2010-03-01 19:12:27

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ(28.02.2010)


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንት ረፋድ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በብዙ ሺ ለሚገመቱ ምእመናን የተለመደውን የእሁድ ጉባኤ አስተምህሮ አቅርበዋል። ትምህታቸውም እንደሚከተል ነበር።

“ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፦ በጾመ አርባ መባቻ ላይ ዘወትር በቫቲካን የሚደረገው ሱባኤ ትናንትና በሐዋርያዊ አደራሽ ተፈጽመዋል። በሐዋርያዊ አገልግሎቴ ከሚተባበሩኝ ኩርያ ሮማና የቅድስት መንበር ተቅዋሞች ብፁዓን አበው የአስተንትኖና የጸሎት ጊዜ አሳልፈናል። ቤተ ክርስትያን ባወጀችው የክህነት ዓመት ውስጥ ስላለን ስለ ክህነት ጥሪ አስተንትነናል። በዚሁ የሱባኤ ጊዜ በመንፈስ በመተባበር በጸሎት የሸኙንን ሁሉ አመሰግናለሁ።

በዛሬው የጾመ አርባ ሁለተኛ እሁድ የዕለቱ ቃለ እግዚአብሔር ስለ በዓለ ደብረ ታቦር የጌታ ፊት መለወጥ ይናገራል። የሉቃስ ወንጌል ከፍጻሜው በኋላ ወዲያውኑ ይህንን ጥሪ ያቀርባል፣ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።(ሉቃ 9:23) ይህ ልዩ ፍጻሜ ኢየሱስን ለመከተል የሚያበረታታ ነው።

ቅዱስ ሉቃስ ስለ ደብረ ታቦር ፍጻሜ ሲናገር ምን እንደተፈጸመ ያወራል እንጂ ስለ ትርጓሜው አይናገርም። የኢየሱስ ገጽ እንደተወጠና ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ እንደሆነ የሕግና የነቢያት ምልክት የሆኑ ሙሴና ኤልያስ እዛ ከእርሱ ጋራ አብረው መገኘታቸውን ይተርካል። ከኢየሱስ ጋር ወደ ተራራው የወጡ ሦስቱ ሐዋርያት እንቅልፍ ከብደዋቸው እንደተኙ፣ ይህም አስደናቂ መለኮታዊ ክንዋኔዎችን እያዩ የማይረዱ ሰዎችን ያመለክታል። በግልጸቱ ክብደት ልፍስፍስ ብለው ሳሉ ነው ጴጥሮስ ያዕቆብና ዮሐንስ የኢየሱስን ክብር ያዩት። ሙሴና ኤልያስ ከጌታ በተለዩ ግዜ ጴጥሮስ መናገር ይጀምራል፣ ሲናገርም ደመና መጣና እርሱንና ሌሎችን ጋረዳቸው፤ ይህ ደመና ለየት ያለ ነው፣ እስራኤላውን በምድረ በዳ በሚጓዙበት ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ እዚህም እየጋረደ የእግዚአብሔርን ክብር የሚያሳይ ደመና ነው። ዓይኖቻቸው ለማየት አይችሉም ነበር፣ ጆሮአቸው ግን ከደመናው የሚመጣውን ድምጽ ሊሰማ ቻለ፣ ከደመናውም። የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ ተሰማ።

ሐዋርያቱ በተለወጠ የኢየሱስ ፊት ወይም በተብለጨለጨው የኢየሱስ ልብስ ፊት ወይም በመለኮታዊው የደመና ህልውና አይደሉም ያሉት። በወንጌሉ ምዕ 9 ቍ 36 “ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ።” ይላል። ኢየሱስ በአባቱ ፊት ሲጸልይ ብቻውን ነበር፣ እግዚአብሔርም ለሐዋርያትና ለቤተ ክርስትያን የሰጣቸው ነገር ቢኖር ኢየሱስን ብቻ ነው። ይህም ማለት ለሚደረገው መንፈሳዊ ጉዞ ኢየሱስ በቂ ነው ለማለት ነው። መሰማት ያለበት ድምጽ እርሱ ብቻ ነው፣ መከተል ያለበትም እርሱ ብቻ ነው፣ ወደ ኢየሩሳሌም በመውጣት ሕይወቱን ስለእኛ የሚሰዋ ኢየሱስ ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው አንድ ቀን እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤  እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።”ምዕ: 3:21።

አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፣ የሚለው የቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር በጌታ ኢየሱስ መጽናናት በምናገኝበት ጊዜ የምንገልጸውን ፍላጎት ይገልጻል። በዓለ ደብረ ታቦር የሚያስተምረን ክስተት ግን ሌላ ነው፣ እግዚአብሔር በሕይወታችን ኑሮ ውስጥ የሚሰጠን ደስታዎች የመጨረሻ ግባችን ሳይሆኑ በዚሁ በምድር በምናደርገው ንግደት መምርያ ሕጋችን ኢየሱስ ብቻ ቃሉም ኑሮአችንን የምንመዝንበት መሣርያ እንዲሆን የሚሰጠን ብርሃን ነው።

በዚሁ ምርጥ የጾም አርባ ዘመን ወንጌልን ጠለቅ ባለ መንፈስ እንድታስተነትኑ አደራ እላለሁ። በዚሁ የካህን ዓመት እረኞቹ ሃሳባቸውንና ሕይወታቸውን እስከ መለወጥ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያውቅትና እንዲወዱት በእርሱ እንዲገዙ እመኛለሁ። ድንግል ማርያም ከጌታ ጋር የምናሳልፋቸውን ግዝያት በእውነት እንድንኖራቸውና እርሱን ከዕለት ወደ ዕለት በደስታ እንድንከተለው ትርዳን፣ አሁን በመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወደ እርስዋ እንማጠን ሲሉ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳርገዋል።

ቅዱስነታቸው ከጸሎቱ በኋላ ባቀረቡት ንግግር በዚሁ ሳምንታት በኢራቅ የሚካሄደው የክርስትያን ስደት በተለይም በመሱል ከተማ ለተገደሉት ክርስትያን በማስታወስ ጥልቅ ሐዘናቸውን ገልጸዋል። በሱባኤው ግዜ ስለዚህ ጉዳይ መጸለያቸውና ዛሬም ስለ ዒራቅ ክርስትያኖች ሰላምና ደህንነት ሁላችን በጸሎት እንድንተባበራቸው አደራ ብለዋል።

እንዲሁም በቺለ ደቡብ አመሪካ በርእደ መሬት ለተጐዱት ወገኖች የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ በጸሎትና በመንፈስ አብርዋቸው እንዳሉ ገልጠዋል። የግብረ ሠናይ ድርጅቶች በተለይም የአብያተ ክርስትያን ግብረ ሠናይ ድርጅቶች የተቻላቸውን ያህል እንዲያበረክቱ አደራ ብለዋል።

በመጨረሻም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን በተለያዩ ቋንቋዎች አመስግነው ትምህርታቸውን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.