2010-10-30 15:06:30

ዘጽጌ 4ኛ


መዝ. በጊዜሁ ኀለፈ ክረምት ቆመ በረከት

ንባባት፤ ሮሜ 7፡1~14፤ 1ጴጥ. 11፡21~ፍጻ፤ ግ.ሓ. 22፡1~6 ወን. ማቴ 6፡25 ~ ፍጻሜ።

ምስማክ፤ አንተ ፈጠርከ ፀሐየ ወወርኃ፡ ወአንተ ገበርከ አድባረ ወምድረ ኲሎ፡ ክረምተ ወሐጋየ ዘዐንተ ፈጠርከ (ፀሐይንና ጨረቃን የፈጠርክ አንተ ነህ፤ አንተ የምድር ዳርቻ ‘ተረራውን ኮረብታውን ሁሉ’ ሠራህ፤ በጋን ክረምትን አንተ ፈጠርክ። መዝ. 73፡17)

ቅዳሴ ዘማርያም

ከሲታውያን ማኅበር ድረ ገጽ (Ethiocist.org) የተወሰደ ኣስተንትኖ። ‘ከዛሬው ወንጌል ከመጀመሪያው ቁጥር ቀደም ብሎ ያለው ቁጥር ላይ ክርስቶስ “አንድ ሰው የሁለት ጌታ አገልጋይ ሊሆን አይችልም፤ አንዱን ይጠላል ሌላውንም ይወዳል፤ አንዱን ያከብራ ሌላውን ይንቃል” በማለት ይጀምርና በማስከተል የሰው ልጅን ልብ ባርያ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮችን ይጠቁማል። ገንዘብ፣ ልብስ፣ ምግብ ማንነታችንን ጠቅልለው ሊይዙ እንደማይገባም ለማጉላት “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?” ይላል። በርግጥ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የመፈጠሩ እውነት ከሌሎች ፍጡራን ሁሉ የተለየ ክብርና ማንነት የተሰጠው ፍጡር እንደሆነ ታላቅ አመላካች ሀሳብ ነው።

ከፈጠርካቸው ነገሮች ሁሉ ከፍተኛ ደረጃ የምትሰጣቸው ፍጥረታት በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሦስት ምንድናቸው ተብሎ እግዚአብሔር ቢጠየቅ ሊሰጥ የሚችለውን መልስ ብንገምት፤ መልሱ:- አንደኛ ሰው፣ ሁለተኛ ሰው፣ ሦስተኛ ሰው የሚል መሆኑን ልንስማማ እንችላለን። ምክንያቱም አንደኛ ልጁን ለዘግናኝ ስቃይና ሞት አሳልፎ የሰጠው ስለኛ ብቻ በመሆኑ ነው። እንዲህ የተከፈለባቸው ፍጥረታት ደግሞ ለአላፊ ነገሮችና እቅድ ራሳቸውን ባሪያ ሲያደርጉ የክርስቶስን መስዋዕትነትና ሞት ትርጉም የለሽ ማድረግ ነው።

ብዙ ጊዜ ጥሩ ብለን የምናስበው የትምህርት መንገድ ላይ ስንገባ ትልቁ እውቀትና እውነት ክርስቶስ መሆኑን ማሰብ ያዳግተናል። እንዲሁም ፍቅር ይዞኛል ወይም ከፍቅር ጋር የተያያዘ ነው የምንለውን ማንኛውንም ነገር ስናስብ ትልቁ ፍቅርና በዚህች ምድር ሊይዘን የሚችለው ፍጹም ፍቅር የክርስቶስ ፍቅር መሆኑን እንዘነጋለን። በዚህም መልኩ እውቀታችንና ፍቅራችን የምንለውን ነገር ከክርስቶሳዊው እውቀትና ፍቅር ጋር አስታርቀን ማየቱ አስቸጋሩ ይሆንብናል። እንደውም ከርሱ የመራቅያ ምክንያት ይሆኑብናል። ወንጌሉ ለንደዚህ ዓይነት የተገደበ የፍቅርና የእውቀት ግንዛቤ ችግር ከምታስቡት በላይ እውነት፣ ከምትገምቱትም በላይ ፍቅር አለ ይለናል። “እናንተኮ እጅግ ትበልጣላችሁ፤ ከጊዜያዊው እውቀትና ከአላፊው “ፍቅር” የበለጠ ነገር ተዘጋጅቶላችኋል” ነው መልእክቱ።

ሁሉ ነገር አሁኑኑ ለሚል ዓይነት ትውልድ ይህ እውነት ቀላል አይሆንም፤ ምክንያቱም “ስልጣኔው” ሁሉ የሚለን አሁኑኑ ይምጡ፤ አሁኑኑ ይጎብኙን፣ በቶሎ ይዘዙ…ነገር ስለሆነ ስንዴ ካልሞተ አያፈራም፤ ሊከተለኝ የሚፈልግ ሁሉ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ የሚል ዓይነት ትምህርትና የሕይወት ምስክርነትን ከሚያዘው ክርስቶሳዊ ትምህርት ጋር ይጋጫል። ስለዚህ ለጊዜያዊው ነገር አትጨነቁ የሚለው እውነት እንዲገባን መጀመሪያ የነገሮች መሟላትን መጠበቅ ሳይሆን መጨነቅን መተው አለብን፤ ይህ ደግሞ ከምንም ጥበብ ወይም ችሎታ ሳይሆን የክርስቶስን ቃል ከማመን የሚመጣ ነው። ካልሆነ ሊገባን አይችልም፤ የማይቻል ነገርና ውሸትም ሊመስለን ይችላል፤ ሰው እንዴት ስለነዚህ ነገሮች ሳይጨነቅ መኖር ይችላል? ያስብላል።

አንድ ተራ መሳይ ታሪክ ከላይ የጠቀስነውን ታላቅ እውነት ሊያስረዳን ይችል ይሆናልና እንየው። በአንድ ትንሽ ኩሬ ውስጥ ትኖር የነበረች አንድ እንቁራሪት የሷ ኩሬ ውስጥ ሌላ እንቁራሪት በማየቷ ግርም ይላትና “ከየት ነው የመጣሽው” ብላ ጠየቀቻት። “የመጣሁት ከባሕር ነው። እዚያ ነው የምኖረው” ብላ መለሰችላት። የመጀመሪያዋ ከኩሬ ሌላ አታውቅምና “ባሕር ምንነው የኔን ኩሬ ያህል ይተልቃል” በማለት ሌላ ጥያቄ አስከተለች። ከባሕር የመጣችው እንቁራሪት ከት ብላ በመሳቅ “ሁለቱንማ ማወዳደር አይቻልም” አለቻት። የመጀመሪያይቱ እንቁራሪት ከባሕር እንቁራሪቷ የሰማችው ነገር ጉጉት ቢያሳድርባትም ቅሉ በሀሳቧ ግን “በሕይወቴ ዘመን ከሰማኋቸው ውሸቶች ሁሉ ያለጥርጥር የዛሬውን የሚወዳደር ትልቅ ውሸት የለም” አለች። አንድ ነገር ምንም እንኳ ጥሩና የሚያጓጓ ነገር ቢሆንም ካልተኖረ መረዳቱ ይከብዳል። የክርስቶስ አዳማጮች እሱ የሚናገራቸው እውነቶች ይከብዳቸው ነበር። እኛም ዛሬም በቃሉ ፊት ተመሳሳይ ክብደት ሊሰማን ይችላል፤ ግን ክርስትና ሲኖር ብቻ የሚጣጣም ዓይነት ስለሆነ መኖሩን ካልጀመርን በስተቀር ጣዕሙና ትርጉሙ አይገባንም።

እንደኩሬ ጠባብ ዓላማ ውስጥ ራሳችንን ከትተን ስለ ባሕርና ውቅያኖስ ማሰብ የተሳነን ከሆነ ለሕይወታችን ኩሬ የሆነብንን ነገር እንመርምረው፤ ከዚያ ካልወጣን ሌላውን ማሰብ የማይቻል ነገር ነው። ዛሬ ዛሬ ዘመናዊነትን የተላበሰ በሚመስል መልኩ ቢሆንም  የሚያዝ፣ የሚጨበጥና በፍጥነት ስሜትን ሊያረካ የሚችል ነገር ሁሉ ቅድሚያ ሲሰጠው እናያለን። እውነተኛውን እውነት፣ እውነተኛውን ውበትና እውነተኛውን መልካም ነገር ሁሉ በጣም ጊዜያዊና ቶሎ ያስደስቱናል ብለን በምንገምታቸው ነገሮች ሁሉ ለውጠን መኖሩ የተለመደ ይመስላል። በዚህም ምክንያት ግብረገባዊ አናኗር ወይም የእምነት ሰው መሆን የዘመኑ ክፍል እንዳለመሆን ስለሚቆጠር እምነታችንን ማለትም ክርስቶሳዊነታችንን በተለያየ መልኩ ለመሸሸግ እንሞክር ይሆናል። ይህን ስንል በምን መልኩ ክርስቶስን በዕለታዊ ሕይወቴ እንደማይታይ አደርገዋለሁ ወይም እኔ እርሱን የማላውቅ መሆኔን የሚናገሩ አዋዋሎቼ የትኞቹ ናቸው ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።

ወንጌላችን በምንም መልክ እንድንጨነቅ አይፈልግም፤ ይህ ማለት ግን ክርስትና አልጋ በአልጋ ነው ማለት እንዳልሆነና ድህነትን ወይም የሥጋ በሽታን አያካትትም ማለት አይደለም። ወንጌል አያታልልም፤ ስለ መስቀል፣ ስደትና ሞትም ጭምር ይነግረናል። ክርስትና ማለትን ቀለል አድርጎ መውሰዱ ሊያሳስት ይችላልና አትጨነቁ ስለተባልን ችግር የሌለበት ሕይወት ማለት አለመሆኑን ነገር ግን በችግራችን ክርስቶስና ትልቅ ዓላማ ስላለን በደስታና በፍቅር እንኖረው ዘንድ መጠራታችችንን ማስታወስ አለብን። “ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?” ሲል ማንም የሚል የጋራ ምላሽ ይኖረን ይሆናል። ታዲያ ለምን ትጨነቃላችሁ ብንባል ግን እንደቁጥራችን የተለያየ መልስ ነው የሚኖረን። እንዲሁም “ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?” ሲል አሁንም እንበልጣለን ...ይሆን ይሆናል መልሳችን በገሀዳዊው አናኗራችን ግን እንጨነቃለን። ማስተዋል ያለብን መልሳችን በተጋጨ ቁጥር አናኗራችንም ከእምነታችን ጋር መጋጨቱን ነው።

እግዚአብሔር አይረሳም አይንቅምም። በእሱ ፊት ችላ የሚባል አንዳችም ፍጥረት የለም። በሰው ዓይንና ግንዛቤ ግን በሆነ መስፈርት የምንንቀው፣ ችላ የምንለው እንደውም መኖሩንም የምንረሳው ሰው ስላለ እግዚአብሔርም እንዲሁ የሚያደርገን እየመሰለን እንፈራለን። ለርሱ ግን የዱር አበባና የሰማይ ወፎች እንኳ የተረሱ አይደሉም።

ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰው ልጅ ሕይወት ስትሟገት በጣም በቂ ምክንያት አላት። አንድ ሰው በየትኛውም የዕድገት ደረጃ ቢሆን ችላ ሊባል አይገባም፤ መናገር ቢችል ባይችል፣ ራሱን መከላከል ቢችል ባይችል፣ እኛ ልንረሳው ብንፈልግ ባንፈልግ…ወዘተ በእግዚአብሔር ፊት እንኳን ሰው የዱር አበባና አዕዋፍ ሁሉ ብርቅዬ ናቸው። ይህን መሰል እውነት ውስጣችን ካደገ ዓለም ብዙ ነገር እያሳየች ስትነሳን ወይም ሳታስጨብጠን ዞር ስትልብልን የእግዚአብሔር አሳቢነትና አዘጋጅነት ለኛ ደስታ ይሆናል።

አንድ ሰባኪ እንደተናገረው “ቤተ ክርስቲያን የኃጢአተኞች ሆስፒታል እንጂ የቅዱሳኖች ሙዚየም አይደለችም” ና ጭንቀታችንና ደካማነታችንን ሁሉ ይዘን በክርስቶስ መስዋዕትነት ለማስወገድ ራሳችንን የቅዱሳን ምስጢራት ተሳታፊ ማድረግን እንወስን።  የእምነት ሕይወታችንም ያብብ ዘንድ እነዚህን በጣም በተስፋና በእምነት የሚሞሉ ጥቅሶች ሌላ ማንም ሳይሆን የተናገረው ክርስቶስ ነውና በልባችን ውስጥ እናስገባው። “እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?”።’








All the contents on this site are copyrighted ©.