2010-04-12 15:28:01

የሆሳዕና ሃገረስብከት ምስረታ በታላቅ ድምቀት ተከበረ


የሃገረስብከቱ አዲስ ጳጳስ ቅብዓተ ጵጵስና ተከናወነ

የአዲሱ ሆሳዕና ሀገረስብከት ምስረታ ሚያዝያ 3 ቀን 2002 ዓ.ም በሆሳዕና ከቴድራል በታላቅ ድመቀት ተከብሮ ውሏል፡፡ የሃገረስብከቱ የመጀመሪያ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ወልደጊዮርጊስ ቅብዓተ ጵጵስናም በብፁ ዕ አቡነ ብርሀነየሱስ ሊቀጳጳሳት ከቶሊካውያን ዘኢትዮጵያ እጅ ተከናውኗል፡፡

በዕለቱ ብፁዕ ለቀጳጳሳት ጆርጅ ፓኒኩለም የቫቲካን አምባሳደር በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት፣ክቡር አባ ፓየስ የአሜሲያ (የምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሃፊ፣ ክቡር አባ ሐጎስ ሐይሽ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች፣ ክቡር ዶ/ር ሺፈራው ተ/ማርያም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣ ኩቡር አቶ መለሰ አለሙ የሃዲያ ዞን አስተዳዳሪ፣ አቶ ታደሰ ሮሞ የከምባታ ጠምባሮ ዞን ኣስተዳዳሪ፣ ከመላዋ ኢትዮጵያ፣ ከሆሳዕናና አካባቢዋ የተውጣጡ፣ ካህናት፣ ደናግልና ምዕመናን እንዲሁም የብፁዕነታቸው ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

በበዓሉ ላይም በሆሳዕናና በኣካባቢዋ የስብከተ ወንጌል እንዴት እንደተጀመረና እንደተስፋፋ የሚያብራራ አጭር ታሪካዊ ዘገባ ቀርበዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በስፍራው የተገኙ የመንግስትና የቤተክርስቲያን ከፍተኛ ተቋማት ተወካዮች ሃገረስብከቱ ራሱን ችሎ በመቋቋሙ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በሚያስፈልገው ሁሉ ከሃገረ ስብከቱ ጎን መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ሚያዝያ 4 ቀን 2002 ዓ.ም አዲሱ የሆሳዕና ሀገረስብከት እጩ ጳጳሥ ወደሆሳዕና በገቡበት ወቅት ከሆሳዕና ከተማ ስምንት ኪሎሜትር ርቃ ከምትገኘው በሌሳ ከተማ ጀምሮ መንፈሳዊ ኡደት የተከናወነ ሲሆን የሃዲያ ዞን አስተዳዳሪ፣ የዞኑ ፖሊስ፣ የሆሳዕና ከተማ ካቶሊካውያን፣ ካህናት ደናግልና በርካታ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ አውራ መንገድ ላይ በመውጣት በፖሊስ ሳይረን፣ በፈረስና በወጣት መዘምራን ዝማሬ የታጀበ የክብር አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ የሆሳዕና ሃገረስብከት የኢትዮጵያ 11ኛ ሀገረስብከት ሆኖ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም የወሰኑ መሆናቸውን የቫቲካን የመረጃ አገልግሎት ጥር 12 ቀን 2002 ዓ.ም ማወጁ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት

ማህበራዊና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ








All the contents on this site are copyrighted ©.