2010-09-21 15:39:04

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ.፦ በጽናት እና በደስታ ሐዋርያዊ ጉዞየን አቀናለሁ


ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ እ.ኤ.አ. ከመስከረም 16 ቀን እስከ መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በታላቅዋ ብሪጣንያ 17ኛው ዓለም አቀፍ ሓዋርያዊ ጉብኝታቸው ለማከናወን በሚጓዙበት አይሮፕላን እንደገቡ ይኸንን RealAudioMP3 ሓዋርያዊ ጉብኝት በቅርብ ከሚከታተሉት 70 ጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ቃለ መጠይቅ ሲመልሱ፦ ወደ ፈረንሳይ ለተመሳሳይ ጉብኝት በተነሱበት ወቅት ፈረንሳይ ጸረ ውሉደ ክህነት ባህል የተስፋፋባት አገር ነች ሲባል፣ በሬፓብሊክ ቸክ ኢሃይማኖታዊነት፣ ጸረ ውሉደ ክህነት ባህል የተስፋፋባት አገር ነች ተብሎ በሚነገርላት አገር ሐዋርያዊ ጉብኝቱ ላይ እንከን ይኖረዋል የተባለውን በማስታወስ፣ ባንጻሩ ግን የሞቀ አቀባበል እንደተደረገላቸው በመግለጥ፣ በታላቅዋ ብሪጣኒያ የሚያከናውኑት ሓዋርያዊ ጉብኝት በተመለከተም ብዙ ቢባልም፣ በርግጥ ከታሪክ እንደምንረዳው ታላቅዋ ብሪጣንያ ጸረ ካቶሊካዊነት ባህል የሚንጸባረቅባት አገር ብትሆንም ቅሉ የመቻቻል፣ ሌላውን የመቀበል ተከባብሮ የመኖር ባህል የተካነች አገር ነች። ስለዚህ ይኽንን የጋራው የመከባበር ባህል በማስቀደም ምንም እንደማያሰጋቸው በመግለጥ፣ በጽናት እና በደስታ ሓዋርያዊ ጉብኝቱን እንደሚያካሂዱ ገልጠዋል።

ቤተ ክርስትያን ማራኪ ለመሆን ብቻ የምትጠመድ ብትሆን ኖሮ መንገድዋን ስታለች ለማለት ይቻላል። ምክንያቱም ቤተ ክርስትያን በአባላት ቁጥር ለማደግ፣ የእራስዋ ሥልጣን ለማጎልበት ስለ እራስዋ የምታገለግል ሳትሆን፣ ሌላውን የምታገለግል፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የምተሰብ ከክርስቶስ ኅላዌ የሚመነጭ እውነት የፍቅር ኃይል እና እርቅ ለሁሉም ይገለጥ ዘንድ ሌላውን የምታገልግል ነች ብለዋል።

አንግሊካውያን እና ካቶሊካውያን እራሳቸውን የሚያገለግሉ ሳይሆን፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሣሪያ እርሱም ቅዱስ ዮሓንስ እንደሚለው የሙሽራው ጓደኞች በመሆን፣ ክርስቶስ የሚያስቀድመውን የሚያስቀድሙ እንጂ፣ እራሳቸውን የማያስቀድሙ እና በጋራ የሚጓዙ ከሆነ፣ ክርስቶስን እና ክርስቶስ የሚያስቀድመው ቅድሚያ የሚሰጡ ሲሆን፣ በመካከላቸው የተፎካካሪነት መንፈስም በምእመናን ብዛት በልጦ ለመገኘት ለሚደረገው ውድድር ሳይቃጡ የክርስቶስን እውነት ለማሳወቅ ባላቸው ተልእኮ ላይ ሲጠመዱ ብቻ ነው ለውህደት የሚደርጉት ጥረት እውነተኛ እና ፍሬያማ የሚሆነው በማለት አብራርተዋል።

በመቀጠል አንዳንድ የውሉደ ክህነት አባላት የፈጸሙት የወሲብ አመጽ ምክንያት ምእመናን በቤተ ክርስትያናቸው ላይ የነበራቸው እምነት ዳግም እንዴት ለመቀዳጀት ይቻላል ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ፣ በርግጥ የተፈጸመው የወሲብ አመጽ በጣም እንደነካቸውና ጥልቅ ሐዘንም እንዳስከተለባቸው ገልጠው፣ አንድ ክርስቶስን በመምሰል የእርሱ ልኡክ እና እንደርሱ እረኛ ለመሆን ሁሉን ለማገልገል የተሟላ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ እነሆኝ ያለ የተጠራ ወደ እውነት የሚመራ የክህነት ማዕርግ የተቀበለ ይኽ ዓይነት አመጽ ሲፈጽም ማየቱ እና መስማቱ ለማመንም ያዳግታል፣ ትልቅ ሓዘንም ነው፣ ካሉ በኋላ ይኸንን ጉዳይ በተመለከተም አንዳንድ የቤተ ርክስትያን የበላይ አክላት የዚህ ዓይነት አመጽ በመቆጣጠር ኃላፊነት ላይ የዘነጉ ሆነው መገኘታቸውንም ሳይደብቁ፣ ወቅቱ የንስሃ የትህትና የቅን እና እውነተኛ ተሃድሶ ጊዜ ነው ብለዋል።

የአመጽ ሰለባ የሆኑትን ከደረሰባቸው ሰብአዊ ስነ አእምሮአዊ ጭንቀት በማላቀቅ ዳግም በክርስቶስ መልእክት ላይ እምነታቸውን ያኖሩ ዘንድ፣ በቅድሚያ የቁሳዊ የስነ ኣእምሮአዊ እና የመንፈሳዊ ድጋፍ ማቅረብ ወሳኝ ነው። የወሲብ አመጽ የፈጸሙት ሰዎች፣ በዚህ ዓይነቱ የጾታዊ ስሜት ግፊት የሚመሩ ናቸው፣ ችግሩ የስሜት ብቻ ሳይታጠር በሽታም ጭምር ነው፣ ስለዚህ ወጣቶች ለማነጽ በሚደረገው የአገልግሎት ተልእኮ እነዚህ ይህ ዓይነት በሽታ ያለባቸው ሰዎች እንዳይሳተፉ በማድረግ ካደረባቸው በሽታ እንዲፈወሱ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ካብራሩ በኋላ፣ የክህነት የገዳማዊ ሕይወት ጥሪ ያላቸውን በሚገባ ቀርቦ ማወቅ፣ ማነጽ በጥንቃቄ መመልመል ያስፈልጋል ብለዋል።

በመጨረሻም፣ ብፁዕ ካርዲናል ኔውማን አንግሊካውያን እና ካቶሊካውያንን የሚያገናኙ ድልድይ ወቅታዊነት የተላበሱ መሆናቸው በማብራራት፣ የሳቸው እምነት የሕግ እና የቀመር ሳይሆን ሥልጡን በግል ከጠበቀ መኖር የመነጨ፣ ስቃይ ያልተለየው ዕለት በዕለት ከመለወጥ በሚገኘው ኃይል የተመራ ነበር ብለው፣ አያይዘውም ታላቅዋ ብሪጣኒያ እና ቅድስት መንበር በጋራ በዓለማችን የሚታየው ድኽነት የተለያዩ በሽታዎች የአንደንዛዥ እጽ የመሳሰሉት ሰብኣዊ ማኅበራዊ ችግሮች መስፋፋት፣ በመቅረፍ ሰላም ፍትህ የጋራ ውይይት የመቀባበል እና መከባበር የተሰኙትን ለሰብአዊነት መሠረት የሆኑትን እሴቶች በጋራ ለማነቃቃት በመተባበር እንደሚሰሩ ጠቀሰው፣ ሰውን ሰብአዊነት ማልበስ አንዱ የእምነት ዓላማ ነው። ይኽ ደግሞ በተለያዩ ምክንያት የወደመው በሰው ገጽ ላይ ታትሞ ያለው የእግዚአብሔር አምሳያ ዳግም ማጎናጸፍ ማለት መሆኑ በማብራርተው የሰጡትን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.