2010-08-18 17:49:21

የር.ሊ.ጳ የዕለተ ሮቡዕ ሳምንታዊ ኣጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ (18.08.2010)


ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ዛሬ ረፋድ ለዕረፍት ከሚገኙት ካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያዊ ኣደራሽ በቦታው ለሚገኙ ምእመናንና ነጋድያን የተለመደውን ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምረዋል። ትምህርቱም ይህ ነው፤ “ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፤ ዛሬ እፊታችን ቅዳሜ በዓልቸውን ስለሚታወሰው ቀድመው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩ ስለ ቅዱስ ፕዮ 10ኛ ለዘመናችን እረኞችና ምእመናን ጠቃሚ የሆኑ ኣንዳንድ ነገሮችን በማውሳት መናገር እወዳለሁ፤ የዚሁ ቅዱስ ስም ጁሰፐ ሳርቶ ነበር፤ ርየዘ በተባለ የትረቪዞ ኣውራጃ በ1835 ዓ.ም. ተወለዱ። ቤተሰባቸውም በግብርና ስራ ይተዳደሩ ነበር። ትምህርታቸውን በፓዶቫ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ በ23 ዓመት ዕድሜያቸው ክህነት ተቀብለዋል። በመጀመሪያ በቶንቦሎ ከተማ ቤተ ክርስቲያን ምክትል ቆሞስሪ በመሆንና ቀጥለውም በሳልዛኖ ቤተ ክርስቲያን ቆሞስ ሆነው አገልግለዋል። ከዚህ ኣገልግሎት በኋላ የትሬቪዞ ካቴድራል ሊቀ ካህን በመሆን እያገልገሉ የጳጳሱ ዋና ፀኅፊና የሰበካው ዓቢይ ዘርአ ክህነት አበ ነፍስ በመሆን አገልግለዋል። በእነዚሁ ዓመታት ብዙ የግብረ ተልእኮ ተመኲሮ የቀሰሙ የወደፊት የመንበረ ጴጥሮስ ጳጳስ ለክርስቶስና ለቤተክርስቲያን ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ኣሳይተዋል፤ በተለይም ደግሞ ለተጎዱ ወገኖች በመርዳትና ትሕትናን በማሳየት ዋነኛ ጠባያቸውን ኣሳይተዋል። በ 1884 የማንቶቫ ከተማ ጳጳስ ሆነው ሲሾሙ በ 1893 ደግሞ የቬኔሲያ ከተማ ፓትሪያርክ በመባል ተሹመዋል። በነሐሴ 4 ቀን 1903 ር እሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ተመርጠዋል፤ ለመዓርጉ ብቁ ኣይደለሁም በማለት ቢጠራጠሩም በትሕትና ጵጵስናውን መቀበላቸው ይታወሳል።

የቅዱስ ፒዮስ 10ኛ የጵጵስና ዘመን፤ በቤተክርስቲያን ታሪክ የማይደመሰስ ምልክት ፈጥሮኣል፤ መንፈሳዊ የመታደስ ትግል ኣድርጎኣል፤ ባጭሩ ሁሉንም በክርስቶስ መታደስ በሚል መሪ ቃል ይገለጣል። ይህ ተግባር ሁሉንም የቤተ ክርስትያን መስኮችን ነክተዋል። ከሁሉ ኣስቀድመው በኩርያ ሮማና የሚታወቀው የቅድስት መንበር ተቅዋሞችን እንደገና በኣዲስ መልክ ኣዋቀሩት፤ ከዚህ በመቀጠል በተከታያቸው በነዲክቶስ 15 የታወጀውን የቤተክርስቲያን ሕግ ቀኖና እድሳትና የጥናት ሥራ ጀመሩ። ሌላው ዋነኛ ጉዳይ የወደ ፊት ካህናት ምንጭ የሆነው የዘር አ ክህነት ጉዳይ ስለነበር በዘር አ ክህነት የሚሰጠው ትምህርት በአጠቃላይ እንደገና እንዲጠናና እንዲሻሻል እንዲሁም በተለያዩ ኣውራጃዎች በደንብ የተዘጋጁ መምህራንና በቂ መጻሕፍት ያላቸው መዝገበ መጻሕፍት ያላቸው የክልል ዘርአ ክህነቶች እንደሚከፈቱ ኣድርገዋል። ሌላው ኣስፈላጊ ክፍል ደግሞ ም እመናንን ትምህርተ ክርስቶስ በሚገባ ማስተማር ነበር። ገና በወጣትነት ዕድምያቸው ክህነት ተቀበለው ቆምስ ሳሉ የትምህርተ ክርስቶስ ማስተማርያ ኣዘጋጁ፤ በማንቶቫም ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ ሳሉ ይህንን የትምህርተ ክርስቶስ ማስተማርያ ለመላው ዓለም ባይሆንም ቢያንስ ቢያንስ በጣልያንኛ ለሁሉም ሊሆን የሚችል ኣንድ የትምህርተ ክርስቶስ መጽሓፍ እንዲሆን ብርቱ ጥረት ኣካሂደዋል።

እውነተኛ እረኛ እንደመሆናቸው መጠን በዚያው ዓመታት የአገሪቷ ዜጎች በስደት ላይ ይኖሩና ይንቀሳቀሱ ስለነበር ሁኔታውን አስቀድሞ በመረዳት የትምህርተ ክርስቶስ መፅሃፍ በማዘጋጀት ማንኛውም አማኝ በሚገኝበት ቦታና በሚያጋጥመው የኑሮ ችግር መመርኮዝ የሚችልበት ኣጋጣሚ ፈጥረዋል። ር እሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው በተሾሙም ግዜ ለሮማ ሃገረ ስብከት የሚያገለግል የትምህርተ ክርስቶስ መጽሓፍ ኣዘጋጅተዋል፤ ቆይቶ መጽሓፉ በመላው ጣልያንና ዓለም ተሰራጭተዋል። ይህ የፕዮስ 10ኛ ትምህርተ ክርስቶስ በማለት ተጠራ መፅሃፍ ቀለል ባለ ቋንቋ የዕምነት እውነትን ለመረዳት የሚገልግል ጥርት ያለና ትክክለኛ በሆነ መንገድ በቅረቡ ለብዙዎች መሪ ሆነዋል።

ምእመናን ጠለቅ ወዳለ የጸሎት ሕይወትና ምሥጢራትንም ሙላት ባለው መንገድ እንዲሳተፉ ለመርዳት የሥርዓተ ኣምልኮ በተለይ ደግሞ የዜማ መታደስ ልዩ ትኲረት የተሰጠው ሌላ ክፍል ነው። በ1903 ዓም በጵጵስና መጀመርያ ዓመታቸው ላይ የሰጡት ትራ ለ ሶለቺቱዲኒ የሚል ሓዋርያዊ መሪ ትምሕርት፤ የእውነተኛ የክርስቲያን መንፈስ ኣንደኛና ዋና ምንጭ ቤተክርስቲያን ቅዱሳት ምሥጢራት በኅብረት መጸለይና በቤተ ክርስትያን በዓላት መሳተፍ ነው። ብለዋል፤ በዚህም ዘወትር ምሥጢራት መሳተፍን ኣደራ ብለዋል፤ በየዕለቱ ቅዱስ ቊርባን ለመቀበልም ገፋፍተዋል፤ ሕጻን ኣ እምሮውን መጠቀም ሲጀር ይቊረብ በማለት የሕጻናት የመጀመርያ ቊርባን ዕድሜን ወደ ሰባት ዓመት ዝቅ ኣድርገዋል፤

ወንድሞቻቸውን ለማጽናናት ታማኝ የነበሩ ቅዱስ ፕዮስ 10ኛ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ በተከሰቱ የንባበ መለኮት ክርክሮች ም እመናንን ከስሕተተኛ ኣስተሳሰብ ለማዳንና ከቤተ ክርስትያን ልማድ የሚጓዝ ጤነኛ የግልጸት ጥናት ለማካሄድ ዘመናዊነት ወይም ሞደርኒዝምን በቊርጠኝነት አውግዘዋል። እ አ አ ግንቦት 7 ቀን 1909 ዓም ቪነያ ኤለክታ በሚል ሐዋርያዊ መል እክት ጳጳሳዊ የቅዱስ መጽሓፍ ተቅዋም ማለት ፖንቲፊቾ ኢስቲቱቶ ቢብሊኮ መሥርተዋል። የሕይወታቸው መጨረሻ ወራት በውግያና በውግያ ወሬ የተሞሉ ነበር። እ አ አ ነሐሴ 2 ቀን 1914 ለመላው የዓለም ካቶሊኮች መራራውን ሥቃያቸውን ለመግለጥ ያቀረቡት ጥሪ እርስ በእርስ በሚጋደሉ ልጆች ኣንጀቱን ያረረ ኣባት ልቅሶ ነበር። ከዚህ በኋላ ወዲያውኑ ነሐሴ 20 ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ቅድስናቸው ወዲያውኑ በክርስትያኖች መሃከል መወራት ጀመር።

ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ ቅዱስ ፕዮስ 10ኛ ለሁላችን የሚሆን ትምህርት ይሰጡናል። በሓዋርያዊ ግብረ ተል እኮም ይሁን በሊሎች በተለያዩ መስኮች ስንሠራ ሁል ግዜ ከክርስቶስ ጋር በየዕለቱ የምንኰተኲተውና የምናሳድገው ጥልቅ ግኑኝነት ሊኖረን ያስፈልጋል። የትምህርታቸውና የግብረ ተልእኮኣቸው ኣንኳር ይህ ነበር። ጌታን የምናፈቅር ሲሆን ብቻ ነው የሰው ልጆችን ወደ እግዚአብሔር ለመሳብና ለመሓሪ ፍቅሩ ክፍት ለማድረግ የምንችለው። በዚህም ዓለም ሙሉ ለእግዚአብሔር ምሕረት ክፍት ይሆናል።’ ሲሉ ስለ ቅዱስ ፕዮስ 10ኛ ካስተማሩ በኋላ የሚከተለውን ጥሪ ኣቅርበዋል። ‘ባሁኑ ግዜ ቀልቤና ሓሳቤ በቅርቡ ብዙ ሕይወት ባጠፋና ብዙ ቤተ ሰብ ቤት ኣልባ ባደረገ በውኃ ማጥለቅለቅ በሚሰቃይ በተከበረው የፓኪስታን ሕዝብ ላይ ነው፤ በዚሁ ኣሳዛኝ ፍጻሜ ሕይውታቸውን ላጡት በቸሩ እግዚአብሔር ምሕረት ሳማጥን በመንፈስ ከቤተሰቦቻቸውና በዚህ ኣደጋ ከሚሰቃዩ ጎን መሆኔን መግለጥ እወዳለሁ። በዚሁ ትልቅ ፈተና እጅግ ለተፈተኑ ለእነዚህ ወንድሞቻችን ኣጋርነታችንና የዓለም ኣቀፍ ማኅበረሰብ እርዳታ እንዳይጐድላቸው ኣደራ፤’ በማለት ጥሪ ኣቅርበዋል።

በመጨረሻም በኤውሮጳ ዋና ዋና ቋንቋዎች ትምህርቱን ኣጠር ባለ መልክ ኣቅርበው ለም እመናኑና ነጋድያኑ በተለያዩ ቋንቋዎች ሰላምታ ኣቅርበው ሓዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.