2010-04-14 15:59:10

የር.ሊ.ጳ. የዕለተ ሮቡዕ የትምህርተ ክርስቶስ አጠቃላይ አስተምህሮ14.03.2010


 

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳጳሳት በነዲክቶስ 16 ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ በቅዱስ ጲጥሮስ አደባባይ አጠቃላይ ሳምንታዊው የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መክፈቻ ጸሎት አሳርገው ከአንደኛይቱ የጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች ምዕራፍ 15 “ አሁን ደግሞ ወንድሞቼ ሆይ! ያበሠርሁአችሁ የምሥራች ቃል ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ፣ ይህም የምሥራች ቃል እናንተ የተቀበላችሁትና ጸንታችሁ የቆማችሁበት ነው። እኔ ያበሠርሁአችሁን የምሥራች ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ የምድሥራች ቃል ትድናላችሁ፣ አለበለዚያ ግን ያመናችሁት በከንቱ ነው። እኔ የተቀበልሁትን በመጀመርያ ደርጃ ያለውን ነገር ለእናንተ አስተላለፍሁላቹ።” የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር በኤውሮጳ ዋና ዋና ቋንቋዎች ከተነበበ በኋላ ቅዱስነታቸው በሰፊው የዛሬን ትምህርተ ክርስቶስ በጣልያንኛ ቋንቋ አቅርበዋል፣ የሚከተለውንም በእንግሊዘኛ በአጭሩ እአስተምረዋል፦ “ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፦ የክህነት ዓመት መዝጊያ ዕለት እየተቃረበ ስለመሆኑ በዚሁ ዘመነ ትንሣኤ ስለ ክህነታዊ ተልእኮ አንዳንድ አስተንትኖዎችን ማቅረብ እወዳለሁ። በተለይም ካህን በክህነት መዓርጉ ከቤተ ክርስትያን ራስ የሆነው የክርስቶስ ክህነት ጋር በማስተማር በመቀደስ እና በማስተዳደር ተልእኮ ተምሳይነት እንዳለው በተመለከተ መናገር እወዳለሁ። በክህነት ተልእኮአቸው ካህናት ካልአ ክርስቶስ በመሆን በክርስቶስ አካል የክርስቶስ እንደራሴ በመሆን ይሰራሉ። ሦስቱም የካህን ተልእክዎች ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ ዛሬም በካህናቱ እጅ የሚፈጽማቸው ተግባራት ናቸው። ክርስቶስ በካህናቱ አማካኝነት ዛሬም እያስተማረ እየቀደሰና ቤተክርስትያኑን እያስተዳደረ ነው። ከሶስቱ ተልእኮዎች ለጊዝያችን እጅግ አስፈላጊው የመጀመርያው ተልእኮ ማለትም ማስተማር ነው። ካህን ለመስበክና ለማስተማር የተላከው በገዛ ራሱ ስም ሳይሆን ክርስቶስና እሱ የገለጠውን እግዘአብሔር አብን ነው። ማስተማር ሀሳባዊ ይዘት ሳይሆን ተጨባጭ እውነትና የደስታችን የሰላማችንና መንፈሳዊ ዳግመ ልደት ምንጭ የሆነ የኢየሱስ ህያው ምስክርነት ነው።

የካህን የማስተማር ተልእኮ ከካህን የሚጠይቀው መሠረታዊ ነገር ካህን የሚያስተምረውን ከሐዋርይት በውረድ ተዋረድ የተረከበውን ቅዱስ ባህል ጋር በመወሃሃድ በሕይወቱ መመስከር አለበት። ብዙውን ጊዜ ይህ ካለው ባህል ጋር ይቃረናል። የትልቁ የአርስ ቆምስ አብነት በመከተል እያንዳንዱ ካህን በታማኝነት ክርስቶስን እንዲሰብክና ሁላቸውም የመልካሙን እረኛ በእርሱ አማካኝነት እንዲሚሰሙ አድርጎ እንዲናገር ይሁን።” ብለው ካስተማሩ በኋላ በተለያዩ ቋንቋዎች ሲያመሰግኑ በቦታው ተገኝተው የነበሩ የቅዱስ ኤጂድዮ ማኅበር ጓደኞች ካህናትንና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለንግደት መጥተው የነበሩ የአየር ጉዞ አባት ነፍሶችን አመስግነው በዚሁ በካህን ዓመት የክርስቶስ ፍቅር ደስተኛ ምስክሮች እንዲሆኑ ለእያዳንዳቸው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንዲሞላቸው ተመኝተዋል።

በመጨረሻም ቅዱስነታቸው የቻይና የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን አስመልክተው፣ ብዙ የሰው ሕይወት ያጠፋ ብዙ ያቆሰለና ብዙ ንብረት ያወደመ ርዕደ መሬት በቻይና ሕዝብ ላይ ያስከተለውን ሥቃይ በማስታወስ በዚህ ባህርያዊ አደጋ ስለተጐዱት እንደሚጸልዩና በጭግርና በሐዘን ከሚግኘው የቻይና ሕዝብ በመንፈስ ከእርሳቸው ጋር እንዳሉና ከእግዚአብሔር ጽናትን ብርታት እንደሚለምኑላቸው ገልጸው፣ የዓለም ማኅበረሰብ እንዲተባበሩና እንዲረድዋቸው አደራ በማለት ሐዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት የዛሬ ትምህርታቸውን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.