2010-01-04 15:37:37

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ 03.01.2010


ቅ.ኣ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናንና ነጋድያን የዕለቱን ቃለ ወንጌል በመጥቀስ “የሰው ልጅ ታሪክ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ጥበብ ስለሚመራ ትርጉም አለው” በማለት ታሪካችን አቅጣጫና ዓላማ ያለው እንጂ በዘፈቀደ የሚሄድና በጥንቈላዊና በምጣኔ ሃብታዊ ትንቢቶች የሚወሰን አለመሆኑን አብራርተው የመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት አሳረጉ።

ትምህርታቸውም እንደሚከተለው ነው፣ ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ

በዚሁ የመጀመርያ ዓመት እሁድ ከልደት በኋላ ሁለተኛ ሰንበት እንደገና ለሁላችሁም በጌታ መልካም ምኞቴን ሳቀርብ ደስ ይለኛል። በእያንዳንዳችን ቤተሰብ ዕለታዊ ችግር እንዳለ ሁሉ በዓለማችንና በቤተ ክርስትያናችን ችግሮች ኣይጠፉም። ሆኖም ግን እግዚአብሔር ይመስገን ምንም እንኳ ጠቃሚ ቢሆኑም በማይታመኑ አዋቂዎችና የሥነ ምጣኔ ሃብት ሊቃውንት በሚያቀርቡልን ትንቢቶች ላይ ተስፋችን ኣንጥልም። ተስፋችን እግዚአብሔር ነው፣ ይህም ተጨባጥ በሌለው ባዶ ወይም የወል ተስፋ ወይንም ደግሞ በጭፍን ዕጣ ፈንታና ዕድል የሚዋልል ተስፋ አይደለም። እኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ በፍጽምና በመገለጥ እንደኛ ሰው ሆኖ በመሃከላችን በመኖርና ታሪኩን በማሳተፍ የፍቅርና የሕይወት ወደ ሆነው መንግሥቱ ሊመራን መልካም ፍላጎቱን በገለጠልን እንተማመናለን። ለሰው ልጅ ተስፋዎቻችን ይህች ትልቅ ተስፋ ሕይወት ትሰጣለች ኣንዳንዴም ታስተካክላለች።

የዛሬው ቃለ እግዚአብሔር፣ ሦስቱም ንባባት ይህንን ክስተት ያብራሩልናል። ንባባቱ እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሃይማኖቶች እንደሚመሰክሩት አባትም ነው፣ ቅዱስ ጵውሎስ ወደ ኤፈውሶን በጻፈው መልእክት “ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንድንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።  በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን” ይላል ለዚህም ልንረዳው በማንችለው ምሥጢረ ሥጋዌ እንደኛ ሰው የሆነው፣ ቅዱስ ዮሓንስም በወንጌሉ ምዕራፍ አንድ ቍ.14 ላይ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ ይላል።

የቃለ እግዚአብሔር ምሥጢረ ሥጋዌ በብሉይ ኪዳን የተዘጋጀ ነበር በተለይም መለኮታዊው የእግዚአብሔር ጥበብ በሙሴ ሕግ ተገልጦ ነበር፣ መጽሓፈ ሲራክ በ24ኛው ምዕራፍ ቍ.8 ከዛ በኋላ ሁሉን የፈጠረ ትእዛዝ ሰጠኝ፣ አዎ የወለድኝ ቤቴን የምሠራበት ቦታ ወሰነልኝ፣ ኑሮህ ከያዕቆብ ልጆች ይሁን ርስትሽ ደግሞ ከእስራኤል ልጆች ይሁን” ይላል።

በኢየኡስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ሕግ ሕያው ምሥክር ሆነ ይህም በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በአንድ ሰው ልብ የተጻፈ ነው፣ በእርሱም የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፣ መልእክተ ጳውሎስ ወደ ቆላስይስ ሰዎች ምዕ 2 ቍ.9 ተመልከት። የተከበራችሁ ጓደኞቼ፣ የሰው ልጅ ተስፋ እውነተኛነት ምስክር የሚሆነን ይህ ነው፣ ታሪክ በእዚአብሔር ጥበብ የሚመራ ስለሆነ ትርጉም አለው፣ ነጻነት የሚሰጥና ነጻነት የሚጠይቅ ፍቅር ዕቅድ ስለሆነ፣ መለኮታዊው የፍቅር ዕቅድ በገዛ ራሱ የሚካሄድ ኣይደለም። በእርግጥም የእግዚአብሔር መንግሥት ይመጣል፣ የክርስቶስ መምጣት ምስጋና ይድረሰውና የእግዚአብሔር መንግሥት ደርሰዋል፣ የጥንተ ጠላታችን መጥፎ ኃይልም ተሸንፈዋል። ይህንን የእግዚአብሔር መንግሥት እያንዳንዱ ወንድና ሴት ከቀን ወደ ቀን እንዲቀበለው ኃላፊነታችን ነው፣ እያንዳንዳችን ኃላፊነታችን በብቃት ለመወጣት ከተሰጠን የእግዚአብሔር ጸጋ ጋር የተባበርን እንደሆነ አዲሱ የ2010 ዓመትም ከመላ ጎደል መልካም ዓመት ይሆናል።

ይህንን መንፈሳዊ ዝንባሌ ለመማር ሐሳባችንን ወደ ድንግል ማርያም እናውለው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ከእርስዋ ሥጋ የወሰደው ሳትፈቅድለት አይደለም፣ ጌታ ከእኛ ጋር በመተባበር ወደ ምድረ ተስፋ አንድ እርምጃ ለመውሰድ በሚፈልግበት ጊዜ መጀመርያ የልባችንን በር ነው የሚያንኳኳው፣ በትናንሽና በትላልቅ ምርጫዎች የእኛን አብየትና እሺ ማለትን ይጠብቃል። የሕይወት ፈተናዎችና ሥቃዮች የእግዚአብሔርን የፍትሕና የሰላም መንግሥት ቶሎ እንዲመጣ ያድርጉት ዘንድ፣ እመቤታችን ማርያም የእግዚአብሔርን ፈቃድ በትሕትናና በጽናት ለመቀበል ትርዳን” ብለው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳረጉ።

ጸሎቱን ካሳረጉ በኋላ ከጣልያን አገርና ከተለያዩ ክፍለ ዓለም ከቅዱስነታቸው አብረው ለመጸለይና ትምህርታቸውን ለመስማት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን በተለያዩ ቋንቋዎች አመስግነው ሓዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት የዕለቱን ጉባኤ አስተምህሮ ደመደሙ።








All the contents on this site are copyrighted ©.