2010-05-22 09:53:15

ብፁዕ አቡነ ብርሃነኢየሱስ ደምረው ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት፣ ለአራተኛ መደበኛ ብሔራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ያስተላለፉት መልእክት፣


የኢትዮጵያ የሃይማኖተ አባቶች በአገሪቱ በመጪዉ እሁድ ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሓዊ እንዲሆን መልዕክት አስተላለፉ ብጹዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ያስተላለፉትን መልዕክት ሙሉ ቃል ከዚህ ሸኚ ጋ አያይዘን ልከናል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት

ማህበራዊና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ
26-8-2002 ዓ.ም.

 
አራተኛ መደበኛ ብሔራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች  

"በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፡ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሣይሆን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሣይሆን ጎብኙት" (1 ጴጥ. 5፡ 2)፡፡
መግቢያ

ከሁሉ አስቀድሜ ይህ ፕሮግራም በመዘጋጀቱ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ "ከችግር መላቀቅ፤ የምግብ ዋስትና ማግኘት፤ ቋሚ ሥራ ማግኘት፤ ኃላፊነቶችን ያለ አድሎ መካፈል፤ ከጭቆና ሁሉ ነጻ መሆን፤ ሰብአዊ ክብሮችን ተከብሮ መኖር፤ የትምህርት ዕድል ማግኘት፤ የመኖር ዋስትናው ተጠብቆ መኖር፤ በአጠቃላይ የተሻለ ኑሮ መኖር" የኢትዮጵያ ሕዝቦች ምኞት ነው (የሕዝቦች እድገት 6)፡፡ "እያንዳንዱ ዜጋ መሪዎቹን መምረጥ የራሱ መብትና ኃላፊነት መሆኑን በማወቅ የመምረጥ መብቱን ተጠቅሞ ለሕዝቦች የጋር ጥቅም አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፤ ለሕዝብ አገልግሎት ራሳቸውን ለመሠዋት እጩ አድርገው የፖለቲካ ሸክም ለመሸከም የሚወዳደሩ ግለሰቦችን በአክብሮት እንመለከታለን" (ቤተክርስቲያን በዘመናችን 75)፡፡

1/ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት፡ በተቻለ መጠን በተለያዩ ፓርቲዎች መካከል ያሉ የምርጫ ልዩነቶችን ለማጥበብ የማያቋርጥ የመግባባት ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡

2/ የኃይል አጠቃቀምን ማስቀረት፡ በምርጫ ወቅትና በኋላም መራጮች ሆኑ ሥነ ሥርዓት አስከባሪዎች የኃይልና የአመጽ አጠቃቀምን ጨርሶ ማስቀረት፡፡ በአጠቃላይ የሰው ክቡርነት ከሀሳብ ልዩነታችን በላይ መሆኑን አውቀን ለሰላም የሚቻለውን ዋጋ መክፈል ተፈጥሮአዊ ግዴታችን ነው፡፡

3/ ያለፈውን ስህተት አለመድገም፡ ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለስ ላለፉት ብዙ ዓመታት የሀገራችን ሕዝብ የኑሮ ሰላም የሚያናጉ አልፎም ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት የሆኑ ብዙ ዓይነት ግጭቶችንና ጦርነቶችን አስተናግደናል፡፡ እኛ በታሪኩ ውስጥ አልፈን በሁኔታው ያለፍን ሰዎች እነዚያ ጊዜያቶች መልሰን በልጆቻችን ታሪክ ውስጥ ማየት አንመኝም፡፡ ሰላምን የሚያደፈርሱ፤ አላስፈላጊ ሕይወትን የሚያስከፍሉ መፍትሔዎች በእኛ ይብቁ፡፡ የበሰለ የሰለጠነና እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው አስተሳሰብና እርምጃ አወሳሰድ ይኑረን በማለት ጥሪያችንን በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም እናስተላልፋለን፡፡

4/ የመምረጥ ኃላፊነት፡ አሁን ያለንበት ወቅት ለቀጣዩ አምስት ዓመታት የሚመራንን ፓርቲ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ የምርጫው ሥነ ሥርዓት በእርግጥ ለአንድ አገር እጅግ አስፈላጊና ሊዘለል የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም ዕድሜው ለመራጭነት የደረሰ ዜጋ ሁሉ የሀገሪቱ የጋራ ጥቅም ተካፋይ ባለመብት እንደመሆናቸው መጠን የመምረጥም ተፈጥሮአዊ የዜግነት መብትና ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን መብታችንን በምንጠቀምበት ጊዜ የመጀመሪያውን ደረጃ በሀገራችን ግንባታ ላይ መሳተፋችን በመሆኑ በኅሊናው የወሰነውን ፓርቲ ያለ ምንም ውጫዊ ተጽእኖ መምረጥ ይችላል፡፡

5/ ከምርጫ በኋላ ጥንቃቄ ስለማድረግ፡ ከተለያዩ ሀገሮች የምርጫ ሂደት እንደምንማረው፤ የሕዝብ ሰላም የሚቃወሰው በምርጫ ዝግጅት ወቅት ሣይሆን በምርጫ ሂደትና ከምርጫ በኋላ ባሉት ቀናት ነው፡፡ እኛም ካለፉት ጥቂት ልምድ ያየነው ይህንኑ ነው፡፡ ለዚህ ሰላማዊ ውጤት የብዙዎች ተሳትፎ የሚጠይቅ (የመንግሥት የተመራጮችና የመራጮች) መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምንም ይሁን ምንም ግን አንዱ በሌላው ላይ በመጠቆም ወይንም ምክንያት በማድረግ የሕዝብን ሰላም ማናጋት አግባብ እንዳልሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ይህን ስል ሊባሉ የሚችሉ ምክንያቶች ትክክል አይደሉም ለማለት ሳይሆን በሰላም መወያየት መነጋገር የማይቻል ምክንያቶች ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ ቢኖርም የሰለማዊ ሰውን ሕይወት ለሞት የሚዳርግ አካሄድ መምረጥ ከተፈጥሮ ሕግ የሚቃረን ነው፡፡

6/ ጸሎት ስለማድረግ፡ በምርጫ ጉዳይ ዙሪያ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብና የሚመለከተው ክፍል ሁሉ ምርጫው ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን የሚቻለውን ጥረት እንዲያደርጉ በእግዚአብሔር ስም አደራ እያልኩ፤ ምእመናን ሁሉ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ጸሎት እንዲያደርጉ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
ጸሎት
ጌታ ሆይ የሰላም መሣሪያ እንድሆን አድርገኝ

ጥል ባለበት ፍቅር

በደል ባለበት ይቅርታ

ክርክር ባለበት ስምምነት

ጥርጣሬ ባለበት እምነት

ስህተት ባለበት እውነት

ተስፋ መቁረጥ ባለበት መጽናናት

ሐዘን ባለበት ደስታ

ጨለማ ባለበት ብርሃን እንዲገኝ አድርግ ዘንድ አብቃኝ! አሜን!!!



+ አቡነ ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት








All the contents on this site are copyrighted ©.