2010-02-19 16:21:08

ጾም እና ርሊጳ በነዲክቶስ፡


“የገዛ ራስህን ድካም መገንዘብ ከሁሉ መቅደም ያለበት አግባብ ነው”፣ ይህን ያሉት ቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ ከትናንትና ወዲያ ሮማ ላይ በሚገኘው የቅድስት ሳቢና ባዚሊካ በሥርዓተ ላቲን የጾም ጅማሬ የቅዳሴ ሥርዓተ በመሩበት እና ባሰሙት ስብከት ነው። አያይዘውም ሰው ዳግም ፍትሔኛ መሆን የሚችለው በክርስቶስ በኩል በተገለጠው የእግዚአብሔር ፍትህ እና ምሕረት መሆኑ አስገንዝበዋል።

በዚሁ ጾመ አርባ በምንጀምርበት ግዜ አንድ ፍትሐዊ ኅብረተ ሰብ ለመገንባት እና የሰው ግርማ የጠበቀ ሕይወት ለማሳለፍ ቤተክርስትያን ግላዊ እና ማኅበረ ሰባዊ መቀየር ወይም መለወጥ እንደሚያሻ ትጠይቃለች ብለዋል። የሰው ልጅ በየዕለቱ በሚያጋጥሙት አሉታዊ ነገራት ቢሰላችም አሁን ካለው የተሻለ ፍትሕ ያለው ዓለም እንደሚመኝ አመልክተዋል።

በመቀጠል ለሰው ልጅ ድኅንነት በሞተ እና በተነሣ ክርስቶስ ሰው ከሚሰጠው ፍትሕ የተለየ ግልጸት መለኮታዊ ፍትሕ መከሰቱ አስረድተዋል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፍትሕ የፍቅርና የምሕረት ፍትሕ በመሆኑ ዘለዓለማዊ ፍትህ እንደሆነ ቅድስነታቸው ገልጸዋል።

ቅድስነታቸው ቀጥለው ፡ በጾም ግዜ መጾም መጸለይ እና ማስተንተን፡ ከልብ የፈለቁ እና ከልብ የመጸጸትን ምልክት ከሌላቸው በእግዚአብሔር ዘንዳ ተቀባልነት እንደሌላቸው አስገንዝበዋል። ሐቅነት የሌለው እና ተጸጽቶ የመቀየር ውሳኔ የሌለው ጾም እና ተጋድሎ ከንቱ ውእቱ ብላሽ እንደሆነ ያመለከቱት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክት ከሁሉም የባሰ ደግሞ ለይምሰል የሚድረግ ጸጸት እና ገቢራዊ የማይሆን ከሆነ ራስህን ማታለል እና ፋይዳ ቢስ መሆኑ ገልጠዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ የንባበ መለኮት በሰል መሆናቸው የሚታወስ እና ጥልቅ የቤተክርስትያን ትምህርት ለዓለም ምእመናን እያበረከቱ መሆናቸው የማይዘነጋ ሲሆን አያይዘው፡ ክርስቶስ በምድረ በዳ ለአርባ ቀናት ያደረገው ቁይታ ፡ ሰው በጦም ግዜ ምን ማድረግ እንዳለበት በምን ዓይነት እኳኀን መጦም እንዳለበት ያመላክታሉ ብለዋል።

በእግዚአብሔር ፍቃድ ክርስቶስ በምድረ በዳ ሲቆይ በፍቃዱ የጠላት ጥቃት ሰለባ ለመሆን ስለፈለገ ነው ይሉና እና ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ አዳም ፈተና ላይ ወድቆ ሞትም የሞት ጅማሬ መሆኑ አመልክተው፡ ክርስቶስ ለጠላት ሲጋለጥ የሃከሌ ኩሉ እግዚአብሔር ፍቅር እና ፍላጎት ለማሟላት መሆኑ አስረድተዋል። ሆኖም የክርስቶስ ትንሳኤ ተሳታፊ ለመሆን ክርስቶስ በምድረ በዳ የተወጣው ተጋድሎ በመከተል ሞትን ማሸነፍ እዚህ ላይ ሞት ማለት ዘለዓለማዊ ጥፋትን ነው እና ለማሸነፍ እንደሚቻል አስገንዘበዋል።

በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው ሰው በፈጸመው ሐጢአት የራሱ ንጽሕና እንዳጠፋ የጠቀሱት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ፡ በእግዚአብሔር መሐሪነት እና ሐቀኛ ፍትህ ንጽሕናውን መልሶ ለመቀዳጀት እንደሚችል ገልጸዋል።

ቅድስነታች ስበከታቸው በማያያዝ እግዚአብሔር ሰውን እንዲጠፋ በሐጢአቱ ተጨማልቆ እንዲኖር ስላልፈለገ ምሕረቱን ሰጠው ጸጋውም አፈሰሰለት። ጾም አመለካከታችን አስተሳሰባችን እንድናሰፋ ፊታችን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንድናቀና እና በዚች ዓለም እንግዶች መሆናችንን ያስረዳናል ብለዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ፡ ቅዱስ አባታች ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ ፊታችን መጋቢት ወር አስራ አራት ቀን ሮማ ውስጥ የምትገኘው ወንጌላዊት ሉተራዊት ቤተክርስትያን እንደሚጐበኙ የቫቲካን መግለጫ አስታውቀዋል። የቤተክርስትያኒቱ ክቡር ቄስ ጂንስ ማርቲን ክሩሰ እንደገለጡት፡ የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት ለኤኩመኒካዊ ለክርስትያን አንድነት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል ፡ ወንጌላዊት ሉተራዊት ቤተክርስትያንም ጉብኝቱ በጉጉት ትጠባበቀዋላች ።







All the contents on this site are copyrighted ©.