2010-10-25 16:40:31

የጥቀ ክቡር ደም ማኅበር ደናግል ኣባል የነበሩ እናቴ ኣልፎንሳ ክለሪቺ ብፅዕት ተባሉ


ሕይወትዋን ሙሉ በማስተማርና ድሆችን በመርዳት ያሳለፈች እናቴ ኣልፎንሳ ክለሪቺ ትናንትና በቨርቸሊ ርእሰ ኣድባራት የቅዱሳን ጉዳይ የሚከታተል ማኅበር ኃላፊና ባለፈው ሳምንት ቅዱስ ኣባታችን ከሾማቸው ካርዲናሎች ኣንዱ የሆኑ ብፁዕ ኣቡነ ኣንጀሎ ኣማቶ ባሳረጉት መሥዋተ ቅዳሴ ሥርዓተ ብፅዕና ተፈጸመላቸው።

እናቴ ኣልፎንሳ በሚላን በ1860 ዓም ተወልደች፤ ቤተ ሰቦችዋ ከሚላኖ ሲሆኑ በእርሻ ይተዳደሩ እንደነበሩና እናቴ ኣልፎንሳ ከ10 ልጆች በኲር መሆንዋን የሕይወት ታሪክዋ ይገልጣል፤ ጥሩ መሠረታዊና ክርስትያናዊ ኣስተዳደግ ኣገኘች፤ ትምህርትዋ ፈጽማ እንደመምህር ስትሠራ የድንግልና ጥሪ ስለተሰማት ድንግል ሆነች፤ ድንግል ከሆነች በኋልም ማስተማርን ቀጠለች፤ ብዙ የሰራችው በቨርቸሊ ነበር፤ ከጌታ ጋር በነበራት ግኑኝነት ሁል ግዜ ደስተኛ ስለነበር ብሩህ ገጽ ነበራት ሌሎችንም ታስቅና ታደስት ስለነበር የነፍስ ደስታ የሚል ቅጽል ተሰጥቶዋት ነበር።

ሥርዓተ ብፅዕናዋን የፈጸሙ ብፁዕ ኣቡነ ኣማቶ ስለ ትዕግሥትዋና ልግሥናዋ ሲናገሩ፤ የሱባኤ ኣላፊ በመሆን ባገለችበት ወቅት ወጣቶችን በፈጸሙት ጉድለት ሳትወቅስ በት ዕግሥትና ፍቅር በመላበት መንገድ ጉድለት ከመፈጸም እንዴት መከላከል እንዳለባቸው ታስተምር ነበር፤ ብለዋል። ድሆችንም እንዲሁ በትሕትናና በት ዕግሥት ዘወትር ታገለግል ነበር። ድሆችን ማገልገልና ማፍቀር ጌታ ኢየሱስን ማፍቀርና ማገልገል ነው በማለት ምን ልስጣቸው ብላ ሳትቸገር በእግዚአብሔር ኣሳቢነት በመታመን ያገነችውን ከድሆች ጋር ትካፈለው ነበር፤ በሕመማቸው በሓዘናቸው ዘወትር እጐናቸው በመሆን ታዝናናቸው ነበር። ሲሉ ብፅ ዕት እናት ኣልፎንሳ ኣብነታዊ የእግዚአብሔር ሰው መሆንዋን ገልጠዋል።

ቅዱስነታቸውም ትናንት የመልኣከ እግዚአብሔር ጸሎት ባሳረጉበት ወቅት፤ ‘ትናንትና በቨርቸሊ የሞንዛ የጥቀ ቅዱስ ደም ደናግል ኣባል የነበረች፤ እናቴ ኣልፎንሳ ክለሪቺ ብፅ ዕት ተብላ በመታወጁ ደስ ብሎኛል፤ ላይናተ በሚባል የሚላን ቀበሌ ብ1860 ዓ.ም ተወልዳ በቨርቸሊ በ1930 ዓም ሞተች። ወደ ፍጹም ፍቅር የመራትን እግዚአብሔር እናመስግን፤’ ሲሉ ደስታቸውን ገልጠዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.