2010-10-04 16:42:34

የር.ሊ.ጳ ሓዋርያዊ ጉብኝት በሲቺልያ


ቅዱስ ኣባትችን ር.ሊ.ጳ ትናንትና በፓለርሞ የኣንድ ቀን ሓዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመዋል፤ ይህ ሓዋርያዊ ጉብኝት ቅዱስነታቸው በኢጣልያ ካደርግዋቸው 21ኛ ነው፤ ባለፉት ዝግጅቶታችን እንደተገለጸው የጉዞው ምክንያት የዞኑ የቤተሰብና የወጣቶች ስብሰባ ነው፤ ትናንትና ፓለርሞ በደረሱበት ግዜ ብዙ ሕዝብ በደስታ ተቀበልዋቸውል፤ በፎሮ ኢታሊኮ ሜዳ ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ ከመላው ሲቺልያ የተሰበሰቡ ከ200 ሺ በላይ የሚሆኑ ም እመናን ተሳትፈዋል።

ከቀትር በኋላ በካተድራል ከስቺልያ ቤተ ክርስትያን ተወካዮች ተገናኝተዋል፤ እንዲሁም በፓለርሞ ፖሊተኣማ ኣደባባይ ከስቺልያ ወጣቶች ጋር ተገናኝተዋል፡ ማምሻውን በሰላም ወደ መንበራቸው ተመልሰዋል።

ፓለርሞ ቅዱስነታቸውን በታልቅ ደስታ ስተቀበላቸው፤ ካለችው ኋላቀርና ኣስቸጋሪ የማፍያ ፍራቻ ወጥታ የበልጠ የወደፊት ሕይወት እንዲኖራት ተስፋ በማድረግ ነው። ቅዱስነታቸው በኣየሮፕላን በፑንታ ራይሲ ከወረዱ እስከ ፎሮ ኢታሊኮ ሜዳ ከ200 ሺ በላይ የሚሆን ሕዝብ በግራና ቀኝ ተሰልፎ በጭብጨባና በመዝሙር ተቀበልዋቸዋል፤ ፎሮ ኢታሊኮ እንደደረሱ የፓለርሞ ከንቲባ ስኞር ድየጎ ካማራታ የእንኳን ደህና መጡ ንግግር ኣቅርበዋል፤ ከንቲባው የከተማው ችግሮች ብዙ እንደሆኑ ከተማዋ ለመኖር ከሚያስፈልጉ መሠረታውያን ነገሮችና ነጻነት ማጣት እስከ የሕይወት ማጥፋት ችግሮች እንደምትሰቃይ ገልጠዋል፤ ሆኖም ግን ፓለርሞ ገና ትልቅ የእምነት ውርሻ እንዳላት ይህ ሁሉ ችግል ሲያንገላታት በብርታትና በተስፋ እየተጓዘች እስካሁን ለማፍያን ለዓመጽ እጅዋን ኣልሰጠችም፤ ገና እምነትዋ ጽኑ ነው።

ከፓለርሞ ከንቲባ በኋላ የፓለርሞ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ኣቡነ ፓውሎ ሮመዮ የእንኳን ደህና መጡ ንግግር ኣድርገዋል፤ ብፁዕነታቸው በከተማው ካሉ ችግሮች ሥራ ኣጥነት ድኅነት ማፍያ ጠቅሰው በኣስተዳደር በቂ እንዳልተደረገ ብዙ ነገር ተጀምሮ እንደሚቀር ኣገንዝበዋል።

በመጨረሻ በቅዱስነታቸው ጉብኝት ሁሉ እንዲያክትምላቸው ምኞታቸውን በመግለጽ በተለይም የወደፊቱ ትውልድና ሃገር ተስፋ የሆኑ ወጣቶች በዚሁ ጉብኝት ቅዳሴና ጉባኤ ታድሰው ዞኑን ለማደስ ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል።

ቅዱስነታቸው በቅዳሴ ግዜ ባሰሙት ስብከት፤ ‘ከእናንተ ጋር ደስታና ተስፋ ለመካፈል እንዲሁም ከእናንተ ጋር ለመድከም ድርሻየን ለማበርከትና ምኞታችሁና ሃሳባችሁን ለመካፈል እነሆ እናንተው መሃከል እገኛለሁ፤ የልብ ምኞቴ ይህች ከተማ በታሪክዋና ባህልዋ ወደ ኋላ መለስ ብላ መሠረታውያን ዕሴቶችዋን ምርኩስ በማድረግ ለከተማዋ ነዋሪችና ለመላው ሃገር የጸጥታና የሰላም መሣርያ እንድትሆን ነው፤ እንደ በሌሎች የስቺልያ ከተማዎች በፓለርሞ ብዙ ችግሮችና የሚያስጨንቁ ነገሮች እንዳሉ ኣውቃለሁ፤ በተለይ የሚያሳስቡኝ በድህነትና በሥራ ኣጥነት መራራ የዕለት ኑሮ የሚያካሄዱ ናቸው፤ ባለው ዓመጽ ዋስትና በማጣት የሚሰቃዩም ያሳስቡኛል፤’ በማለት በፓለርሞ ስላለው ችግር ኣውስተው የሚከተለውን የተስፋ ቃል ሰጥተዋል፤ ‘ቅርበትየን ለማሳየትና በጸሎት እንደማስባችሁ ለመግለጥ እንዲሁም በዚሁ መሬትና ሕዝብ ታሪክና እምነት ላይ የተመሠረቱ ሰብኣዊና ክርስትያናዊ ዕሴቶች በእውነት ለመመስከር እንዳትፈሩ ለማበረታታት ዛሬ እዚህ መሃከላችሁ እገኛለሁ።’

ኣያይዘውም የዛሬው ቃለ ወንጌል ስለ እምነት እንደሚናገር ሓዋርያት ጌታ እምነት ጨምርልን ሲሉ የክርስትና ሕይወት በተገባ ለመኖር እምነት መሠረታዊ መሆኑን እንደሚገልጡ ኢየሱስም ሓዋርያቱን በእምነት እንዲያድጉ እንዳስተማራቸው እናያለን፤ ሓዋርያት ቊሳዊ ነገሮችን ኣልጠየቁም፤ ሕይወታቸው የሚያበራና የሚመራቸው የእምነት ጸጋ ነው የለመኑት፤ ይህ ጸጋ እግዚአብሔርን ለማወቅና ከእርሱ ጋር ኣንድ ሆኖ ለመኖርና የተቀሩትን የብርታት የፍቅርና የተስፋ ሥጦታዎች እንዲቀበሉ ይረዳል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእምነት ብርታትና ኃይል ሲገልጥ ‘የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር።’ በማለት የማይሆንና የማይቻል የሚመስለን በእምነት እንደሚፈጸም ያስረዳል።’ በማለት እምነት እንዲኖራቸውና ትክክለኛ ሥራ እንዲሰሩ ኣደራ ብለዋል።

መሥዋተ ቅዳሴ ከተፈጸመ በኋላ ቅዱስነታቸው በእኩለ ቀን የመልኣከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት ባድረቡት ኣስተምህሮ ትናንትና በፓርማ ሥርዓተ ብፅዕና የተፈጸመላቸው ብፅዕት ኣና ማርያ ኣዶርን ‘በእስር ቤት በነበሩ ሴቶች መሃከል የእግዚአብሔር ፍቅር ምስክር ሆና የተገኘት’ ሲሉ ኣስታውሰዋል።

በሲቺልያ ያሉትን የእመቤታችን ማርያም መካነ ንግደቶችና ኣባያተ ክርስትያናትን እንደ ሰማይ ከዋክብት ገልጠው ለእመቤታችን ያላቸውን ፍቅር እንዲያጐለብቱት በተግባር የተሰኘ እምነት እንዲኖራቸው ኣደራ በማለት የመል ኣከ እግዚአብሔር ጸሎት ኣሳርገዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.