2010-09-29 17:59:55

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ


“ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፡ ዛሬ በ13ኛው ክፍለ ዘመን የኖረችና፡ ከሀልፍታ ገዳም ትላላቅ ሰዎች ኣንድ ስለሆነችው ስለ ቅድስት ማቲልደ ዘሃከቦርን መናገር እወዳለሁኝ። የገዳምዋ ኣባልና ትልቅ እኅትዋ የነበረች ቅድስት ገርትሩደ በፃፈችው ሊበር ስፐሻሊስ ግራስየ ማለትም የልዩ ፀጋ መፅሓፍ በ4ኛ ክፍል ቅድስት ማቲልደ ከእግዚአብሔር ስለ ተቀበለቻቸው ልዩ ፀጋዎች እንዲህ ስትል ትተርካለች፡ “ከሁሉ በላይ ለራስዋ ሳይሆን ለእኛና ከእኛ በኋላ ለሚከተሉን ትውልድ ይሆን ከእግዚአብሔር የተቀበለቻቸው ብዙ ፀጋዎች ሳንናገር ዝም ማለት ቅኑ ሆኖ ስላልታየን የፃፍነው ሳይፃፍ ከቀረው ቢያንስም፡ ብቻ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሌሎች እንዲጠቅም በማለት እነኚህን እንፅፋለን።” ብላ ኣስፍራለች።

ይህ በቅድስት ገርትሩድና በሌላ የሀልፍታ እኅት የተዘጋጀ ፅሑፍ ልዩ ታሪክ ኣለው። ማቲልደ ገና በ50 ዓመት ዕድሜዋ ብርቱ ኣካላዊ ስቃይ ያለበት ኃይለኛ መንፈሳዊ ቀውስ/ፈተና ኣጋጠማት። በእንዲህ ያለ ሁኔታ እያለች ለሁለት ጓደኞችዋ ደናግል እግዚኣብሔር ከሕፃንነትዋ ጀምሮ ስለሰጣት ልዩ ልዩ ፀጋዎች ኣካፈለቻቸው እነኚህ ደናግል የሰሙትን ይፅፉ እንደነበሩ ግን እርስዋ ኣታውቅም ነበር፡፡ ይህንን ባወቀች ግዜ እጅግ ተበሳጭታና ተረብሻ ነበር። ጌታ ግን የሚፃፈው ለእግዚአብሔር ክብርና ለሌሎች ጥቅም መሆኑን ኣረጋገጠላት። ስለዚህም ይህ መፅሓፍ ስለ ቅድስትዋ ሕይወትና መንፈሳውነት የሚያስፈልገውን መረጃ ለማግኘት ዋና ምንጭ ሆነ፡፡

ከትላልቅ ቤተ ሰብ ሃክቦን ከሚባል የተከበሩ ሃብታሞችና በቱሪንጃ ክፍለ ሃገር ሃያላን ከነበሩ ከገዢው ፈድሪኮ ሁለተኛ ከተዛመዱ መስፍናዊ ቤተ ተወለደች፡ በዘመኑ ገነና ከሆኑ ገዳሞች ኣንዱ በነበረው በሀልፍታ ገዳም ገባች፡ መስፍኑ ለገዳሙ ትልቅዋ እኅትዋ ማለት ገርትሩድ ዘሃከቦርን ሰጥቶ ነበር። እኅት ገርትሩድ በሳላና ለ40 ዓመታት ያህል እንደ እመ ምኔት ያገለገለች ለገዳሙ መንፈሳውነት ቅድምያ በመስጠትም ገዳሙን የብሕትውናና የባህል ማእከል በማድረግ ሳይንሳዊና ንባበ መለኮታዊ ትምህርት በመስጠት ገዳሙ እንዲያብብ ያደረገች ነበር።

ገርትሩድ ለመነኮሳቱ ከፍተኛ የእውቀት ትምህርታቸውን እንዲያዳብሩ በማለት የቅዱሳን መጻሕፍት የሥርዓተ አምልኮ የሃይማኖተ ኣበው ባህል በቅዱስ በርናርዶስ ዘክያራባለና ጉልይልሞ ዘቅድስት ትየሪ ልዩ ትኲረት በመስጠት የሲታውያን መነኮሳት ሕግና መንፈሳውነት እንዲሚያጠኑ ኣደረገች። ቅድስቷ በሥር ነቀል ወንጌላዊ ለውጥና በሓዋርያዊ ቅናት እውነተኛ መምህርና በሁሉም ኣብነታዊት ነበረች፤

ማቲልዴ ከልጅነቷ ጀምሮ በእህቷ የተፈጠረውን መንፈሳዊና ባሕልዊ አኗኗር በመቀበል ኣጣጠመችው፤ በመጨረሻም የገዛ ራስዋ በማድረግ ለሌሎች ኣበረከተችው።

ማቲልዴ 1241ዓ/ም ወይንም በ 1242 ዓ/ም በሄልፍታ ቤተ መንግሥት ተወለደች፤ የመስፍኑ 3ኛ ልጅ ነበረች። የ7 ዓመት ልጅ ሳለች ከወላጅ እናቷ ጋር ታላቅ እኅትዋንገርቱሩድን በሮደርስዶርፍ ገዳም ለማየት ሄደች። በማርካዊው የገዳሙ ኣቀማመጥ ስለተማረከች በልቧ ለወደፊት በዛ ቦታ ለመኖር እጅግ ፈለገች። በቦታው መጀመሪያ እንደ ተማሪ ገባች፤ በ1258 ዓ/ም ላይ በገዳሙ የድንግልና መሃላ ፈጸመች፤ ከዛ ለግዜው ወደ ሄልፍታ የሃክቦርን ርስት ተዛወረች። በዛ ቦታ ከሌሎች የሚለይዋት ባህርያት እንደ በትሕትናዋ: ቸርነት: ፍቅርና ንጽሕናዋ ከአምላክ ከቅድስት ድንግልና ከቅዱሳን ጋር ያላት ግንኙነት ጐልተው ይታዩ ነበር። በከፍተኛ የተፈጥሮና መንፈሳዊ ስጦታዎች ኣሸበረቀች፤ ይህም በሳይንስም ሆነ በተለያዩ የእውቀት ደርጃዎች የዳበረች እንዲሁም ኣስደናቂ ጣዕም በነበረው ድምጽዋ በተለይም ትኖርበት ለነበረው ገዳም በሁሉም መስክ እውነተኛ መዝገብ ናት ብለው ያምኑ ነበር። ትኖርበት በነበረው ገዳም የእግዚአብሄር መሳሪያ ጣት ተብላ ትጠራ ነበር። ገና ወጣት እያለች የገዳሙ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህራን የመዘምራን ዋና ኅላፊና የተመካርያን መምህር በመሆን ጥበብና የማይታክት ቅናት የሚያስፈልጋቸውን ኣገልግሎቶች ለመነኮሳቱ ብቻ ሳይሆን የእርሷ ጥበብና በጎነት ለመጣጣም ለፈለጉ ሁሉ ያለ ድካምና ያለማማረር በትህትና ያገለገለች ነች።

እግዚአብሔር በሰጣት መለኮታዊ የተመስጦ ኣስተንትኖ ማቲልተ ብዙ ጸሎቶች ደረሰች። የታምኝ ዓምደ ሃይማኖትና የዓቢይ ትህትና መምሕር ኣማካሪ ኣጽናኝና በመፈሳዊ ጉዞ መሪ ነበረች፡ በሕይወት ታሪክዋ እንደሚነበበው ‘በገዳም ታይቶ በማይታወቅ ዓይነት የእምነት አንቀጽ ሃይማኖተ ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ ታስተምር ነበር፤ እንደሷ አይነት ለወደፊትም የሚታይ አይመስልም የሚያሰኝ ኣብየት የሚያሰኝ ትልቅ ፍርሃት ኣለን፤ ደናግሎቹ ቃለ እግዚአብሔርን ከእርሷ ለመስማት ባለችበት በመሰባሰብ እንደ ቄስ ሰባኪ ያዳምጡ እንደነበር ይታወሳል። የሁሉም መካሪና መደገፊያ ጥላ የነበረች ሲሆን በተለይም በነበራት ልዩ የእግዚአብሔር ስጦታ የእያንዳንዱን የልቡን ምሥጢር የማወቅ ጸጋ ነበራት። በገዳሙ የነበሩ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰዎች ከገዳሙ ውጭም የሚመጡ ገዳማውያንና ዓለማውያን ከተለያዩ ቦታዎች በመምጣት ያለባቸውን ችግር በዚኅች ቅድስት ኣማካኝነት ለችግራቸው መፍትሄና መጽናናትን ያገኙ ነበር። የተለያዩ የጸሎት ትምህርቶችን እንደፃፈችና እንዳስተማረችም ሲታወቅ መጽሃፎችዋ ቢታተሙ ከመዝሙረ ዳዊት በበዙ ነበር፤ በማለት ይተርካል።

በ1261 በምትኖርበት ገዳም ገርትሩድ የምትባል የ5 ዓመት ሕፃን ሲቀበሉ ሕፃንዋን ማቲልዴ ምንም እንኳ እድሜዋ 20 ዓመት ቢሆንም እንድትከባከባትና እንድትከታተላት ኅላፊነት ተሰጣት። ሕፃናዋን በሷ አርአያና በመንፈሳዊ ሕይወት ኮትኩታ ኣሳደግቻት፤ የሷን ኣብነት ተከትላ ድንግል ብቻ ሳይሆን ምሥጢርዋን የምታካፍላት የልብ ጓደኛዋም ሆነች። በ 1271 ዓ/ም ወይንም በ1272 ዓ/ም ሌላ ማቲልዴ ዘማግዴቡርጎ የምትባል በገዳሙ ገባች። እንዲህ ባለ መንገድ ገዳሙ 4 ታላላቅ ደናግሎች ሁለት ገርትሩድና ሁለት ማልቲደ በማስተናገዱ ይታወቃል። ዘመኑም የጀርመን ገዳማት ወርቃዊ ዘመን ሆነ። ማቲልዴ በገዳሙ ባሰለፈችው የሕይወት ዘመኗ በብዙ በሽታ የተሰቃየች ሲሆን በዚህ ላይ ደግሞ ኅጥአንን ወደ ክርስቶስ እንዲመለሱ ብርቱ ተጋድሎ ታደርግ ነበር፤ በዚህም እስከ ሕይወትዋ ፍጻሜ የክርስቶስን ሕማማት ተካፈለች፤ ፀሎትና ኣስተንትኖ የመኖርዋ ምንጭ ነበሩ፤ የተሰጥዋት ራእዮች ትምህርቶችዋ ለሌሎች ታደርገው የነበረ ኣገልግሎት በእምነትና በፍቅር ያደረገችው ጉዞ መሠረታቸውና ክንዋኔያቸው ከዚህ ነው ያገኙት፤

በሊበር ስፐሻሊስ ግራስየ የመጀመርያ መጽሓፍ ኣዘጋጆቹ በጌታ በዓላትና በቅዱሳን በዓላት በተለይ ደግሞ በቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት ማቲልዴ ያለቻቸውን በመምዝገብ ይጀምራሉ። ማቲልደ ሥርዓተ ኣምልኮን በተለያዩ ክፍሎቹ እንዴት እንደምትኖረው ሲታይ እንዲሁም ዕለታዊ ኑሮዋን ከዚህ እንዴት እንደምታያይዘው ማየት የሚያደንቅ ነው። በሥር ዓተ ኣምልኮ የሚፈጸሙ አንዳንድ ምልክቶች መግለጫዎች እና ሁኔታዎች ልብ ብለን ኣናያቸውም ስሜትም ኣይሰጡንም ሆኖም ማቲልደ ገዳማዊ ሕይወትዋ የመዝምራኑ መምህርና ኃላፊ በምሆንዋ እንዲሁም በኣስተማሪነትና በኲትኰታ የነበራት ልዩ ችሎታ ለእኅቶችዋ ከሥር ዓተ ኣምልኮ ጀምሮ እያንዳንዱዋን የገዳም ሕይወት ኑሮ በሙላት እንዲሚኖርዋት ኣደረገቻቸው።

ማቲልደ ከጸሎታት የዳዊት መድገም ጸሎተ ሰዓታትና መሥዋዕተ ቅዳሴን ልዩ ትኲረት ትሰጥ ነበር በተለይ ግን ቅዱስ ቊርባን መቀብልን እጅግ ትወድ ነበር፤ ቅዱስ ቊርባን በምትቀበልበት ግዜ በተመስጦ እጅግ ጣፋጭና ኣፍቃሪ ከሆነው ልበ ኢየሱስ ጋር ጥልቅ ግኑኝነት በመፍጠር ውሳጣዊ ብርሃን በመጠየቅና ለማኅበርዋና ለእኅቶችዋ በመለመን ከጌታ ጋር ማራኪ ውይይት ታካሄድ ነበር። በእነዚህ መካከል ‘እውነተኛ ቅድስናን የምትፈልግ ከሆነ በልጄ ኣጠገብ ነው ያለው፤ እርሱ ሁሉም የሚቀድስ ራሱ ቅድስና ነው’ በማለት ድንግል ማርያም እያንዳንዳችን በቅድስና ጐደና ወደ ልጅዋ ለመራመድ የምትመራን የክርስቶስ ምሥጢራት ማለትም የጸሎተ መቊጠርያ ምሥጢራት ኣሉ፤ ከእግዚኣብሔር በምናደርገው በእንዲህ ያለ ቅርብ ግኑኝነት ዓለም በሙሉ ቤተ ክርስትያን መልካም ሥራ የሚሰሩ ኃጢኣተኞች ይገኛሉ።

የእርስዋ ራእዮች ትምህርቶችዋ የሕይወትዋ ኣካሄድ ራሱ ሁላቸው በሥር ዓተ ኣምልኮኣዊና ቅድስ መጽሓፋዊ ኣገላለጥ የተመለከቱ ናቸው። በዚህም የዕለት መግቧ የነበረው የቅዱስ መጽሓፍ ጠለቅ ያለ ዕውቀትዋ ይገለጣል። ሁል ግዜ በሥርዓተ ኣምልኮ የሚነበቡ የቅዱስ መጽሓፍ ክፍሎችን ከፍተኛ ትኲረት በመስጠት ቃላቶቹ ምሳሌዎቹና የተለያዩ ምልክቶችን ጠለቅ ባለ መንገድ ታስተነትን ነበር፤ ከመጽሓፍ ቅዱስ የወንጌል ክፍልን ትመርጥ ነበር፤ ገርትሩድ ይህንን ለመግለጥ፤ የወንጌል ቃላት ለእርሷ ኣስደናቂ ምግብ ነበሩ በልብዋም የደስታ ስሜት ይፈጥርላት ነበር በዚሁ የጋለ ስሜት ኣንዳንዴ ንባቡን ኣትጨርሸውም ነበር… እነኚህን ቃላት ስታነብ ሁለመናዋ በእግዚአብሔር ተውጦ ኣንዳንዴ ሳይታወቃት ምልክቶችም ታደርግና በእርሷ መመሰጥ ሊሎችም ይመሰጡ ነበር፤ ኣንዳንዴም ሌሎች ሲጠርዋትም ይሁን ሲነቅንቅዋት ኣትሰማም ነበር፤ በማለት ጽፋለች። ከራእዮቹ ባንዱ እንደተገለጸው የጥቀ ቅዱስ ልቡ ቊስል እያሳየ ወንጌልን በብዛት እንድታስተንትን ኣደራ ያላት ኢየሱስ እንደነበረ ይግልጣል፤ እንዲህም ኣላት ‘ፍቅሬ ምንኛ ያህል ትልቅ መሆኑን እሰቢ በደንብ ለማወቅ የፈለግሽ እንደሆነ ከወንጌል የበለጠ የሚገልጥልሽ የለም፤ እንደዚሁ ኣድርጎ የሚገልጥ ሌላ ምንም የለም፤ በዮሓንስ ወንጌል 15፡9 ኣባቲ እንዳፈቀረኝ እኔም እንደዚሁ ኣፈቀርክዋችሁ፤ ብሎታል።

ውድ ጓደኞቼ፤ የግል ጸሎትና ሥር ዓተ ኣምልኮ በተለይም ጸሎተ ሰዓታትና መሥዋዕተ ቅዳሴ የቅድስት ማቲልደ ዘሃከቦርን የመንፈሳውነት መሠረት ናቸው፡ በመጽሓፍ ቅዱስ እየተመራችና በቅዱስ ቊርባን እየተመገበች እርሷ ሙሉ በሙሉ በቤተ ክርስትያን በመተማመን ከጌታ ጋር በጥልቅ ኣንድነት ትጓዝ ነበር፤ ይህ ኣብነት ለእኛም ከጌታ ያለንን ጓደኝነት እንድናሳድግ ጥሪ ያቀርብልናል፤ በተለይ ደግሞ ዕለታዊ ጸሎታችን በሚገባ በማሳረግና በጥንቃቄና በእምነት በመሥዋዕተ ቅዳሴ መሳተፍ ኣለብን፤ ሥርዓተ ኣምልኮ ትልቅ የመንፈሳውነት ትምህርት ነው።

እናቴ ገርትሩድ የቅድስት ማልቲደ ዘሃከቦርን የመጨረሻ ሕይወት ግዜን በሰፊው ትዘረዝራለች፤ እጅግ ከባድ ግዝያት ነበሩ፤ ሆኖም ግን በቅድስት ሥላሴ በጌታ ኢየሱስ በድንግል ማርያምና በቅዱሳን ሁሉ መኖር በብርሃንቸው እንዲያንጸባርቁ ኣደረግዋቸው፤ ጌታ ወደ እርሱ ሊወስዳት ግዜው በደረሰ ግዜ ቅድስትዋ ለነፍሳት ድሕነት ጥቂት እየተሰቅየች እንድትቆይ ጠየቀችው ኢየሱስም በዚህ የፍቅር ምልክት ደስ ኣለው።

ማቲልድ 58 ዓመት ነበራት፤ የመጨረሻዎቹ ስምንት ዓመታት በትልቅ ሕመምና ሥቃይ ኣሳለፈቻቸው፤ መልካም ተግባርዋና የቅድስናዋ ዜና በሁሉም ተሰማ፤ ገርትሩድ እንደምትተርከው ሰዓትዋ በደረሰ ግዜ ለምታፈቅረው ነፍስ ጣዕምዋ እሱ ብቻ የሆነው ልዑል እግዚአብሔር፤ በኣባቴ የተባረካችሁ እናንተ ኑ መንግሥተ ሰማይን ለመውረስ ኑ ብሎ ጠራት በክብሩም ተቀበላት’ ብላ ጻፈች።

ቅድስት ማቲልድ ዘሃከቦርን ለጥቀ ቅዱስ ልበ ኢየሱስና ለጥቀ ቅዱስ ልበ ድንግል ማርያም አደራ ትሰጠናለች፤ የተከበርሽ ድንግል ሆይ! ከቅድስት ሥላሴ ልብ ባንቺ ላይ በፈሰሰው ጸጋ ሰላም እልሻለሁ፤ በምድርና በሰማይ ከሚገኙ ፍጡራን የተከበርሽና ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የተመረጥሽ ኣሁን በመንግሥተ ሰማያት ለዘለዓለም በምትደሰቺበት ክብር ስላም እልሻለሁ፤ ስትል ለልጅዋ በእናት ልብ ምስጋናና ክብር እንድናቀርብለት እንዲሁም ለማርያም በምትወደው ልጅዋ ልብ ክብር እንድናቀርብላት ጥሪ ታቀርበንናለች። ኣሜን” ካሉ በኋላ በተለያዩ ቋንቋዎች ምስጋና ሲያቀርቡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ይህን ጥሪ ኣቅርበዋል፤ ሓሳቤ በቅርቡ በሰሜን ናይጀርያ ሁለት ሚልዮን የሚሆን ሕዝብ ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው ማጥለቅለቅና ያስከተለው ዓቢይ ሰብኣዊ ቀውስ ላይ ነው፤ የዚህ ቀውስ ሰለባ ለሆኑት በጸሎት እንደማስባቸው በመንፈስ እጐናቸው መሆኔን መግለጥ እወዳለሁ’ ብለዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.