2010-11-03 16:15:16

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምህሮ (03.11.10):


ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ በጳውሎስ 6ኛ ኣደራሽ ለተለመደው ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምህሮ መክፈቻ ጸሎት ካሳረጉ በኋላ ከሉቃስ 18፡28 5፡17 “ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል። አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። በእውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን ወይም ወንድሞቹንወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የሚተው ሰው የበለጠ ያገኛል፥ ይኸውም አሁን በዚህ ዓለም ብዙ እጥፍ ይቀበላል በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት ያገኛል ማለት ነው፤ ኣላቸው። ” የሚለው በተለያዩ ቋንቋዎች ከተነበበ በኋላ በጣልያንኛ ቋንቋ ሰፋ ያለ ትምህርት ኣቅርበው የሚከተለውን ኣጭር ኣስተምህሮ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ኣቅርበዋል። ‘ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ የዛሬ የትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምህሮኣችን በ13ኛ ክፍለ ዘመን የካርቱዝያን ገዳም እመምኔትና በብሕትውናና ሰቂለ ኅሊና ትኖር ስለነበረች ስለ ማርገረት ዘዋጝ ይናገራል፤ የማርጋረት ጽሑፎች በፈረንሳይ ክፍለ ሃገር ስለነበሩ ገዳማት እንደ መጀመርያ ኣብነት ሲጠቀሱ በቅዱስ ብሩኖ ወንጌላዊ መንፈሳውነት የተመሠረቱ ናቸው፤ እነዚህ ጽሑፎችዋ የማርጋረት ብልኅ ኣስተዋይነትና ለእግዚአብሔር የነበራት ጥልቅ ፍላጎት ይገልጣሉ።

ማርጋረት ሕይወትን እንደ ፍጽምና ጉዞ ታየው ነበር፤ ይህም የፍጽምና ጉዞ የኢየሱስ ኣዳኝ ሕማማትን በማስተንተን ከኢየሱስ ጋር ኣንድ በመሆን ከእርሱ እስከ መዋሃድ ነው። የኢየሱስ ሕይወት ቃላቱ እና ተግባሩ እንደ ኣንድ መጽሓፍ ኣድርጋ ትረዳው ነበር፤ በእርሷ ኣመለካከት ኢየሱስ ይህን መጽሓፍ እፊታችን ከፍቶ ኣስቀምጦታትል፤ መጽሓፉ መጠናት ያለበት ትልቅ ሥጦታ ነው፤ ቅድስት ሥላሴን በማስተንተን ኣንድ ቀን ከውስጣችን ልናነበው እስከንችል ድረስ መጽሓፉን ማጥናት ኣለብን፤ እንዲሁም በልባችንና በሕይወታችን መታተም ያለበት መጽሓፍ ነው።

የማርገረት ጽሑፎች ከቤተ ሰብ ሕይወት በተወሰዱ ኣምሳሎች የተቀረጸ ነው፤ መጽሓፉም የጋለ የእግዚአብሔር ፍቅርን ያንጸባርቃል፤ ስሜታችን በማንጻት ወደ እርሱ የሚያቀርበን ጸጋ ስለሰጠንም ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባል።

የማርገረት ዘኦይጝት ሕይወትና ጽሑፎች በየዕለቱ ክርስቶስ በመስቀል ተንጠልጥሎ በተቀበለው ሥቃይ የሚገለጠውን መጨረሻ የሌለው የእግዚአብሔር ፍቅር ምሥጢርን እንድናስተነትን በዚህ ፍቅር ደግሞ ሕይወታችንን ለእርሱ ለወንድሞቻችንና ለእኅቶቻችን ኣገልግሎት እንድናውል ኃይልና ደስታ እንድናገኝ ይጠራናል፤’ ሲሉ ትምህርታቸውን ደምድመዋል።

ቅዱስነታቸው ኣስተምህሮኣቸውን ከፈጸሙ በኋላ በተለያዩ ቋንቋዎች ኣመስግነው በዚሁ ሳምንት በላቲኑ ሥር ዓተ ኣምልኮ የቅዱሳን ሁሉ ዝክር በማስታወስ ቅዱሳኑ በዚሁ ዓለም ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንኖርና ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ኣገልግሎት ክፍት እንድንሆን ዕድሜ እንድሚያቀርቡልን በማስታወስ በተለይ ወጣቶች ትርጉም ያለው ክርስትያናዊ ሕይወት እንዲኖሩ የቅዱሳን ምሳሌ እንዲከተሉ ኣደራ በማለት ኣባታችን በሰማይ የምትኖር በላቲን ከም እመናኑ ጋር በማዜም ሓዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.