2009-12-28 17:35:31

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ


ቅ.ኣ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናንና ነጋድያን የቅድስት ቤተ ሰብ በዓልን አስመልክተው “የቅድስት ሥላሴ አምሳል የሆነውን ቤተ ሰብን እንደግፍ - በዘመናችን ካሉ ጥቃቶችም እንከላከልለት” በማለት ቤተ ሰብን መርዳትና ማደራጀት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለው የመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት አሳረጉ።

ትምህርታቸውም እንደሚከተለው ነው፣ “የተከበራችሁ ወንድሞቼና እኅቶቼ የዛሬው እሁድ የቅድስት ቤተ ሰብ ዕለት ነው። ራሳችንን መልአኩ ካበሰራቸው በኋላ በቀጥታ ወደ ኢየሱስ የተወለደበት ዋሻ በመሮጥ እመቤታችን ማርያም ቅዱስ ዮሴፍና በግርግም የተኛውን ኢየሱስ ሕፃንን ያገኙ ከቤተ ልሔም እረኞች ጋር ማስመሰል እንችላለን። ይህንን ትዕይንት ለማስተንተን ቀስ ብለን ትርጉሙን እናስብ፣ የኢየሱስ ልደት የመጀመርያ ምስክሮች የሆኑ እረኞች ኢየሱስ ህጻንን ብቻ ኣልነበረም ያገኙት፣ እፊታቸው የተደቀነው ትንሽ ቤተ ሰብን ነው ያገኙት፣ እናት ኣባትና ያኔ የተወለደ ጨቅላ ያካተተ ቤተ ሰብ ነው ያገኙት፣ እግዚአብሔር በአንድ ሰብአዊ ቤተ ሰብ በመወለድ ራሱን ሊገልጥ ወደደ፣ ስለዚህ ቤተ ሰብ የሥሉስ ቅዱስ እግዚአብሔር አምሳል ሆነ፣ ቅድስት ሥላሴ ውህደት አንድነት ፍቅር ነው፣ ምንም እንኳ በፍጡርና በመለኮታዊው የእግዚአብሔር ምሥጢር ልዩነት ቢኖርም ቤተ ሰብ አእምሮአችን ሊረዳው የማይችለውን የእግዚአብሔር ምሥጢርን ለማስተንተን ይረዳናል። በእግዚአብሔር ኣምሳል የተፈጠሩት ባልና ሚስት በምሥጢረ ተክሊል አንድ አካል ይሆናል፣ ይህም አዲስ ሕይወት የሚወልድ የፍቅር አንድነት ነው። የሰው ልጅ ቤተ ሰብ የእግዚአብሔር ምልክት ወይም ኣምሳልም ነው፣ በቅድስት ሥላሴ መሀከል ያለው ውስጠ አካላዊ ፍቅርና የዚህ ፍቅር ልምላሜ ቋሚ ምልክት ነው።

የዛሬው ሥርዓተ ኣምልኮ ንባብ ኢየሱስ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ ወላጆቹ እንደ በዓሉ ሥርዓት በያመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ስለነበር ነበር ይዘውት ወደ ኢየሩሳሌም እንደወጡ ሲመለሱ ሳሉ ዮሴፍና ማርያም ሳያውቁ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም መቅረቱንና ለሶስት ቀናት ያህል ጨንቆአቸው ሲፈልጉት ኖረው በመጨረሻ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፣ ለምን እንደዛ እንዳደረገ እናቲቱ በጠየቀችበት ወቅት ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲሚገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው። በዚሁ የወንጌል ክፍል ብላቴናው ኢየሱስ በእግዚአብሔርና በቤተ መቅደሱ ቅናት የተሞላ ይመስላል። ኢየሱስ ለአባቱ ቤት ጉዳዮች ፍቅርን ከማን ቀመሰው ብለን የጠየቅን እንደሆን እርግጥ ነው ከእግዚአብሔር አባቱ ጋራ የጠለቀ ግኑኝነት ነበረው፣ ግን ተወልዶ ባደገበት ባህል ጸሎትንና የወላጆቹ ወግና ልማድ እንዲሁም ቤተ መቅደሱን ማፍቀር ከወላጆቹ ነው የተማረው። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ በቤተ መቅደስ እንዲቀር የወሰነበት ምክንያት ከሰማያዊ አባቱ ጋር ባለው ፍቅር ቢሆንም ከድንግል ማርያም ከቅዱስ ዮሴፍ ባገኘው ትምህርትም ነው። እዚህ ላይ የትምህርተ ክርስቶስን ትርጉም መረዳት እንችላለን፣ ትምህርተ ክርስቶስን ማስተማር ሁል ጊዜ በእግዚአብሔርና በቤተ ሰብ መተባበር የሚደረግ ነው፣ ክርስትያናዊ ቤተ ሰብ ልጆች የእግዚአብሔር ሥጦታና ዕቅድ መሆናቸውን ይረዳሉ። እንደ የራሳቸው አድርገው ሊቆጥርዋቸው ይችላሉ ግን የእግዚአብሔር ዕቅድ መኖሩን ሳይዘነጉ በጥሪአቸው መሠረት ለትልቁ ነጻነት ማስተማር አለባቸውም ይህም የእግዚአብሔር ፍቃድ ለመፈጸም እሺ ማለት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፣ የዚህ እሺ የማለት አብነታችን ድንግል ማርያም ናት፣ የመላው ዓለም ቤተሰቦችን ለእርስዋ በማማጠን የቤተ ሰቦች ክቡር ተልእኮ ስለሆነው ስለ ልጆችን ማስተማር ተልእኮ እንጸልይ።” ብለው በማድሪድ ለቅድስት ቤተ ሰብ በዓል ለተሰበሰቡት በቀጥታ በተለ ቪድዮ መልእክት ካስተላለፉ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳርገዋል።

ጸሎቱን ካሳረጉ በኋላ ከጣልያን አገርና ከተለያዩ ክፍለ ዓለም ከቅዱስነታቸው አብረው ለመጸለይና ትምህርታቸውን ለመስማት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን በተለያዩ ቋንቋዎች አመስግነው ሓዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት የዕለቱን ጉባኤ አስተምህሮ ደመደሙ።








All the contents on this site are copyrighted ©.