2010-01-20 17:00:28

የር.ሊ.ጳ. ጉባኤ አስተምህሮ 20.01.2010


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳጳሳት በነዲክቶስ 16 ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ የተለመደውን አጠቃላይ ሳምንታዊው የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መክፈቻ ጸሎት አሳርገው ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ከቍ.44-49 “እርሱም። ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። እናንተም ለዚህ ምስክሮች” የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር በኤውሮጳ ዋና ዋና ቋንቋዎች ከተነበበ በኋላ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምረዋል።

“ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፦ የዛሬ የዕለተ ሮቡዕ ጉባኤ አስተምህሮ ለክርስትያን አንድነት በምንጸልይበት ሳምንት ይካሄዳል፣ በዚሁ ሳምንት የጌታ ተከታዮች እርስ በእርሳቸው በመከፋፈል የሚከሰተውን ትራጀዲ ለማስተንተንና ከጌታ አብረው “ሁላቸው አንድ እንዲሆኑ አለም እንዲያምን” (ዮሐ.17፣21) የሚለውን ጸሎት ለማሳረግ ነው፣ ለዚህ ዓመት የተመረጠው አርእስት “የእነዚህ ነገሮች ምስክሮች እናንተ ናችሁ፣” ሉቃ.24.48 በክርስትያን አንድነትና በስብከተ ወንጌል ያለውን ግኑኝነት የሚያጠነክር ነው፣ ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት ዘመናዊው የክርስትያን አንድነት እንቅስቃሴን የጀመረው የኤድንብራ ጉባኤን ያሳሰበውም ይህ የክርስትያኖች መከፋፈል ነበር።

በየዕለቱ ዓለማዊነት እየተስፋፋበት ላለው ለዛሬው ኅብረተሰብ በጋራ እምነት የተመሠረተ ለኢየሱስ ክርስቶስ የጋራ ምስክርነት መስጠት አንገብጋቢ አስፈላጊነት አለው፣ እንዲሁም በተለያዩ ክርስትያኖች መሀከል በወንድማማችነት የተመሠረት መተባበር፣ ውይይት እና በሚለያይዋቸው ነጥቦች በጥልቅ ማስተንተን ያስፈልጋቸዋል። በዚሁ ሳምንት ሁላችሁ በእነዚህ ሐሳቦች በጸሎት እንድትተባበሩኝ እጠይቃለሁ፣ ባለፈው ዓመት የክርስትያን አንድነት እንቅስቃሴ ስላደረገው ዕድገት እግዚአብሔርን እያመሰገን የዘመናችን ክርስትያኖችን በአንድነት እያደጉ ልብን የሚነካና የሚለውጥ ከሙታን ተለይቶ ለተነሣው ክርስቶስ ምስክርነት እንዲሰጡ አደራ እላለሁ።” በማለት ትምህርታቸውን ደምድመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.