2010-04-06 18:15:26

በመላው ኢትዮጵያ የትንሳኤ በዓል በደማቅ ሁኔታ ይከበራል


ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል

ከትላንት በስቲያ መጋቢት 23 ቀን 2002 ዓ.ም በዕጽበተ እግር የተጀመረው የ2002ዓ.ም የብርሃነ ትንሳኤ በዓል ትላንት በበዓለ ስቅለት የስግደት ስነስርዓት ቀጥሎ ውሎ ዛሬ ከማለዳው 12፡30 የቅዳሜ ስዑር የቄጤማ በዓል በመላው ሃገሪቱ ሲከናወን አርፍዷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ መጋቢት 23 ቀን 2002 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ካቶሊካውያን ዘኢትዮጵያ ለመላው ኢትዮጵያውያንና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ የ2002 ዓ.ም የብርሃነ ትንሰኤ በኣልን አስመልክተው የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ይኸው መልዕክታቸው ከዛሬ ቅዳሜ ምሽት ጀምሮ በኢትዮጵያ በሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን በሙሉ ለህዝብ ይተላለፋል፡፡

ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት መልካም የትንሳኤ በዓልን ከተመኙ በኋላ የአገራችን ዜጎች በቻልነው ሁሉ የተቸገሩ ወገኖቻችንን እንድናስብ፣ በአካባቢያችን የታመሙትን በመጠየቅና በመንከባከብ በተለይ በኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ የታመሙትን፣ አቅመ ደካሞችን፣ ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡ ህጻናትንና የጎዳና ተዳዳሪዎች በዓሉን በደስታ ማክበር እንዲችሉ እንደየአቅማችን ስለእግዚአብሄር ብለን እንድንረዳቸው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የተቸገሩትን የመርዳት ባህላችንም በታላላቅ በዓላት ጊዜ ብቻ መወሰን እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም የአገራችን ዜጎች ጤናቸውን በመጠበቅ፣ ከሙስና በመጽዳት በልማት ሥራ ላይ በመሳተፍ የተያዘውን ለውጥ አጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም በመጪው ግንቦት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን አራተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ አስመልክተው ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲሆን ምዕመናን ሁሉ ጸሎት እንዲያደርጉና በምርጫው በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በተለይም በየቤቱና በየሆስፒታሉ ላሉ ህመምተኞች፣ ከቤተሰቦቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች ርቀው ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ በማረሚያ ቤት ለሚገኙ ወገኖች ሁሉና ለአገር ደህንነት በጠረፍና በድንበር ጥበቃ ላይ ለተሰማሩ ሁሉ እንኳን ለ2002 ዓ.ም የብርሀነ ትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

ዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2002 ዓ.ም. ዕኩለ ሌሊት የብርሃነ ትንሳኤ ቅዳሴ በመላው ኢትዮጵያ የሚደረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት

ማህበራዊና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ 








All the contents on this site are copyrighted ©.