2010-06-28 13:18:46

ዓለም አቀፍ የመናብርተ ጥበብ አስተማሪዎች ጉባኤ


ፍቅር በሓቅ በሚል ርእስ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ የደረስዋት አዋዲት መልእክት ማእክል ያደረገ የሮማ ሰበካ የመናብርተ ጥበብ ሓዋርያዊ ኖልዎ የሚከታተለው ድርገት እና ጳጳሳዊ የፍትሕ እና የሰላም ምክር ቤት ያነቃቃው ዓለም አቀፍ የመናብርተ ጥበብ አስተማሪዎች ጉባኤ ለሶስት ቀናት መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፈው ቅዳሴ በተካሄደው የአውደ ጥናቱ የማጠቃለያ RealAudioMP3 ጉባኤ፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሓፊ ብፁዕ ካርዲናል ታርቺዚዮ በርቶነ ተገኝተው የጉባኤው ርእስ፣ ፍቅር በሓቅ፣ ለማኅበረ-ሰብ ዓለም የሚያገለግል ኤኮኖሚ የሚል መሆኑ በማስታወስ፣ በዓለማችን ተከስቶ ያለው የኤኮኖሚ ቀውስ እና የዚህ የኤክኖሚ መቃወስ በእጅጉ ሰለባ የሆኑት በድኽነት ጫንቃ ሥር የሚገኙት አገሮች እና ሕዝቦች መሆናቸው ገልጠው በበለጸጉት አገሮች እያስከተለው ያለው አዲስ ድኽነት እና የሥራ አጥነት መስፋፋቱ ጉዳይ በመተንተን፣ የሰውን ልጅ የተሟላ እድገት መሠረት በማድረግ የማገልገል ብቃት ያለው ኤኮኖሚ በማረጋገጥ ብቻ ተከስቶ ካለው የኤኮኖሚ ቀውስ ለመላቀቅ የሚቻለው፣ ኤኮኖሚ ለሰው ልጅ እንጂ የሰው ልጅ ለኤኮኖሚ አይደለም ብለዋል።

በዚህ አጋጣሚም ብፁዕነታቸው በዓለማችን ተከስቶ ያለው የኤኮኖሚ ቀውስ ዋና ርእስ በማድረግ በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ የተካሄደው እና ትላትና የተጠናቀቀው በኢንዳስትሪ የበለጸጉት አገሮች ጠቅላይ ስብሰባ በመጥቀስ፣ ፍቅር በሐቅ የተሰኘቸው አዋዲት መልእክት፣ ተከስቶ ካለው የኤኮኖሚው ቀውስ ለመላቀቅ፣ አለማዊነት ትሥሥር በመከተል ሥነ ምግባር የሚያቀድም አዲስ የኤኮኖሚ ሥርዓት አስፈልጊ መሆኑ እንደምታስተምርም ገልጠው፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ፍቅር በሐቅ በሚል ርእስ ሥር የደረስዋት ዓዋዲት መልእክት Rerum Novarum / አዳዲስ ነገሮች በሚል ርእስ ሥር እ.ኤ.አ. ግንቦት 15 ቀን 1891 ዓ.ም. ር.ሊ.ጳ. ሊዮነ ስምንተኛ የደረስዋት ዓዋዲት መልእክት ጋር በማመሳሰል የዘመናችን ሬሩም ኖቫሩም ነች ብለዋል።

ፍቅር በሐቅ የተሰኘችው አዋዲት መልእክት በመጥቀስ ብፁዕነታቸውን ይላሉ ኤኮኖሚ እና ግብረ ሰናይ የማይነጣጠሉ መሆናቸው በማስረዳት፣ ኤኮኖሚ ግለኝነት የሚያንጸባርቅ ሳይሆን ኵላዊነት መልክ ያለው፣ ማንንም በማያገል የሰው ልጅ የተሟላ እድገት የሚደግፍ በአዲስ ደንብ መመራት ይኖርበታል እንዳሉ ተገልጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በዚህ የሶስት ቀናት ጉባኤ የተሳተፉት ጳጳሳዊ የፍትህ እና የሰላም ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ፐተር ኮድዎ አፒያህ ቱርክሶን 500 ተጋባእያን ባሳተፈው ስምንተኛው ዓለም አቀፍ የመናብርተ ጥበብ ጉባኤ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፣ የሰውን ልጅ እና ክብሩን ማእከል ያደረገ ሥነ ምግባር የሚከተል አዲስ የኤኮኖሚ ሥርዓት ወሳኝ መሆኑ በማብራራት፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ፍቅር በሐቅ በሚል ርእስ ሥር የደረስዋት ዓዋዲት መልእክት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ ደግሞ በሥነ ኤኮኖሚ ሊቃውንት እና በተለያዩ የኤኮኖሚ አውታሮች ልዩ ጥናት እየተደረገባት መሆኑ በመግለጥ፣ በዚህች አዋዲት መልእክት ዙሪያ ባንድ ዓመት ውስጥ 4 ሺሕ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችም መካሄዳቸው ገልጠው፣ ስለዚህ አዋዲት መልእክቷ ተክስቶ ካለው የኤኮኖሚ ቀውስ ለመላቀቅ እንዴት እንደሚቻል በምርምር የተደገፉ ምክንያቶች የምታቀርብ መሆኗ ብዙ የኤክኖሚ ሊቃውንት ይናገራሉ፣ አዋዲት መልእክቷ በሁሉም የትምህርት ዘርፍ ጥናት መሠረት መመልከቱ ለሁሉም የሚበጅ ነው እንዳሉ የቅድስት መንበር መግለጫ ይጠቁማል።

ሮማ በሚገኘው የቶር ቨርጋታ መንበረ ጥበብ የኤክኖሚ የትምህርት ዘርፍ ሊቀ መንበር የሥነ ኤኮኖሚ ሊቅ ፕሮፈሰር ሚከለ ባጀላ፣ ዓውደ ጥናቱን በማስመልከት ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፣ የተካሄው ጉባኤ ይላሉ ተቀባይነት ያለው ማንንም የማያገል የኤኮኖሚ ሂደት ለማረጋገጥ ያስችላሉ የሚባሉት መንገዶች መመልከታቸው ገልጠው፣ ተከስቶ ካለው የኤኮኖሚ ቀውስ ለመላቀቅ፣ የኤኮኖሚው ሂደት ግልጽነት፣ ልዩ ቁጥጥር የሚጠይቅ፣ ኃላፊነትን የሚያጎላ መሆን እንዳለበት፣ ፍቅር በሓቅ በተሰኘችው አዋዲት መልእክት ዘንድ የሠፈረው ሃሳብ በአሁኑ ወቅት ብዙ የኤክኖሚ ሊቃውንት እያስተጋቡት መሆኑ በተካሄደው ዓውደ ጥናት መረጋገጡንም ገልጠው የሰጡትን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.