2010-04-07 18:34:16

የር.ሊ.ጳ. የዕለተ ሮቡዕ የትምህርተ ክርስቶስ አጠቃላይ አስተምህሮ 07.03.2019


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳጳሳት በነዲክቶስ 16 ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ በቅዱስ ጲጥሮስ አደባባይ አጠቃላይ ሳምንታዊው የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መክፈቻ ጸሎት አሳርገው ከማቲዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28 “ በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ። መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆም፥ ነገርኋችሁ።” የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር በኤውሮጳ ዋና ዋና ቋንቋዎች ከተነበበ በኋላ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምረዋል፦ “ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፦ የዛሬው የተለመደው የዕለተ ሮቡዕ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ አሸብራቂ በሆነው በትንሣኤ ደስታ አሸብርቅዋል። በእነዚህ ቀኖች ቤተ ክርስትያን ኢየሱስ በኃጢኣትና በሞት ላይ በተጕናጸፈው ድል ብሥራት ያገኘችውን ደስታ በመጣጣም ምሥጢረ ትንሣኤን ታከብራለች፣ ይህ ደስታ እስከ ዳግማይ ትንሣኤ ብቻ የሚቆይ የትንሣኤ ሳምንት ደስታ ብቻ ሳይሆን ለሐምሳ ቀናት እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ የሚዘልቅ ደስታ ነው። ከዓርብ ስቅለት ልቅሶና ድንጋጤ እንዲሁም ከቀዳም ሥዑር ፍርሃት የሞላበት ጸጥታ እነሆ የምሥራች ጌታ ከሞት ትነሣ ለስምዕንም ታየ የሚል ብሥራት መጣ። ይህ ለመላው ዓለም የሚሆን ትልቅ ብሥራት ነው፣ ቅዱስ ወንጌልም ከዘመናት ይህንን ብሥራት ከትውልድ ለትውልድ ሲያተባ እኛ ጋ ደረሰ። የክርስቶስ ትንሣኤ ወደር የሌለበት የእግዚአብሔርን ትልቁ ሥራ የሚገልጽ ነው። ምሥጢረ ትንሣኤ ተጨባጭ የሆነ አስደናቂ ፍሬ ያሳየ የእግዚአብሔር ምሥጢር መግለጫ ነው። ልዩና እጅግ ከመጠን በላይ ስለሆነ በአእምሮ ችሎታችንና በዕውቀት አቅማችን ሊገለጽ አይችልም፣ ያም ሆነ ይህ ግን ታሪካዊ ሐቅ ነው። የተመሰከረለትና በታሪክ የተመዘገበ እውነት ነው። ይህ ፍጻሜ የእምነታቸን ርእሰ ነገር በመሆን በእርሱ የምናምንበት መሠረታዊ የክርስትና ይዞታ ነው፣ ለምን እንደምናምን የሚገልጽ ምክንያትም ነው። አዲስ ኪዳን የኢየሱስ ትንሣኤ አፈጻጸምን አይተርክም፣ ከትንሣኤ በኋላ በአካል ያገኙት ሰዎች ዘገባን ይተርካል፣ ሦስቱ ተመሳሳይ ወንጌሎች ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን የሚለው ብሥራት መጀመርያ በመላእክት እንደታወጀ ይነግሩናል፣ ለዚህም ይህ ብሥራት መሠረቱ እግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔር ግን ብሥራቱን ወደ ሁሉ እንዲያዳርሱት ወዲያውኑ ለመልእከተኞቹ በአደራነት ያስረክበዋል፣ ለዚህም ነው መላእክቱ ቀን ሲነጋ ወደ መቃብር ለሄዱት ሴቶች “እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው።” ብለው ያበሰርዋቸው። በዚህም በወንጌሉ በተጠቀሱት ሴቶች አማካኝነት መለኮታዊው መልእክት የትንሣኤው ብሥራት ለሁሉና ለእያንዳንዳቸው ተዳረሰ፣ ብሥራቱን የተቀበሉ ሁሉ ደግሞ በበኩላቸው ይህንን መልእክት በታማኝነትና በቈራጥነት ለሁሉም እንዲያዳርሱ ግዳጅ አላቸው። ይህች መልእክት ጣፋጭ የደስ ደስና ፍስሃ የምትሰጥ ናት።
እርግጥ ነው! ውድ ጓደኞቼ ሃይማኖታችን ቀጣይና ታማኝ በሆነ መንገድ ይህንን የምሥራች ዜና ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ይመሠረታል። ዛሬ ለእግዚአብሔር ጥልቅ ምሥጋና ማቅረብ ያለብን ይህንን እምነት መሠረት በማድረግ ለዘመናት የተቀበሉትን የወንጌል ስብከት በታማኝነት ከትውልድ ለትውልድ ያስተላለፉ ቀድመውን ያለፉ ቍጥር ሥፍር የሌላቸው የምእመናን ሠራዊት ስለሰጠን ነው። የፋሲካ መልካም ዜና መቀበል በጉጉትና በቈራጥነት የመመስከርን ግዴታ ያሸክማል። እያንዳንዱ የኢየሱስ ተከታይ እኛንም ጭምር ምስክር እንዲሆን የተጠራ ነው፣ ይህ ተልእኮ ትክክለኛ ፅኑ እና ከፍ የሚያደርግ ከሞት የተነሣ ጌታ ተልእኮ ስብከተ ወንጌል ነው። በኢየሱስ የሚገኘው አዲስ ሕይወት ዜና በአንድ ክርስትያን ሕይወት መንጻባረቅ አለበት። ሕያውና የሚሠራ መሆን አለበት። ልብንና ኑሮን የሚለውጥ መሆን አለበት፣ ይህ ዜና ሕያው በሆነና ሕይወት በሚሰጥ ክርስቶስ ስለሚንቀሳቀስ ሕያው ነው። ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ መደምደሚያ ላይ “ደቀ መዛሙርቱም በየስፋራው ሁሉ እየሄዱ አስተማሩ፣ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፣ ተአምራትንም የምድረግ ሥልጣን በመስጠት የትምህርታቸውን እውነተኛነት ያጸና ነበር” ይላል።

የሐዋርያቱ ሁኔታ የእኛና ጌታን በመቀበል ደቀ መዝሙር ሆኖ ይህንን መልካም ዜና የሚያበሥር ሁሉ ሁኔታ ነው፣ እኛም ጌታ እንደ ትናንትና እርሱን ከሚመሰክሩ ጋር እንደሚሰራ እርግጠኞች ነን። የጌታ ቃል ተሰብኮ የእውነተኛ ሰላም ፍሬ በምንመለከትበት ጊዜና የክርስትያንና የባለ በጎ ፈቃድ ሰዎች ግኑኝነት ፍትሕን ባለማጓደል ሰላማዊ ውይይት ሌሎችን በማክበር፣ የጋራ በጎ ነገርን በማስቀደም የራስ ጥቅምን በመተው በሚከፈለው መሥዋዕትነት ጌታ ከእኛ ጋር እንደሚሠራ ለማረጋገጥ እንችላለን።

በሌላ በኩል ደግሞ በዓለም ብዙ ሥቃይ ዓመጽና አለመግባባት እንመለከታለን፣ የምሥጢረ ትንሣኤ አስተንትኖ፣ኃጢኣትንና ሞትን በእግዚአብሔር ፍቅር ኃይል የሚያሸንፍ የክርስቶስ አስደሳች ትንሣኤን ማስታወስ፣ ከሞት በተነሣና ተአምራት በማድረግ የትምህርታቸውን እውነተኛነት ያጸና በነበረ ጌታ ያለንን መተማመን እንደገና ለማግኘት ይህ ጊዜ የተመረጠ ጊዜ ነው። የእርሱ ፍቅር በእኛ ላይ እንዲያንጸባርቅ ያደረግን እንደሆነ በእውነት እስከ መጨረሻ ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ክርስቶስ ምስክሮች እንሆናለን። ይህም ማለት በቃለ ወንጌል ተመርተንና እሱ እንደሚያዘን አድርገን በምንናገራቸው ቃላት በበለጠም በምንፈጽማቸው ተግባራት የኢየሱስ ድምፅና ተግባር ሊያንጸባርቅ ከቻለ የእርሱ እውነተኛ ምስክሮች እንሆናለን።

የምሥጢረ ፋሲካን ትርጉም ያጣጣምን ሁላችን ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ጌታ ከዓለም ዳርቻ እስከ ዓለም ዳርቻ በሚልከን ጊዜ እንደ መግደላዊትዋ ማርያም “ጌታን አየሁት” ለማለት መቻል አለብን፣ በዚሁ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣው ክርስቶስ ጋር በሚደረገው ግላዊ ግኑኝነት የማይነቃነቀው የእምነታችን መሠረትና ይዘት እንዲሁም የማይደርቀው ዘለዓለም አዲስ የሆነ የተስፋችን ምንጭ፣ ጽኑና የጋለ ታታሪ ፍቅራችን ይገኛል። ይህንን ይደረግን እንደሆነ ክርስትያናዊ ሕይወታችን ከሙታን ተለይቶ ከተነሣው ክርስቶስ ጋር ይወሃሃዳል፣ ስለዚህ በዚሁ አስደናቂ ፍጻሜ ልባችን እንዲገዛ ይሁን፣ ድንግል ማርያም በጥበቃዋ ትደግፈን፣ የፋሲካ ደስታን እንድናጣጥምና ለሁላቸው ወንድማሞቻችንና እኅቶቻችን እንድናዳርሰው ዘንድ ትርዳን፣ እንደገና መልካም ፋሲካ ለሁላችሁ፣” በማለት ትምህርታቸውን ደምድመው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አብረዋቸው ለነበሩና በተለቪዥንና በረድዮ ለተከታተልዋቸው ምእመናን በተለያዩ ቋንቋዎች አመስግነው ሓዋርያዊ ቡራኬ ሰጥተዋል።
All the contents on this site are copyrighted ©.