2010-08-26 10:48:46

የር.ሊ.ጳ የዕለተ ሮቡዕ ሳምንታዊ ኣጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ (25.08.2010)


ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ዛሬ ረፋድ ለዕረፍት ከሚገኙት ካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያዊ ኣደራሽ በቦታው ለሚገኙ ምእመናንና ነጋድያን የተለመደውን ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምረዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ሳምንታ መጨረሻ ቅዳሜ ላይ ዝክረ በዓሉ ለሚታወሰው ቅዱስ ኣጎጢኖስ የተመለክተ ትምህርት ሰጥተው በመጨረሻም ትናንትና በሶማልያ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሓዘን ገልጠው ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ ኣቅርበዋል። ኣስተምህሮውም ይህ ነው፤ “ውድ ውንድሞቼና እኅቶቼ፤ በእያንዳንዳችን የኑሮ ሕይወት ውስጥ ለእኛ ውድ የሆኑ ሰዎች ለየት ባለ መንገድ ቅርብ ሆነው የሚሰሙን ኣሉ፤ ከእነዚህ ኣንዳንዶቹ የዚህን ዓለም ሕይወት ፈጽመር በእግዚአብሔር እቅፍ ይገኛሉ፤ የቀሩትም ገና ከእኛ ጋር የዚህ ዓለም ኑሮ ጉዞ እየፈጸሙ ናቸው። እነኚህ ልዩ ሰዎች ወላጆቻችን ኣሳዳጊዎቻችን ኣስተማሪዋቻችን ናቸው፤ ከእነዚህ ሰዎች ብዙ መልካም ነገሮችን ኣግኝተናል፤ እኛም መልካም ነገሮች ሰጥተናቸዋል፤ እነኚህ ሰዎች በእርሳቸው መመካት የምንችል ሰዎች ናቸው። በዚህ ምድር በምናደርገው ጉዞ የሕይወት ጓደኞችም ያስፈልጉናል፤ ለምሳሌ ያህል ለመንፍፈሳዊ ጉዞኣችን አበ ነፍስ የሚያናዝዝ ካህን ጠቅለል ባለ መንገድ በዕለታዊ ኑሮኣችን ስለሚያጋጥሙን ልዩ ልዩ ነገሮች ልብ ለልብ በመወያየት ሁሉን ምሥጢራችን ከእሳቸው ጋር የምንካፈል ሰዎች ናቸው። ለመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞና ዕድገት እንዲህ ዓይነት ሰዎች እጅግ ኣስፈላጊ ናቸው። በዚህ ኣጋጣሚ እመቤታችን ድንግል ማርያንና ቅዱሳንን ማስታወስ እወዳለሁ፤ እያንዳንዳችን የሚጠጋበት ቅዱስ ኣለው ብየም ኣምናለሁ። ይህንን ቅዱስ በጸሎትና ኣማላጅነት እንቀርበዋለን። እንዲሁም ቅዱሱን ለመምሰል እንደኣርኣያ ልንከተለው ይረዳናል።

የመጠርያ ስማችሁ ከሆነው ቅዱስ ወይም ስማችሁ ከሚጠጋው ቅዱስ በመጀመር የብዙ ቅዱሳን ታሪክና ሕይወት እንድታውቁ ኣደራ እላለሁ። የሕይወት ታሪካቸው እንዲሁም የጻፉትን በማንበብ እንድታውቁዋችው ይሁን። ጌታን በበለጠ ለማፍቀርና ለሰብኣዊና ክርስትያናዊ እድገታችሁ መሪ እንደሚሆንዋችሁ እርግጠኛ ነኝ።

እንደምታውቁት እኔም መሪ ከሆኑ ኣንዳንድ ቅዱሳን የሚያገናኝ ኣለኝ፤ ከነዚሁ ቅዱሳን ለመጥቀስ ያህል ቅዱስ ዮሴፍ መጠርያ ስሜ፡ ለጵጵስና ስሜ የመረጥሁት ቅዱስ በነዲክቶስ፡ እንዲሁም ከሌሎቹ ቅዱሳን በትምህርት ጥናትና በጸሎት እጅግ ያወቅሁት ቅዱስ ኣጎስጢኖስ በሕይወት ጉዞየና በተለእኮየ መልካም ጓደኛ በመሆን የሸኘኝ ቅዱስ ነው።

የዚሁ ቅዱስ ሰብኣዊና ክርስትያናዊ የሕይወት ገጠመኝ እንደገና ለመጥቀስ እወዳለሁ፤ ልክ በዘመኑ እንደነበረው፡ ኣሁንም እውነት ተዛማጅ ነው፡ የሚለው የረላቲቪዝም ኣደገኛ ኣስተሳሰብ ዓለማችንን ከእውነት እያራቀ ነው፤ ቅዱስ ኣጎስጢኖስ በኣስመሳይነት ያልኖረ እውነተኛ ሰው ነበር፤ ለእውነት የነበረው የማይረካ ጥማትና ኣሰሳ ከባህርያቱ የጎላ ነበር፡ ዘላቂ ሰላም ለልብ የማይሰጠው ግዝያዊና ኣስመሳይ እውነት ኣልፎ እውነተኛውንና ዘላቂ ሰላምና ደስታ ለልብ እንዲሁም ለሕይወቱ ኑሮ ትርጉም የሚሰጠውን እውነት ሲፈልግ ከርመዋል።

እንደምናውቀው የቅዱስ ኣጎስጢኖስ የሕይወት ጉዞ ቀላል ኣልነበረም፤ እውነትን በክብረት በትልቅ ሥራ እንዲሁም ግዝያዊ ደስታ በሚሰጡት ብዙ ነገሮችን በማከማቸት ውስጥ ለማግኘት ሞክሮዋል፤ ብዙ ስሕተት ፈጽመዋል፤ ኣዝነዋል፤ ብዙ ሽንፈት ኣጋጠመው፤ ሆኖም ግን በዚህ በቃኝ ብሎ ተስፋ በመቊረጥ ኣልቆመም፤ ግዝያዊ እፎይታ በሚሰጠው የብርሃን ነጸብራቅ ኣልተደናገረም፤ ወደ ልቡ ተመልሶ በገዛ ራሱ ውስጥ በጥልቀት ለመመርመር ቻለ፤ ኑዛዜ በሚለው መጽሓፉ እንደሚገልጠውም ያ ይፈልገው የነበረ እውነት፤ ፍጹም እውነት እግዚአብሔር ራሱ ሆኖ ከገዛ ራሱ ለእርሱ ቅርብ ሆኖ ኣገኘው፤ ዘወትር ከእርሱ ጋር መኖሩንም ኣረጋገጠ፤ በምንም ተኣምር እንዳልተወውም ተገለጠለት፤ ላንዴና ለመጨረሻ ሕይወቱን እንዲለውጥለት ሲጠብቀው መኖሩንም በራለት።

በጽሑፉ እንደገለጸው እመጨረሻ ላይ እውነትን ያገኘ እርሱ ሳይሆን ለካ ፍጹም እውነት የሆነ እግዚአብሔር ይፈልገውና ይከታተለው ኖሮ ኣገኘውና ላንዴና ለመጨረሻ ሕይወቱን ለወጠለት፤

ሮማኖ ጓርዲኒ የሚባሉ ጸሓፊ ቅዱስ ኣጎስጢኖስ በጻፈው መጽሓፈ ኑዛኣኤ ሶስተኛ ም ዕራፍ ላይ ባቀረበው ሓተታ፤ ‘ቅዱስ ኣጎስጢኖስ፡ እግዚአብሔር የሚያንበረክክ ሰማያዊ ክብር፤ ጥማትን የሚቆርጥ መጠጥ፤ የሚያስደስት ክቡር ዕንቊ መሆኑንና በመጨረሻ ለተረዳው ሰላም የሚሰጥ እርግጠኝነት መሆኑን ተረዳ፤ እንዲሆም ሁሉም የሚያውቅ ፍቅር ብፅዕና መሆኑን ከተረዳ በኋላ፤ ይህ ሁሉ እርሱ ነው፤ እርሱም ይበቃኛል ብሎ ኣረፍ ኣለ።’ ሲል ጽፈዋል። በመጽሓፈ ኑዛዜ ዘጠነኛ ቁጥር ላይ ከእናቱ ከቅድት ሞኒካ ጋር ያደረገው ውይይትን ዘግቦኣል። እርሱና እናቱ በኦስትያ በሚባል የሮማ ከተማ ክፍል በእንግዶች መቀበያ ሆነው በመስኮት ባህርንና ሰማይ እየተመለከቱ፡ ከባሕሩና ከሰማዩ እጅግ ሰፍቶና ከፍ ብሎ መጥቆ የሚሄድ ውይይት ሲያካሂዱ ቆይቶው የፍጥረት ሁሉ ጸጥታ በሰፈነበት ኣፍታ የእግዚአብሔርን ልብ ይነካሉ። እዚህ ላይ ለቅዱስ ኣጎስጢኖስ መሠረታዊ የእውነት ፍለጋ ሂደት ተገለጠለት፤ እግዚአብሔር ለመናገር ፍጥረት ሁሉ ጸጥ ማለት ኣለበት፤ ይህ ዛሬም በግዝያችን ሳይቀር ዘወትር እውነት ነው። ኣንዳንዴ ጸጥታ ሲሰፍን ያስፈራል፤ ስለገዛ ራሳችን ሁኔታና ተግባር ማስተንተን ያስፈራል፤ ከዚህ ይልቅ ግዝያዊ ደስታና እፎይታ በማግኘት መኖር ይመረጣል በማለት ለመሸሽ እንሞክራለን፤ ለይስሙላ ከኣንገት በላይ የሆነ ሕይወት ይመረጣል ምክንያቱም የእውነት ፍለጋ ብርቱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም እውነት እንዳታገኘንና እንደ ቅዱስ ኣጎስጢኖስ ላንዴና ለመጨረሻ እንዳትለውጠንም ያስፈራል።

ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ በእምነት ጉዞ ላሉ፡ በችግር ላይ ላሉትም ይሁን፡ በቤተ ክርስትያን ሕይወት ውስጥ በሙላት ለማይሳተፉም፡ እንዲሁም እግዚአብሔር እንዴሌለ በማሰብ ለሚኖሩትም ሳይቀር ለሁላችሁም ለማለት የምፈልገው ነገር ይህ ነው። እውነትን ኣትፍሩ፤ ወደ እውነት የምታደርጉትን ጉዞ በምንም ተኣምር እንዳታቋርጡ፤ በዓይነ ልቦናችሁ ጥልቅ እውነትን በገዛ ራሳችሁ ውስጥና በኣከባቢያችሁ በሚገኙ ነገሮች ከመፈለግ እንዳትቦዝኑ ኣደራ እላለሁ። እግዚአብሔር እውነትን እንድታዩ ብርሃን ከመስጠት ኣይቆጠብም እንዲሁም እንደሚያፈቅረንና ልናፈቅረው እንድሚፈልግ በልባችን ሆኖ የሚያሞቅ ጸጋው ከመስጠት ዝም ኣይልም። በዚሁ ጉዞ የእመቤታችን ድንግል ማርያም የቅዱስ ኣጎስጢኖስና የቅድስት ሞኒካ ኣማላጅነት ይሸኙን።’ በማለት መልካም ምኞታቸው ገልጠው፤ ምእመናኑንና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመጡ ነጋድያን በተለያዩ ቋንቋዎች አጠር ያለ ትምህርት ከሰጡ በኋላ ትናንትና በሶማላያ ላይ ስለተፈጸመው የግድያ ተግባር የተሰማቸውን ጥልቅ ሓዘን ገልጠው ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ ኣቅርበው ነጋድያኑንና ምእመናኑን ባርከዋል፤ ከትምህርቱ በኋላም በቦታ ጥበት ምክንያት በካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያዊ ኣዳራሽ ውስጥ ለመግባት ያልቻሉትንም ወደ ከተማዋ ኣደባባይ ብቅ በማለት ሰላምታና ሓዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.