2010-07-28 12:36:32

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ (18.07.2010)


ትናንትና እሁድ ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ለበጋ ዕረፍት ከሚገኙት ከካስተል ጋንደልፎ ሓዋርያዊ አዳራሽ ኣብሮዋቸው ለመጸለይና ትምህርታቸውን ለመስማት ለተሰበሰቡት ምእመናንና ነጋድያን ባሰሙት ትምህርት፤ በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የዕረፍትና የመዝናናት ጊዜ የሆነው የበጋ ወቅት ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት ቅድሚያ የሚሰጥበት ምርጥ ጊዜ መሆኑን አመልክተዋል፡ ለዕረፍትና ለጸሎት ከሚገኙበት ባስተላለፉት መልእክት የሰው ልጅ ከሁሉ ይልቅ በመጀመርያ እግዚአብሔር እንደሚያስፈልገው ገልጠዋል::

“የበጋ ወቅት ትምህርት ቤቶች የሚዘጉበት ኣብዛኛውም ለዕረፍት የሚያስብበት ጊዜ ነው፤ የግብረ ኖልዎ ኣገልግሎትም ሳይቀር ቢቀነስም ወቅቱ ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማትና ለማስተንተን የምንጠቀምበት ምርጥ ግዜ ነው” ካሉ በኋላ “የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ እጅግ ከሚያስፈልገውና ዋነኛ ቦታ መሰጠት ያለበት የጌታን ቃል መስማት ነው፤ የዛሬ እኁድ ወንጌልም ይህንን ነው የሚያስተምረን፤ ጌታ ኢየሱስ የማርታና የማርያም ቤት በጎበኘበት ወቅት ቅዱስ ሉቃስ እንደሚተርከው ይህንን ያስታውሳል፤

በወንጌሉ እንደተመለከተው ማርታ ቤቱን ለማዘጋጀትና ትልቁን እንግዳ ለመቀበል ስትዘጋጅ ማርያም ግን የኢየሱስ መኖር ልብዋን ስለሳበው እግሩ ስር ተቀምጣ እርሱን ትሰማ ነበር፤ ማርታ በእኅትዋ ኣኳሃን ስለማትረዳት ስታጒረመርም በሰማት ጊዜ ኢየሱስ ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪያለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት። (የሉቃስ ወንጌል 10፤41=42)

ቅዱስነታቸው የኢየሱስ ንግግርን ሲገልጡ: “ይህ ንግግር የኑሮኣችን እንቅስቃሴን ኣያጓድልም እንዲሁም መስተንግዶን ኣያንቋሽሽም የሚያቀርበው ጥሪ ለሰው ልጅ በእውነት የሚያስፈልገው ሌላ ነገር መሆኑን ያመለክታል፤ ይህም የጌታ ቃልን ማዳመጥ ነው፤ ቃሉን ስናዳምጥ ጌታ በኢየሱስ ኣካል እዛ ኣለ፤ ሌላ ሁሉ ያልፋል የእግዚ አብሔር ቃል ግን ዘለዓለማዊ ነው፤ ለዕለታዊ ተግባራችን ደግሞ ትርጉም ይሰጠዋል። ኢየሱስ በማርታና ማርያም ቤት ያደረገው ጉብኝት የዕረፍት ወቅትን ያመለክታል፡ “ምክንያቱም የሰው ልጅ በቤትም ይሁን በሌላ ቦታ መሥራት እንዳለበት ያስረዳል፤ ሆኖም ግን ከሁሉ ኣስቀድሞ የሚያስፈልገው የፍቅርና የእውነት ውስጣዊ ብርሃን የሆነው እግዚ አብሔር ያስፈልገዋል” ብለዋል።

“የሰው ልጅ ተግባር በዚህ ትርጉም ልንረዳው ይገባል ኣለበለዚያ ግን መሠረታዊ ስሜቱ ኣጥፍቶ ባዶ ሆኖ ይቀራል: ማለትም ተግባራችን ኣለምንም ተጨባጭ ትርጉም ፍሬ ኣልባና መደብ ኣልባ ሆኖ ይቀራል፤ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለኑሮኣችን ፍቅርና እውነት ሊሰጠን የሚችል ማን ነው፤ ወንድሞቼ ኣንዱ ሌላውን እየረዳን መተባበርን እንማር፤ ከሁሉም ኣስቀድመን ግን የላቀውን ብጎኣችን ማለት የተሻለውን ነገር እንምረጥ”፤ ሲሉ ትምህርታቸውን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.