2010-07-28 12:40:53

የእግዚአብሔር ፈቃድ መፈጸም የሰው ልጅ ነጻነትን እውን ያደርገዋል እንጂ ኣይጨቊነውም፤


በላቲኑ ሥርዓተ ኣምልኮ የትናንትና ወንጌል “የሰማያዊ አባቴ ፈቃድ የሚፈጽም፤ እርሱ ለእኔ ወንድሜ ነው፤ እኅቴና እናቴም ነው” በሚል ሓረግ ይደመደማል፤ ይህ የወንጌል ጥቅስ እመቤታችን ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ሁሉ ለእግዚ አብሔር ፈቃድ በመገዛት ሰብ ኣዊና መለኮታዊ ነገሮች እንዲገናኙ ማድረጋቸውን ያመለክታል።

ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በዚህ ር እስ ብዙ ስብከትና ኣስተምህሮ ኣቅርበዋል፤ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ታዛዥነትና ትሕትና ለሰው ልጅ ደኅንነት ምንኛ ያህል ኣስፈላጊ እንደነበረ ለመግለጥ ከዓመታት በፊት “በሰው ልጅ ደኅንነት ታሪክ ውስጥ በናዝሬት ከተማ ኣንድ ወጣት ድንግል ራስዋን ለእግዚ አብሔር ፈቃድ ዝቅ በማድረግ እሺ በማለት በችግር ተውጦ የነበረው የሰው ልጅ ሕይወት የእግዚ አብሔር ጸጋ ሊፈስበት ጀመር፤ የእመቤታችን ድንግል ማርያም አለ ምንም መጠራጠርና መከራከር የእግዚ አብሔር ፈቃድ መቀበል ዛሬም ቢሆን እግዚ አብሔር የሰው ልጆችን በምሕረት እንዲጎበኝ ያደርገዋል፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከ20 ዘመናት በፊት በናዝሬት ቤተ መቅደስ በልበ ምሉነት እነሆኝ የእግዚአብሔር እገልጋይ እንደ ፈቃዱ ይሁን ያለችው ገና ዛሬም የክርስትና እምነት ዕድገት ጽኑ ትእምርት ነው፤ ምክንያቱም በዘመናችን የተመለከትን እንደሆነ ገደብ የለሽ ነጻነትና ግዳጅ ኣልባ መብት የእግዚ አብሔር ፈቃድ መፈጸምን ኣግደዋል፤ እንዲሁም የግል ጥቅምን ቅድሚያ በመስጠት የሰው ልጅ ማኅበራዊ ሕይወትና ጥቅምን ጐድተዋል፤በአጠቃላይ በዘመናችን በትሕትና ለሌላ ሰው መታዘዝ ለብዙዎች ትርጉም ኣልባና የማይዋጥ ሆነዋል፤ሲሉ የመታዘዝ መንፈስ ለኅብረተሰብ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሕይወት ኣስፈላጊነት ኣስተምረው ነበር፤

በበዓለ ፅንሰታ ለማርያም ታሕሣሥ 8 ቀን 2005 ዓመተ ምሕረትም “የዘመንችን ሰው በእግዚ አብሔር መታመንን እያቃተው ነው፤ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ነጻነት የሚጫረት ከሕይወቱ የሚቀንስ ለእርሱ እንድንገዛ ነጻነታችን እንደሚወስን ኣድርጎ በማየት የሰው ልጅ ደግሞ ለዚህ የተገዛ እንደሆነ በሙላት እንደሚኖር ኣድርገው የሚገምቱ ኣሉ፤ እንዲሁም የእግዚኣብሔር ፍቅር ጥገኝነት እንደሚፈጥር ግዳጅ ኣድርጎ መገመትም ኣይጠፋም፤ በሚል ጥርጣሬ በችሎታና በእውቀት መካከል ለሚታገለው የዘመናችን ሰው የእመቤታችን ትህትና የእግዚአብሔር ችሎታና ጥበብ ኣካል በመሆን የሰው ልጅ ሁኔታን በሚያስደንቅ ሁኔታ ይለውጠዋል፤እንደ እርስዋም እሺ ለማለት ብቃት ይሰጠዋል ብለው ነበር።

ሁለመናውን በእግዚአብሔር እጅ በመተው ለእግዚአብሔር ብቻ የሚታዘዝ ሰው የእግዚአብሔር አሻንጒሊት ኣይሆንም ነጻነቱን ኣያጠፋም፤ በእግዚአብሔር የሚጠጋ ሰው ከፍ በማለት ትልቅ ሰው ይሆናል እንጂ ኣያንስም፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰውና መልእልተ ባህርያዊ በመሆን እውነተኛ ሰው ይሆናል፤ ሁለመናውን በእግዚአብሔር እጅ በመተው ለእግዚአብሔር ብቻ የሚታዘዝ ሰው ከሌሎች ኣይርቅም፤ የሌሎች ሁኔታ የሚያሳስበው ለሌሎች ክፍትና ወዳጅ ይሆናል፤ ሲሉ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ስለሚገኘው ጸጋ ኣስተምረው ነበር።

በእግዚአብሔር የሚታመን ሰው ክፍትና ወዳጅ ይሆናል፤ ኃይለኛና ጽኑም ይሆናል፤ ለዚህም አብነትና ትምህርት የሚሆነን ክርስቶስ በምድረበዳ ከሰይጣን ብቻው ሲፋለም ያሳየው ኃይልና ጽናት በቂ ትምህርት ይሰጠናል።

ቅዱስነታቸው ይህንን ሲያብራሩ በተያዝነው ዓመት ለዓቢይ ጾም መባቻ በሰጡት ትምህርት የሚከተለውን ብለው ነበር። “ጌታ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ዋነኛውን መምርያ ኣስቀድሞ ይሰጣል፤ ይህም መምርያ ለእግዚአብሔር ፈቃድ መታዘዝ ነው፤ ይህ ለእኛ መሠረታዊ ትምህርት ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል በኣእምሮኣችንና በልባችን የምንይዝ ከሆንና ይህ በሕይወታችን የምንኖረው ከሆነን ከፈታኙ የሚደርሰንን የሆነ መታለል ለመቃወም እንችላለን” ብልዋል።

ኢየሱስ ሕፃን ሆኖ በናዝሬት በወላጆቹ ሥር ባደገበት ግዜ፤ ለድንግል ማርያምና ለጻድቁ ዮሴፍ በመታዘዝ የሚያስተምረን ነገር ኣለ፤ ቤተ ሰብ በሰው ልጅ ዕድገትና ሕይወት ውስጥ መሠረታዊ አስፈላጊነት እንዳለው ያመለክታል፤

ለእግዚአብሔር ፈቃድ በትሕትና መታዘዝ ምንኛ ያህል ኣስፈላጊ መሆኑን ሲያስረዱ ቅዱስነታቸው ክህነትን እንደ ትልቅ ኣብነት ያቀርባሉ፤ ክህነቱን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የማያገናኝ ካህን እግዚአብሔርንና ሌሎችን በእውነት ሊያፍቅር ኣይችልም፤ ገዛ ራሱን ብቻ ያፈቅራል፤ ተሎ ብሎ ካልታረመ ደግሞ ራሱንም ሊያድን ኣይችልም፤ ስለዚህ ክህነት የእግዚአብሔር ፈቃድ ለመፈጸም እሺ ለማለት መዘጋጀትን ይጠይቃል ሲሉ ኣስተምረዋል።

“የሰማያዊ አባቴ ፈቃድ የሚፈጽም፤ እርሱ ለእኔ ወንድሜ ነው፤ እኅቴና እናቴም ነው” የሚለው የወንጌል ቃል ዘወትር የእግዚአብሔር ፈቃድን ማስቀደም እንዳለብን ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ በምድርም ይሁን የሚለው ጸሎትም ይህን እንድንፈጽም ይጠራናል።








All the contents on this site are copyrighted ©.