2010-10-10 11:52:16

የመሃከለኛው ምሥራቅ የጳጳሳት ሲኖዶስ


የመሃከለኛው ምሥራቅ የጳጳሳት ሲኖዶስ ዛሬ ተከፈተ። የመክፈቻውን መሥዋዕተ ቅዳሴ ዛሬ ጥዋት በሮም ሰዓት 9፡30 ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ በ177 የሲኖዶሱ ኣበውና 69 የሲኖዶሱ ተባባሪ ካህናት ተሸኝተው በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ኣሳርገዋል።

ቅዱስነታቸው ከፍተኛ የምሥጋና ጸሎት የሆነው መሥዋዕተ ቅዳሴ ዛሬ ለምን እንደሚያቀርቡት በስብከታቸው እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፤ ‘ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ከፍተኛ የምሥጋና ጸሎት የሆነው ዛሬ በቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር ስናሳርግ ለልዩ ምክንያት ነው፤ የመሀከለኛ ምሥራቅ የሲኖዶስ ኣባቶች ለመጀመርያ ግዜ ከሮማው ጳጳስና የእንተ ላዕለ ኩሉ ቤተ ክርስትያን እረኛ ጋር ኣብረው ለመቀደስ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ጸጋ ልዩ በመሆኑ ልዩ ምሥጋና እናቀርባለን። ይህ ልዩ ፍጻሜ ቤተ ክርስትያን ለክቡርና ለተወደደው በቅድስት መሬትና በመላው መሀከለኛ ምሥራቅ ለሚኖረው የእግዚአብሔር ሕዝብ ያላትን ፍቅር ይገልጣል’ ሲሉ እግዚአብሔር በዚሁ የዓለም ክፍል የፈጸመውን ታሪክ በነዋሪዎቹ ኣማካኝነት ለመላው ዓለም የቸረው ሥርዓተ ኣምልኮኣዊ መንፈሳዊ ባህላዊና ሥነ ሥርዓታዊ ባህል ኣመስግነዋል።

ቅዱስነታቸው በላቲኑ ሥርዓት በዕለቱ በተነበበው ቃለ እግዚአብሔር በማትኰር ባንደኛው ንባብ በሁለተኛው መጽሓፈ ነገሥት የናእማን መዳንና ከሉቃስ ወንጌል የ10 ለምጻሞች መዳንን በማመለከት ሥጋዊ መዳን ለሃይማኖት ክፍት በማድረግ ኣዳኝ ወደ ሆነው የነፍስ መፈወስ እንደሚያደርስ ገልጠዋል።

የሲኖዶሱ ዓላማና ዝግጅት ኣስቀድሞው በቀፕሮስ ባደረጉት ሓዋርያዊ ጉብኝት ለጳጳሳቱ ባስረከቡት መርኃ ግብርና የሥራ ሰነድ እንደተገለጸው በዞኑ በሚገኙት ልዩ ልዩ ጉዳዮች ከግብረ ተል እኮ መታደስ እስከ ያሉ ኅብረተሰባዊና ፖሎቲካዊ ችግሮች ለመወያየትና ሁነኛ መመርያዎች ለማግኘት መሆኑን ከገልጡ በኋላ ሲኖዶሱ እንዲሳካ ጸሎት እንደሚያስፈልግ እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፤ የተከበራችሁ ጓደኞቼ፤ የመሀከለኛው ምሥራቅ ሲኖዶስ ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን ማለት ሲኖዶሱ ለመሃከለኛው ምሥራቅ ሕዝብ ለዛሬና ለወደፊት መልካም ፍሬ እንዲያፈራ በሚያደርገው ጸሎት ኣስተንትኖና በወንድማማነት የተመሠረተ ኣንድነት እንዲሳካ ለዛችው ቅድስት ቦታ ቅዱሳንና ቅዱሳት እንማጠናለን፤ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጥበቃም ኣይለየን፤ ሕዝቡን በልበ ሙሉነት ፤ ሰላም ላንተ ሰላም ለቤትህ ሰላም ለወገኖችህ በማለት ያለኝን መልካም ምኞት እገልጠለሁ፤ በማለት የሲኖዶስ መክፈቻ ስብከታቸውን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.