፍ ደረጃ የጥቀ ቅዱስ ቊርባን በዓልን ኣክብረዋል።

ቅድስት ጁልየን ዘኮኒልሎን በምናስታውስበት ግዜ የክርስቶስ በቅዱስ ቊርባን እውነተኛ መኖር እምነታችንን እናሳድስ፤ ዛሬ በቤተ ክርስትያን የምንመሰክረው የቅዱስ ቊርባን ዘመነ ጸደይ ለቅዱስ ሥጋሁና ለቅዱስ ደሙ የምናቀርበው ስግደት ሁል ግዜ እንዲያድግ እንጸሊ’ ሲሉ ትምህርታቸውን ከፈጸሙ በኋላ በዘመናችን በተለይ ባሁኑ ወቅት በመላው ዓለም በተለያዩ ቦታዎችና ምክንያቶች ክርትያንን የሚያሳድዱ ወደ ልባቸው ተመልሰው የሰው ልጅ ክብርና መብት እንዲያከብሩ ኣደራ በማለት በተለይ በፓኪስታን ውስጥ ስለሚፈጸመው ዓመጽና ኣድልዎ የሚከተለውን ጥሪ ኣቅርበዋል። 'ባሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በፓኪስታን በሚገኙ ክርስትያኖች ላይ እየተፈጸመ ባለው ጥቃትና ማጒጒላት ምእመናኑ የሚያሳልፉትን ከባድ ሁኔታ በትልቅ ሥጋት እየተከታተለው ነው፤ በተለይ ዛሬ በተመሠረተባት የአምላክ ስም በከንቱ ማንሣት ክስ ለሞት ለተፈረደችው አስያ ቢቢና ቤተሰቦችዋን በጸሎት እንደማስባቸውና በመንፈስ ቅርበቴን ስገልጥ ሁኔታው ታይቶ በተሎ ነጻነትዋን እንድታገኝ እጠይቃለሁ፤ እንዲሁም በመላው ዓለም በተለያዩ ቦታዎች በተመሳሳይ ሁኔት እየተቸገሩ ላሉ ክርስትያኖች ሰብአዊ ክብራቸውና መብታቸው እስኪጠበቅ ድረስ ስለእሳቸው እጸልያለሁ'። ካሉ በኋላ በተለያዩ ቋንቋዎች ኣመስግነው ሓዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.