2010-08-16 16:54:58

ፍልሠታ ለማርያም


ክርስትና የሚያበስረው ደኅንነት የምንወደውን ዘለዓለማዊ ሕይወት እንጂ የማይጨበጥ ደኅንነት ኣይደለም

ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና ረፋድ ላይ ለዕረፍት ከሚገኙት ካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያዊ ኣደራሽ የመልኣከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት ‘እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደ ክርስቶስ ልጇ ሞትን ኣሸንፋ በነፍስዋና በሥጋዋ በሁለመናው ሰማያዊ ክብር እንደተጐናጸፈች እናምናለን’ ሲሉ በላቲኑ ሥርዓተ ኣምልኮ ትናንትና የተዘከረውን የፍልሠታ በዓል የተመለከተ ትምህርት ሰጥተዋል።

እንዲሁም ቅዱስነታቸው ትናንትና ጥዋት በካስተንጋንደልፎ በሚገኘው የቅዱስ ቶማስ ዘቪላኖቫ ቊምስና ቤተ ክርስትያን ውስጥ ቅዳሴ ኣሳርገዋል።

የፍልሠታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚከተለዉን ስብከት ሰብከዋል።

“ልዑላን ካርዲናላትና ብፁዓን ጳጳሳት፤ የተከበራችሁ ባለሥልጣናት፤ ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ

ዛሬ ቤተ ክርትያን በሥርዓተ ሊጡርግያችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ከምታበረክታቸው ታላላቅ በዓላት ኣንዱን በዓለ ፍልሠታን ታከብራለች፤ ምድራዊ ሕይወትዋን ከፈጸመች በኋላ እመቤታችን ማርያም በሥጋዋና በነፍስዋ ለዘለዓለማዊ ክብር ከእግዚአብሔር ጋር በሙላትን በፍጽምና በመወሃሃድ ወደ ሰማይ አረገች። በዚህ ዓመት ዝክረ ጥዑም ር.ሊ.ጳ ፕዮስ 12 በ1950 ዓም ኅዳር ኣንድ ይህንን ዓንቀጸ ሃይማኖት በይፋ ካወጁት 50ኛ ዓመት ይታወሳልን፤ የዓንቀጸ ሃያማኖቱ ኣጻጻፍ ከበድ ያለ ቢሆንም ላነበው እወዳለሁ፤ ዓንቀጸ ሃይማኖቱ ‘ከዘለዓለም በምሥጢራዊ መንገድ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኣንድ የሆነች፤ ካለ ኣዳም ኃጢኣት የተፀነሰች ድንግል በክልኤ በመልኮታዊ እናትነትዋ፤ የመለኮታዊ መድኃኒ ለጋስ ተባባሪ የሆነች፤ በኃጢኣትና በሳቢያው ላይ ሙሉ ድል የተጐናጸፈች በመጨረሻ ላይ እንደ ክብርዋ ኣክሊል በመቃብር ውስጥ ከመበስበስ ተጠበቀች፤ በሰማይ ኣሸብራቂ ንግሥት ሆና ዘለዓለማዊ የማይሞት ንጉሥ በሆነ በልጇ ቀኝ ለመኖር እንደ ልጅዋ በሥጋዋና በነፍስዋ ወደ ሰማያዊ ክብር ከፍ በማለት ሞትን ኣሸነፈች’ ይላል። በፍልሠታ የእምነታችን ኣንኳር ይህ ነው፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደ ክርስቶስ ልጅዋ ሞትን ኣሸንፋ በሥጋዋና በነፍስዋ ሰማያዊ ክብር በመጎናፀፍ ወደ ሰማይ አረገች።

ቅዱስ ጳውሎስ ዛሬ በሚነበበው መልእክቱ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈው ይህንን ለማብራራት ይረዳናል፤ የሞቱ በኲር የሆነ የክርስቶስ ትንሣኤ የዚህ ታሪክና የእምነታችን ታሪክን ይገልጣል፤ እኛ ሁላችን በኢየሱስ ምሥጢረ ፋሲካ በመጣመር እርሱ በኃጢኣትና በሞት ላይ በተቀዳጀው ድል እንደምናሳተፍ ኣድርጎናል። የሰው ልጅ ሕይወት ቁልፍና ኣስደናቂ ምሥጢር በዚህ ይገኛል። ቅዱስ ጳውሎስ ‘ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ’ በማለት ሁላችን ከኣሮጌውና ከኣንደኛው ኣዳም የወረስነውን ይገልጣል፤ ይህም ሥቃይ ሞትና ኃጢኣት መሆናቸው ናቸው፡ ሆኖም ግን በዚሁ ሁላችን የማናየውና የምንኖረው ዕለታዊ ሕይወት መታደስን ያበስራል፤ንግግሩን በመቀጠል ‘እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።’ በማለት ከኣዲሱ ኣዳም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣው ክርስቶስ ጋር ኣንድ ኣካል እንደሆንም ይገልጣል። ስለዚህ ከእርሱ ጋር ኣንድ ስላደረገን የትንሣኤ ሕይወት በውስጣችን ኣለ። ለማጠቃለል የመጀመርያው ኣካልነት ሥነ ሕይወታዊ ወይም ባዮሎጂካዊ ሲሆን ሞት የሚያመጣ መጣመር ነው። ሁለተኛው ኣንድ ኣካል መሆን በምሥጢረ ጥምቀት የሚሰጠን የሕይወት ኣንድነት ነው። በተጨማሪ ለመጥቀስ ቅዱስ ጳውሎስ ‘ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤ በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል።’ 1ቆሮ 15፤21/24።

ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሁሉ የሰው ልጅ የሚያጸድቀውን ቤተ ክርስትያን በማይሳሳት ትምህርትዋ ላንዴና ጥርት ባለ መንገድ የኣምላክ እናት በመሆን በምሥጢረ ክርስቶስ የተሳተፈተች የዚህ ዓለም ሕይወትዋን ከፈጸመች በኋላ በሁለመናዋ በልጅዋ ትንሣኤም ትሳተፋለች፤ በዓለም መጨረሻ ያ እኛ የምንጠባበቀው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው የመጨረሻው ጠላታችን የሆነ ሞት ከነጭራሹ የተደመሰሰበት ኑሮ ትኖራለች፤ በጸሎተ ሃይማኖት ‘የሙታን ትንሣኤንና በሚመጣው ዓለም ባለው ሕይወት እናምናለን’ የምንለውን ትኖራለች። ስትል ስለ እመቤታችን ንፅሕት ድንግል ማርያም ፍልሠተ ሥጋ ወነፍስ ታስተምራለች።

የዚህ ለማርያም በቅድምያ የተሰጣት ድል መሠረቱ የት ነው ብለን ለመጥየቅ እንችላለን፤ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ 1፡39~56 እንደዘገበው የዚህ መሠረት በናዝሬቲቱ ድንግል እምነት ነው፤ ይህ እምነት በእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ሁለ ነገርዋን በእግዚአብሔር እጅ በመተው ለመለኮታዊ ተግባር መሰጠት ነው። የእመቤታችን ድንግል ማርያም ታላቅነቷ እምነቷ ነው፤ ይህንን ቅድስት ኤልሳቤጥ ‘እመ ኣምላክ በመሆንሽ ከሴቶች ሁሉ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፤ የብፅዕናዎች ሁሉ መጀመርያ የሆነውን የእምነት ብፅዕናን በመቀበልና ልዩ በሆነ መንገድ እተግባር ላይ ስላዋለችው ነው። ይህንን ቅድስት ኤልሳቤጥ በማኅፀንዋ በዘለለው ሕፃን ደስታ ተሞልታ ‘ኣንቺ እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ የሚፈጸም መሆኑን በማመንሽ ምንኛ የታደልሽ ብፅ ዕት ነሽ’ በማለት ገለጠችው።

ውድ ጓደኞቼ እመቤታችን ድንግል ማርያምን በተቀበለቸው ክብርና ጸጋ ከእኛ እጅግ እንደ ተለየች ኣድርገን ኣናስብ፤ ይልቅስ ጌታ በፍቅሩ እኛ ደስ የሚያሰኝ ፍጻሜ እንዲኖረን ምንኛ ያህል እንዳደረገልን ተጠርተናል፤ በእምነት ከእርሱ ጋር ኣንድ በመሆን በፍጽምናና በእውነት ለመኖር እንደምንችል እናስታውስ።

ወደ ዓንቀጸ ሃይማኖት መለስ ብለን የተመለከትን እንደሆነ፤ ስለ ወደ ሰማያዊ ክብር ፍልሠት ወይም መውጣት ይናገራል። ባለነው የትምህርትና የኣስተሳሰብ ዕድገት ሰማይ ስንል ስለቦታ ወይም ስለኮከብ ኣለመናገራችንን እንረዳለን፤ እኛ የምንናገረው ስለ ሌላ ኑሮ ማለት ከዚህ የላቀ ትልቅ ነገር ነው የምናመለክተው፤ ሰማይ ስንል ከድንግል ማርያም በመወለድ ከእኛ ጋር የሆነ እግዚአብሔር ለዘለዓለምም የማተወን ለእያንዳንዳችን ቦታ ኣለው ለማለት ነው። ይህንን ለመረዳት በሕይወት የሚገጥመንን መመልከት እንችላለን፤ የምንወደው ሰው የሞተ እንደሆነ በሚወዱትና በሚያውቁት ኣ እምሮ ሁል ጊዜ ኣለ፤ በእነዚህ ኣማካኝነት መኖርን ይቀጥላል ለማለት እንችላለን፤ ይህ በሰዎች ልብ ወይም ኅሊና መኖር ግን እንደ ጥላ ነው፤ የጊዜ ገደብ ኣለው። እግዚአብሔር ግን የጊዜ ገደብ የለውም፤ ለዘለዓለም ይኖራል፤ እኛ ሁላችን በፍቅሩ ኃይል እንኖራለን። ስለሚያፈቅረን እንኖራለን፤ ስለሚያስበን እንኖራለን፤ ለሕይወት ስለ ጠራን እንኖራለን። በእግዚአብሔር አሳብና ፍቅር እንኖራለን። እንደ ጥላ በሚመሰለው በናኝና ኣላፊ ሁኔታችን ሳይሆን በጌታ ፍቅርና ህልውና በእውነት እንኖራለን። እርጋታችን ተስፋችንና ሰላማችን በእግዚአብሔር ፍቅርና ኣሳብ ይመሠረታሉ፤ በጥላችን ወይም ኣስተሳሰባችን ሳይሆን በእርሱ በፈጣሪ ፍቅሩ እንኖራለን፤ በዚህ ፈጣሪ ፍቅሩ እንጠበቃለን በዚህም ላለነው አጠቃላይ ሕይወትና ለሚመጣው ዘለዓለማዊ ሕይወት እንጠበቃለን።

ሞትን በማሸነፍ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠን ፍቅሩ ነው፤ ይህንን ፍቅር ነው ሰማይ ብለን የምንጠራው፤ ለሁላችን የሚሆን ሥፍራ ያለው እግዚአብሔር ይህን ያህል ትልቅ ነው። ስለ ድኅነታችን ሰው የሆነው ኢየሱስ እግዚአብሔርም ነው፤ የዚህ ትልቅ ስጦታ ኣብነት ነው ማለት ሰው መሆንና እግዚአብሔር መሆን ኣብሮ ለዘለዓለም እንደሚኖር ዋስትና ሆኖልናል። እያንዳንዳችንን እንደየሁኔታችን በሙላት እንዳለነው እንኖራለን፤ ይህ ማለት እግዚአብሔር እንዳለነው ያውቀናል ያፈቅረናልም፤ በዘለዓለማዊ መንግሥቱም በዚሁ በሥቃይና ፍቅር በተስፋ በደስታና በኃዘን እያደገና እየተለወጠ የሚጓዝ ሕይወት እንዳለነው ይቀበለናል፤ የሰው ልጅ ሕይወት ከእግዚአብሔር ይመጣል በእርሱ ጠርቶም ለዘለዓለማዊነት ይበቃል። ውድ ጓደኞቼ ይህ እውነት ጥልቅ በሆነ ደስታ ልባችንን መምላት ያለበት ነው ብየ ኣምናለሁ፤ የክርስትና እምነት ሁኔታው ያልታወቀ የነፍሳት ደኅንነት ማለትም በዚህ ዓለም ጣዕምና ክብር ያለው ሁሉ ይደመሳል ብሎ ብቻ ኣያስተምርም፤ በእግዚአብሔር ፊት ሙላት የሚያገኛ የማያልፍና የማበርስ ክብርና ጣዕም ባለው በሚመጣው የሕይወት ዓለም የሚገኝ የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ይሰጣል፤ ኢየሱስ በማቴዎች ወንጌል 10፡30 እንዳለው የራሳችን ጠጒሮችም ሳይቀሩ የተቆጠሩ ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮማውያን 8፡21 በጻፈው ‘ይሁን እንጂ ይህ ትስፋ ኣለ፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ከእግዚአብሔር ልጆች የነፃነት የክብር ተካፋይ እንዲሆን ነው።’ ሲል እንደሚያረጋግጥልን የሚመጣው ዓለም የዚህ ምድር ፍጻሜ ሊሆን ነው። ስለዚህ የክርስትና ሃይማኖት ብሩህ መጻኢ የሆነ ኃያል ተስፋ በመስጠት ለዚሁ የወደፊት ሕይወት መንገድ ይከፍታል። እንደ ክርስትያን እኛ ሁላችን ይህንን ኣዲስ ዓለም ለመገንባት የተጠራን ነን፤ ይህ ዓለም ለመገንባት ከምንችለው ሁሉ በላይ የሆነ የእግዚአብሔር ዓለም እስከ ሚሆን እንድንሠራ የተጠራን ነን፤ የልጅዋን ትንሣኤ በሙላት በመሣትፍ ወደ ሰማይ ከወጣችው ድንግል ማርያም በመሆን የዚሁ የእግዚአብሔር ዓለም እቅድ እውን እንዲሆን እንትጋ፤ ሕይወታችን በእግዚአብሔር ፊት ምንኛ ያህል ክብርት መሆንዋን ለመገንዘብ እንድንችል እንዲረዳን ለዘለዓለማዊ ሕይወት ያለንን እምነት እንዲጐለብትልን እንዲሁም የተስፋ ሰዎች በመሆን ለእግዚአብሔር ክፍት የሆነ ዓለም እንድንገነባ ለዚሁ ለከንቱ ነገሮች ትኲረት የሚሰጠውን ሕይወታችን የመጪው ዓለም ጣዕም እንዲረዳና በዚሁ እርግጠኝነት እንድንኖር እንድናምንና ተስፋ እንድናድርግ ደስታ የሞላቸው ሰዎች እንዲያደርገን እግዚአብሔርን እንለምን፤ ሲሉ ስብከታቸውን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.