2010-08-20 14:11:41

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርሲቲያን የሀገረስብከት የጠቅላይ ፀሐፊዎች የተሞክሮ ልምድ ልውውጥ ጉብኝትና ስብ


ዲስ አበባ, ነሐሴ 15 ቀን 2002 ዓ.ም (አዲስ አበባ)- በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርሲቲያን የሀገረስብከት የጠቅላይ ፀሐፊዎች የተሞክሮ ልምድ ልውውጥ ጉብኝትና ስብሰባ ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2002 ዓ.ም በሐረር ሀገረስብከት ተካሄደ፡፡

የተሞክሮ ልምድ ልውውጥ ጉብኝቱ የተጀመረው በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አሰበ ተፈሪ ከተማ ጠቅላይ ፀሐፊዎቹ ሐምሌ 29 ቀን 2002 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ከደረሱበት ጀምሮ ሲሆን ጉብኝቱንና ስብሰባውን አባ ሐጎስ ሐይሽ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማህበራዊና ልማት ኮሚሽንና ጠቅላይ ፀሓፊ፣ ዶ/ር ዳንኤል ከፍታሳ የማህበራዊና ልማት ኮሚሽኑ አስፈፃሚ ዳይሬክተርና ስምንት የሀገረስብከት ጠቅላይ ፀሐፊዎች ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡

ጠቅላይ ፀሐፊዎቹ አሰበ ተፈሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቁምስና ሲደርሱ የቁምስናው የሰበካ ካህናትና የካፑቺን ወንድሞች ከሐረር ሀገረስብከት ማኅበራዊና ልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሠራተኞች ጋር በመሆን አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን አዲሱን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሕንፃና በቁምስናው ቅጥር ግቢ ስለሚካሄዱት ሐዋሪያዊና ልማት ሥራዎች በአባ ተክለብርሃን የማታዬ የሀገረስብከቱ መሪ ካህንና የጳጳሱ ረዳት ገለፃ ተደርጎላቸዋል ፡፡ በመቀጠልም ለጠቅላይ ፀሐፊዎቹ በቅዱስ ጊዮርጊስ ዘርዓ ክህነት መኖርያ ቤት የእራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡

ሐምሌ 30 ቀን 2002 ዓ.ም የስርዓተ ቅዳሴ ከተከናወነ በኋላ ተቅላይ ፀሐፊዎቹ በአሰበ ተፈሪ የፍራንሲስከን እህቶች መኖርያ ቤትንና የፀሎት ቤት ከጎበኙ በኋላ የቅድስት ማርያም አፀደ ህፃናትና 1ኛ ደረጃ ት/ቤት አስጎብኝቶ እንዲሁም የቅድስት ማርያም ክሊኒክን አገልግሎት አሰጣጥና አዲስ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ ያለውን የኪሊኒኩን የማስፋፊያ ህንፃ በሲ/ር እታለማሁ ከበደ መሪነት ጎብኝተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአሰበ ተፈሪ የካፑቺን ወንድሞች መኖሪያ ቤትና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የቀድሞ ህንፃ በአባ ማቴዎስ አሥራ መሪነት ጎብኝተዋል፡፡

በአሰበ ተፈሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢና ዙሪያውን ያሉት የቤተክርስቲያኗ ሐዋሪያዊና የልማት ሥራዎች ጉብኝት እንደተጠናቀቀ በአቶ በቀለ ሞገስ የሐረር ሀገረስብከት ማህበራዊና ልማት ጽ/ቤት ረዳት አስተባባሪና የፕሮግራም ዳይተሬክተር በሆኑት በአቶ ዘመዴ አበበ መሪነት ከአሰበ ተፈሪ ወጣ ብሎ የሚገኘውና ከ200 በላይ አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ ያደረገውንና ግንባታ ከስድሰት ዓመታት በበፊት ተጠናቆ ህብተተሰቡ በባለቤትነት የሚያስተዳድረውን የመጢቾ የተቀናጀ የውሃ ግንባታ ጎብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ጸሐፊዎቹ ጉዟቸውን ወደ ድሬዳዋ ከመጀመራቸው በፊት በጽ/ቤቱ የማህበራዊ ደህንነት ክፍል ተግባራዊ የተደረገ ያለውንና ሁለት መቶ ሃምሳ ህጻናትን ተጠቃሚ እያደረገ ያለውን በአሰበ ተፈሪ ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ህጻናት መከላከያና መቋቋሚያ ፕሮጀክት ማዕከል ከጎበኙ በኋላ ከአሰበ ተፈሪ ከተማ ወጣ ብሎ ወደ ድሬዳዋ በሚስደው መንገድ አካባቢ የሚገኙ የቂሊሶ ገ/ማኅበር በብድርና ቁጠባ ተደራጅተው በጽ/ቤ ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉ ሴት አርሶ አደሮችን የስራ የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡

የምዕራብ ሐረርጌ ክልል አቋርጠው ምስራቅ ሐረርጌ ዞን እንደደረሱ በጎሮጉቱ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የወርጂ ጃለላ ተፋሰስ የተቀናጀ ተፈጥሮ ሐብት ልማትና እንክብካቤ በአቶ በቀለ ሞገስና በአቶ ዘመዴ አበበ አማካኝነት ጎብኝተው በተፋሰሱ ላይ እየታየ ስላለው አዎንታዊ ለውጥ ገለፃና ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል፡፡

በመቀጠልም ከካራሚሌ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያንና በስሩ የሚገኘውን 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የጎበኙ ሲሆን ቁምስናው እየሰጠ ስላለው አገልግሎት በቁምስናው ካህን በአባ ሐብተወልድ መሸሻ ገለፃ ተደርጎላቸው ጉዟቸውን ወደ ድሬዳዋ ቀጠሉ፡፡

ጠቅላይ ፀሐፊዎቹ ድሬዳዋ እንደደረሱ በዕለቱ ከአዲስ አበባ በአየር ተጉዘው እዚያ ይገኙ የነበሩት አባ ሐጎስ ሃይሽ ከድሬዳዋ ቅዱስ አውጎስጢኖስ ቁምስና ካህናትና ከሐረር ሀገረስብከት ማኅበራዊና ልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ የተዘጋጀ የእራት ግብዣ የተደረገላቸው ሲሆን በእራ ግብዣው ላይ አቶ በቀለ ሞገስ ጽ/ቤቱን በመወከል የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡

ነሐሴ 1ቀን 2002 ዓ.ም ጠቅላይ ፀሀፊዎቹ ከአባ ሐጎስ ሃይሽ ጋር በመሆን በድሬዳዋ አስተዳደር የመንግሥት አጋር በመሆን እያበረከተች ያለው አስተዋፅዖ በአስተዳደሩ አብይ ግምት የተቸረው መሆኑንና በዚህ ረገድ ቤተክርስቲያኗ ለምታደርገው ጥረት የመንግስት ድጋፍ እንደማይለያት ተገልፆላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ፀሐፊዎቹ በዕለቱ ቀጣይ ተግባራቸው ያደረጉት ከልምድ ልውውጥ ጋር ተያይዞ በስድስት ወሩ በመካከላቸው የሚካሄደውን ውየረየረት ሲሆን ውይይቱ አቡነ ወልደትንሳኤ ገብረጊዮርጊስ ሀረር ሀገረስብከት ጳጳስ በፀሎት ከከፈቱ በኋላ ስብሰባውን የመሩት አባ ሐጎስ ሃይሽ ናቸው፡፡ የስብሰባው አጀንዳዎች ዶ/ር ዳንኤል ከፍታሳ ለተሰብሳቢዎቹ አስተዋውቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ አቶ በቀለ ሞገስ የሐረር ሀገረስብከት ልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤትን አስመልቶ እ.አ.አ ሚያዝያ 1 ቀን 1987 ዓ.ም መቋቋሙን ጠቅሰው በሃያ ሶስት ዓመት ቆይታው በርካታ የድንገተኛ ችግር ሰለባዎችን በመልሶ ማቋቋምና በዘላቂ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንና በአሁኑ ጊዜ ለድንገተኛ ችግሮች የሚወሰደው እርምጃ ከመልሶ ማቋቋም ጋር በማቀናጀት ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ በመቀጠልም አቶ ዘመዴ አበበ በጽ/ቤቱ እየተከናወኑ ያሉትን ስራዎች በዝርዝር ለተሰብሰቢዎቹ ገለፃ አድርገዋል፡፡

አቡነ ወልደትንሳኤ ገ/ጊርጊስ በእስካሁኑ ድረስ በሀገረስብከቱ የተከናወኑት የማኅበራዊና የልማት ስራዎች በርካታ ችግረኛ ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረጉ በመሆናቸው የሐዋርያዊ ተልዕኳችን ውጤቶችም ጭምር መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ቤተክርስቲያኗ በሀገረስብከቱ ውስጥ ከሚገኙ የሌሎች እምነት ተከታዮችና ተቋማት ጋር ተቻችሎ ከሞኖርና ተባብሮ ከመስራት ጋር ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡

ጠቅላይ ፀሐፊዎቹ ሌላው ትኩረት ሰጥተው የተወያዩበት ጉዳይ የአየር ንብረት ለውጥ በሐገራችንና በዓለም ላይ እያስከተለ ስላለው ቀውስና ችግሩን በመከላከል ሂደት ቤተክርስቲያኗ አፅንዖት ሰጥታ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን ነው፡፡ ዶ/ር ዳንኤል በቅርቡ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ይህንኑ አስመልክቶ አውደ ጥናት መካሄዱንና ወጣቶችን ጨምሮ ተለያዩ የቤተክርስቲያኗ አባላት መሳተፋቸውን ጠቅሰው በዚህ ረገድ የቤተክርስቲያኗ ጥሩ ገፅታ በብዙሃን መገናኛ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗ የአየር ንብረት ለውጥን እያስከተለ ያለውን ቀውስ ለመከላከል በቀጣይነት ለምትወስዳቸው እርምጃዎች ግልፅ የሆነ የጋራ የማስፈፀሚያ ስልት ሊኖራት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ፀሐፊዎቹ በሀገር አቀፉ ጽ/ቤትና በሀገረስብከቶች ደረጃ አሉ በተባሉ የፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በማስፈፀም ሂደት ስላጋጠሙ ችግሮች ተወያይተዋል ፡፡ዶ/ር ዳንኤል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ጽ/ቤት በኩል ከለጋሽ ድረጅቶች ለሀገረስብከቶች የሚሰጡ ድጋፎች ከአንዳንድ ሀገረስብከቶች ወቅቱን ጠብቆ ሪፖርት ስለማይቀርብ ችግሮች እተከሰቱ መሆኑን ገልጸው ድጋፉን ቀጣይ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረትም አደጋ ላይ እንደጣለው አስታውሰዋል፡፡

ለችግሩ መከሰት ፕሮጀክቶቹ ሲነደፉ አሳታፊ ባለመሆናቸው በሚፈጠር የመረጃ ክፍተትና ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጽ/ቤት በኩልም ተከታታይ ክትትልና ግምገማ ስለማይደረግ ስለሆነ በሁሉም በኩል ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተገልጿል፡፡

ቀጣይ እቅዶችን አስመልክቶ ጠቅላይ ፀሐፊዎቹ መድረኩ ከየሀገረስብከቶቹ በከፍተኛ ሀላፊነት ደረጃ ላይ ያሉና በቂ ልምድም ያላቸው ተወካዮች የተወከሉበት ስለሆነ የተሻለ ተግባር መፈፀም እንዲችል የተግባር መመሪያ ሊዘጋጅለት ይገባል በሚለው ሃሳብ ላይ የጋራ ስምምነት አድርገዋል፡፡ በዚህ ረገድ መድረኩ ለማህበራዊና ልማት ሥራዎች የሰጠውን ትኩረት ለሐዋርያዊ ተግባሮቻችንም ተመሳሳይ ትኩረት መስጠት አለብን ብለዋል፡፡

የተግባር መመሪያውን ዶ/ር ዳንኤል ከፍታሳና አቶ ዘመዴ አበበ ረቂቅ ነድፈው የሚቀጥለው ስብሰባ ከመድረሱ ቀደም ብለው እንዲያቀርቡ የተወሰነ ሲሆን ቀጣዩን ስብሰባ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት እንዲያስተናግድ ተወስኖ ለስብሰባው አጀንዳዎች ሁሉም ሀገረስብከቶች ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም አባ ሀጎስ ሃይሽ ስብሰባው የተሳካ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡ አቶ በቀለ ሞገስ በበኩላቸው ለተሳታፊዎች ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ወደየቤታቸው በሰላም እንዲመለሱ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት

ማህበራዊና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ








All the contents on this site are copyrighted ©.