2010-04-12 15:15:57

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የንግሥተ ሰማያት ጉባኤ አስተምህሮ


ውድ ውንድሞቼና እኅቶቼ፦ “የዛሬ እሁድ በጌታ እንደ አንድ ቀን የተፈጠረውን የፋሲካን ሳምንት ይደመድማል፣ የተለየ የሚያደርገውም በጌታ ትንሣኤና ሐዋርያትን ኢየሱስን ከሞት ተነሥቶ ባዩት ጊዜ የተሰማቸው ደስታ ነው። ከጥንት ጀምሮ ይህ ቀን የንጋት ቀን ሲባል ኖሮዋል፣ የመጀመርያ ክርስያኖች በዚሁ ቀን ይጠመቁና ነጭ አዲስ ልብስ ለብሰው ሲያበቁ በስምንተኛው ቀን ያወልቁት ነበር፣ ይህም የዛሬ እሁድ ነው፣ የተከብሩ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ እ.አ.አ ሚያዝያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም የእናቴ ማርያ ፋውስቲና ኮዋልስኪ ቅድስና ባወጁት አጋጣሚ ይህንን እሁድ የመለኮታዊ ምሕረት እሁድ ብለው ሰይመውታል።

በዚች እሁድ የሚነበበው የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20:19-30 በጌታ መለኮታዊ ምሕረትና በጎነት የሞላ ይዘት አለው። ጌታ ኢየሱስ ከትንሣኤ በኋላ በጽርሐ ጽዮን በሩ ተዘግቶ እያለ ሐዋርያቱን እንደጐበኘ ይተርካል። ቅዱስ አጎስጢኖስ ይህንን ፍጻሜ ሲገልጽ እንዲህ ይላላ። የተዘጉ በሮች መለኮታዊው ይኖርበት የነበረውን ሰውነት ቤት ለመግባት አልከሉትም፣ ከድንግል ማርያም ሲወለድ ድንግልናዋን ያልነካ አሁንም በጽርሐ ጽዮን ዝግ በሮች መግባት ቻለ” ይላል። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዓቢይ ደግሞ “መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ በማይበሰብስና ሊዳሰስ በሚችል ሆኖም በክብር ያሸበረቀ አዲስ ሰውነት ቀረባቸው” ይላል። ኢየሱስ ተጠራጣሪውን ቅዱስ ቶማስ እንዲንካው በመጠየቅ የሕማማቱ ምልክቶች ቍስሎቹን ያሳያቸዋል። አንድ ሐዋርያ እንዲጠራጠር እንዴት ይቻላል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የቅዱስ ቶማስ በመልኮታዊ ራእይ መጠራጠር ከሊሎቹ አማኞች ሐዋርያት በይበልጥ ጥቅም ይሰጠናል። በመሆኑም ተጠራጣሪው ሐዋርያ የጌታን ቍስሎች በመንካት የራሱን መጠራጠር ብቻ ሳይሆን የእኛንም ሳይቀር መጠራጠር ይፈውሳል።

ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ መታየት በጽርሐ ጽዮን ብቻ አልተወሰነም፣ ሁላቸው የሰላምና የሕይወት ስጦታን በፈጣሪው መንፈስ እስኪያገኙ ድረስ ከጽርሐ ጽዮን ወዲያም ይሸጋገራል። በዚህም ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ሁለት ጊዜ “ሰላም ከእናንተ ይሁን” ብሎ “አብ እኔን እንደላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” ይላቸዋል። ይህን ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፣ እናንተ የሰዎችን ኃጢኣት ይቅር ብትሉ ይቅር ይባልላቸዋል፣ እናንተ የሰዎችን ኃጢኣት ይቅር ባትሉ ግን ይቅር አይባልላቸውም” አላቸው። ቤተ ክርስትያን በመንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስ እየተረዳች ዘወትር የምትፈጸመው ተልእኮ ይህ ነው፣ የምሥራች ዜና የሆነውን አስደሳች ከእግዚአብሔር ፍቅር የመነጨውን ምሕረት ማወጅ ነው፣ ይህም ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ምዕራፍ 20 ቍ.31 እንደሚለው “ኢየሱስ መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንድታምኑና አምናችሁም በእርሱ ስም የዘላለም ሕይወት እንድታገኙ” ይህ ተጽፈዋል።

በእነዚህ ቃላት ተመርቼ የነፍሳት አረኞች ሁላችሁ የአርስ ቆሞስ ቅዱስ ዮሐንስ ማርያ ቪያነይ አብነት እንድትከተሉ አበረታታለሁ፣ የአርስ ቆምስ ቅዱሱ በጊዜው ለነበሩት ብዙ ምእመናን የጌታን ፍቅራዊ ምሕረት እንዲረዱ በማድረግ ልባችውን ሕይወታቸው እንዲለውጡ አድርገዋል። ዛሬም በዘመናችን የዛ ዓይነት ተልእኮና የፍቅር እውነት ምስክርነትያስፈልጋል። እንዲህ ባለ አኳሃን ዓይኖቻችን ያልዩት ጌታ ግን መጨረሻ የሌው ምሕረቱ ፍጹም በሆነ እርግጠኝነት ያለን ጓደኛነትና ቅርበት ይዳብራል፣፣ የሐዋርያት ንግሥት ለሆነችው ድንግል ማርያም የቤተ ክርስትያንን ተልእኮ እንድትደግፍ እንለምናት በትንሣኤ ደስታ ተሞልተንም እንማጠናት ብለው የንግሥተ ሰማያት ጸሎት አሳርገዋል።

ቅዱስነታቸው ከጸሎቱ በኋላ በቅዳሜ በሩስያ በበረራ ላይ ሳሉ የፖላንድ ፕረሲደንት ለኽ ካዚንሽኪ ባለቤቱ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የፖላንድ ሠራዊት ሊቀ ጳጳስ ያጋጠመውን 90 የሚያህሉ ሰዎች የሞቱበት አደጋን በማስታወስ የተሰማቸውን ጥልቅ ልባዊ ሓዘን ገልጸው በጸሎታቸው እንደሚያስብዋቸው እንዲሁም ለፖላንድ ሕዝብና መንግሥት መጽናናት እንዲያገኙ እንደሚጸልዩ አሳስበዋል።

በመጨረሻም ከትናንትና ወዲያ በቶሪኖ ለትዕንተ ሕዝብ የቀረበው ቅዱስ መግነዝ በማስታወስ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ሆኖ እ.አ.አ. ግንቦት 2 ቀን 2010 ዓ.ም በቦታው ለንግደት እንደሚሄዱ አመልክተዋል። የሚደረገው ንግደት ጥናትና ምርምር የጌታ ሕማማት ምሥጢርን በልባችን በማተም የሓዋርያት ጥልቅ ፍላጎት የነበረው የጌታን ፊት ለማየት ያብቃን ብለዋል።

በመጨረሻም የትናንትና እሁድ የመለኮታዊ ምሕረት ክብረ በዓል በመኖሩ ለሁሉም መልካም ምኞት በመመኘትና ልዩ ቡራኬ በመስጠት የመሐሪ ኢየሱስ ምስል በሁላችን ውስጥ እንዲያሸብርቅ ተመኝተው ዘወትር እንደሚያደርጉት በተለያዩ ቋንቋዎች በማመስገን ሐዋርያዊ ቡራኬ ችረዋል።










All the contents on this site are copyrighted ©.