2010-08-11 16:12:39

የር.ሊ.ጳ የዕለተ ሮቡዕ ሳምንታዊ ኣጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ (11.08.2010)


ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ዛሬ ረፋድ ለዕረፍት ከሚገኙት ካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያዊ ኣደራሽ በቦታው ለሚገኙ ምእመናንና ነጋድያን የተለመደውን ሳምንታዊ የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ ኣስተምረዋል። ትምህርቱም ይህ ነው፤ “ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ ዛሬ በሥርዓተ ኣምልኮኣችን የክላሪሰ ደናግል ማኅበር መሥራችና ብርሃናዊት ኣብነት የሆነች ቅድስት ክያራ ዘኣሲዚ እናስታውሳለን፤ ስለ እርሷ ወደ ፊት በኣንድ የዕለተ ሮቡዕ ሳምንታዊ ኣጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ እንናገራለን፤ ባለፈው እሁድ የመልኣከ እግዚአብሔር ኣስተምህሮ እንደገልጥሁት በዚሁ ሳምንት ብዙ ቅዱሳን ሰማዕታት እናስታውሳለን፤ እንደ ቅዱስ ሎረንሶ ሰማዕት ዲያቆን ቅዱስ ፖንስያኖ ጳጳስ ቅዱስ ሂፖሊቶ ካህን ጥንታውያን ሰማዕታት፤ እንዲሁም የቅርብ ግዜ ሰማዕታት ቅድስት ተረዛ በነደታ ዘመስቀል ወይም ቅድስት አዲት ሽታይን ሰማዕት የኤውሮጳ ጠባቂ፤ ቅዱስ ማሲሚልያኖ ኮልበ ሰማዕት ካህን እናስታውሳለን። ስለዚህ በዛሬው ትምህርት ስለ ሰማዕትነት መናገር እወዳለሁ፤ ሰማዕትነት ለእግዚአብሔር በሙላት የሚገለጥ ፍቅር ነው።

ሰማዕትነት መሠረቱ የት ነው፧ መልሱ ቀላል ነው፤ በኢየሱስ ሞት ነው፤ በዮሓንስ ወንጌል 10 እንዳለው እኛ ሕይወት እንድናገኝ እንዲያውም የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖረን ስለኛ በመስቀል ላይ የተፈጸመው የኢየሱስ ከፍተኛና ፍጹም መሥዋዕት የሰማዕትነት መሠረት ነው። ክርስቶስ በነቢይ ኢሳያስ የተነገረው የሚሰቃይ የእግዚአብሔር ባርያ ነው፡ ስለ ብዙዎች መሥዋዕት እንዲሆን ራሱ ሰጥተዋል፤ ክርስቶስ የእርሱ ተከታዮችን ለሁላችን፤ ‘በየዕለቱ እያንዳንዳችን መስቀላችን እንድንሸከምና ለእግዚአብሔርና ለመላው የሰው ልጅ ባለን ፍጹም የፍቅር ጐዳና እንድንከተለው ኣደራ ይላል። ስለዚህም በወንጌለ ማቴዎስ 10፡38 “መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።” በማለት ያስጠነቅቀናል።

ይህ ኣስተሳሰብ የስንዴ ዘር ምሳሌን ይከተላል፤ ‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በመሬት ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ታፈራለች፡’ (ዮሐ 12፡24) ኢየሱስ ራሱ ከእግዚአብሔር የመጣ የስንዴ ቅንጣት ነው፤ በመሬት ላይ ወድቆ መሞትን የወደደ ኅብስት ሆኖ እንዲቆረስ የፈቀደ እንዲሞት የፈቀደና በዚህም ለዓለም ሙሉ የሚሆን ፍሬ ለመስጥትና ራሱንም ለመክፈት የመጣ መለኮታዊ የስንዴ ቅንጣት ነው። ሰማዕት ባስቸጋሪ የእምነትና የፍቅር ፈተና ጊዜ በነጻነቱ ለዓለም ደኅንነት እንዲሞት ዝግጁ በመሆን ኢየሱስን እስከ መጨረጻ ይከተላል።፡(ብርሃነ ኣሕዛብ ቊ.42)

መለስ ብለን የተመለከትን እንድሆነ ሰማዕትነትን ለመጋፈጥ የሚሆን ኃይል ከየት ይወለዳል፧ ሰማዕትነትና የሰማዕትነት ጥሪ በሰው ልጅ ዐቅም ልንደርሳቸው ስለማንችል ምንጫቸው ከክርቶስ ጋር ካለን ጥልቅና ጥብቅ ግኑኝነት ነው፤ ስለዚህም ሰማዕትነ የእግዚአብሔር ጸጋ ሆኖ ለእግዚአብሔር ጥሪ የሚሰጥ መልስ ነው፤ ይህም ጸጋ ሕይወትን ለክርስቶስ ለቤተ ክርስትያንና ለዓለም ፍቅር ለመስጠት የሚያስችል ጸጋ ነው። የሰማዕታት ሕይወትና ገድል ያነበብን እንደሆነ ሥቃይንና ሞትን ሲገጥሙ በሚያሳዩት እርጋታና ብርታት እንደነቃለን፤ የእግዚአብሔር ችሎታና ኃይል በሙላት በሰው ልጅ ድካምና ድህነት ሲገለጥ እናያለን፤ ‘የእኔ ኃይል የሚግለጠው በኣንተ ደካማነት ስለሆነ ጸጋዬ ይበቀሃል’ ያለው በእርሱ ለሚያምኑትና በእርሱ ተስፋ ለምያደርጉት ኃይልና ብርታት ይሰጣቸዋል። ሆኖም ግን የእግዚአብሔር ጸጋ የሰማዕታት ነጻነትን እንደማጨቊን መረዳት ያስፈልጋል በተቀራኒው ሃብታተ መንፈስ ቅዱስ እየስጠ ከፍ ያደርገዋል፤ ሰማዕት ከዓለም ሙሉ በሙሉ ነጻ ነው፤ ለኣንዴና ለመጨረሻ በትልቅ የእምነት የተስፋና የፍቅር ሥራ ሕይወቱን ለእግዚአብሔር የሚሰዋ ነው፤ ነፍሱን በፈጣሪውና በኣዳኙ እጅ ይተዋል፤ በመስቀል ከተሰዋ ክርስቶስ ጋር ኣንድ ለመሆን ሕይወቱን መሥዋዕት ያደርጋል። በሌላው ኣነጋገር ሰማዕትነት ወደር ለሌለው የእግዚአብሔር ፍቅርን ለመመለስ የሚፈጸም ትልቅ የፍቅር ተግባር ነው።

ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ ባለፈው ሮብ እንዳልኩት፤ ምናልባት እኛ ለሰማዕትነት የተጠራን ኣይደለንም፤ ሆኖም ግን ለቅድስና ከሚደረገው መለኮታዊ ጥሪ ኣንድም ነጻ ኣይደለም፤ ክርስትያናዊ ህይወታችንን በፍጽምና እንድንኖር ተጠርተናል ይህም በየዕለቱ እያንዳንዳችን መስቀሉን መሸከም እንዳለብን ያሳስበናል። ለኔ ይምቸኝ የሚል የግል ኑሮ ስግብግብነት በሞላበት ዘመናችን በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ ፍቅር በየዕለቱ መገስገስ ኣለብን፤ ይህን ያደረግን እንደሆነ ሕይወታችንም ይሁን ዓለማችን ለመለወጥ እንችላለን። እርሱ እያንዳንዳችን እንደሚያፈቅረን ልባችንን ለፍቀር እንዲከትልናን እንዲያበራልን እግዚአብሔርን በቅዱሳኑና በሰማዕታቱ እንለምነው፡፡” በማለት ትምህርታቸው ፈጽመዋል። በመጨረሻም በተለያዩ ቋንቋዎች ሰላምታ ኣቅርበው ኣባታችን በሰማይ የምትኖር በላቲን ቋንቋ እንዘምር በማለት ከምእመናኑ ኣብረው ኣዚመው ሓዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.