2009-12-27 18:49:00

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የልደት መልእክት


ኡርቢ ኤት ኦርቢ - ከተማዋና መላው ዓለም በሌላ አነጋገር ለሮማና ለመላው ዓለም በልደት ቀን የሚያስተላልፉት የተለመደው የልደት መልእክት ዛሬ እኩለ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አስተላልፈዋል።

“ውድ በሮማና በመላው ዓለም የምትገኙ እግዚአብሔር የሚያፈቅራችሁ ወንዶችና ሴቶች፣ ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፣ የሮማዊው አኰቴተ ቍርባን መግቢያ “ጌታ ተወለደልን ብርሃን በላያችን ሊያንጸባርቅ ነው” ይላል። ስብሓተ ነግሁ የሌሊቱን ማለፍና ቀን መቅደዱን ከቤተ ልሔም ዋሻ የሚፈነጥቀው ብርሃን በእኛ ላይ መንጸባረቁን ይገልጻል። ቅዱስ መጽሐፍና ሥርዓተ አምልኮው ስለ ባህርያዊ ብርሃን ኣይደለም የሚናገሩን፣ ለእኛ በእኛ ላይ ስለሚያቶኵር ስለ ልዩ ብርሃን ይናገራል፣ ለእኛ በቤተልሔም ሕጻን ተወልዶልናል፣ ይህ “እኛ” የሚለው ተውላጠ ስም፣ በተስፋ የመድኅኔ ዓለምን ልደት የጠበቀውና ዛሬ የበዓለ ልደት መሠረታዊ ምሥጢርና ትርጉም ለሚያከብረው፣ በኢየሱስ የሚያምነውን ትልቁን ዓለም አቀፍ ቤተ ሰብ፣ ቤተ ክርስትያንን ያመለክታል።

በመጀመርያ ኢየሱስ የተወለደበትን የቤተ ልሔምን ግርግም ሳይገለጥ ይህ “ለእኛ” የሚለው ለሰው ዓይን ስውር ነበር። የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል እንደሚተርከው ከማርያምና ዮሴፍ ጋር መላእክት ካበሰርዋቸው በኋላ ወደ ዋሻው የመጡትን እረኞችን ይጨምራል። የልደት የመጀመርያ ብርሃን በሌሊት ነዶ ብርሃን እንደሰጠ እሳት ነው። አከባቢው ሁሉ ጨልሞ ሳለ ከዋሻው እውነተኛ ብርሃን ፈነጠቀ፣ ይህ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ም.1 ቍ.19 እንደሚለው “ለሰው ሁሉ ብርሃን የሚሰጥ እውነተኛ ብርሃን ነው”። ይህ ሁሉ እግዚአብሔር በድኅነታችን ታሪክ እንደሚያደርገው በየዋህነትና በሥውር ነው የተፈጸመው። ሰፊ ቦታዎችን በብርሃን እንዲያሸብርቁ እግዚአብሔር ትናንሽ ቀንደሎችን ማብራት ይወዳል፣ ብርሃኑን በተቀበሉበት አከባቢ ይዘቱ እውነትና ፍቅር ይሆናል፣ ልባቸውን በመክፈት ወደው በነጻነት ዕፁብ ድንቅ የሆነውን ብርሃንን የተቀበሉት ራሳቸው የብርሃን ምንጭ በመሆን ከልባቸውና ከአእምርአቸው ያልናቸው እውነትና ፍቅር እንደ ቀስተ ደመና በዙርያቸው ያሸብርቃሉ። የቤተ ክርስትያን ታሪክ እንዲህ ነው፣ ጉዞዋን በትሑቱ የቤተ ልሔም ዋሻ ጀመረች፣ ከዘመናት በኋላ ለሰው ልጅ ዘር የብርሃን ምንጭ ሆነች። ዛሬም እግዚአብሔር በኢየሱስ የደኅንነትና የነጻነት ምልክትና እውነት ለማየት የሚችሉትን የሰው ልጆች ከሁሉም እየጠራ በጨለማው ዓለም እሳቱን በማብራት “ለእኛ” ያልናትን በክርስቶስ ለምታምነው ቤተ ክርስትያን ለመላው የሰው ልጅ እያሰፋ ነው።

የእግዚአብሔርን ፍቅር የምትቀበል ቤተ ክርስትያን ባለችበት ቦታ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ አጋጣሚዎች ሳይቀር ሁል ጊዜ የክርስቶስ ብርሃን ያሸብርቃል። ቤተ ክርስትያን እንደ ድንግል ማርያም ራስዋ እንደ ስጦታ የተቀበልችውን የሰው ልጅ ዘርን ከኃጢአት ባርነት ነጻ ለማውጣት የመጣውን ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስን ለዓለም ታበርክታለች። እንደ ድንግል ማርያም ኃይልዋ ሕጻኑ ስለሆነ ቤተ ክርስትያንም አትፈራም። ለገዛ ራስዋ አትይዘውም፣ በየዋህ ልብ እሱን ለሚሹ ለዝቅተኞችና ለተጐዱ ወገኖች እንዲሁም የዓመጽ ሰለባና ሰላምን ለሚጓጉ ሰዎች ትሰጠዋለች።

ዛሬም በምጣኔ ሃብት ቀውስ የባሰው ደግሞ በግብረ ገብነት ቀውስ እንዲሁም በአሰቃቂ የጦርነትና የግጭት ቍስሎች እጅግ ለተጐዳው የሰው ልጅ ቤተ ሰብ፣ ለአጋርነትዋ ታማኝ የሆነች ቤተ ክርስትያን ከእረኞቹ ጋር በመሆን “እንግዲህ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” (ሉቃስ 2:15)፣ እዛ ላይ ተስፋ እናገኛለን ትላለች።

ቤተ ክርስትያን ኢየሱስ በተወለደበት ቦታ በቅድስት መሬት ህያው ናት፣ የዓመፅና የቂመ በቀል ሥነ መጎት ሁሉን ትታችሁ በሰላም አብሮ ለመኖር ለሚመራ ሂደት በአዲስ መንፈስና ቸርነት እንዲሰማሩ ጥሪ ታቀርባለች። ቤተ ክርስትያን በመህከለኛ ምሥራቅ አለች፣ አስቸጋሪውን የኢራቅ ሁኔታና በክፍለ ሃገሩ የምትገኘውን “ትንሽዋ የክርስትያን መንጋ” እንዴት እንረሳለን፤ አንዳንድ ጊዜ የአመፅና ኢፍትሐውነት ሰለባ ትሆናለች፣ ሆኖም ግን ለግጭትና ጐረቤትን የመጥላትን አስተሳሰብን የሚቃወም ኅብረተሰብ ለመገንባትን የተቻላትን በማበርከት ትገኛለች።

ቤተ ክርስትያን በስሪላንካ በኮርያ በፊሊፒንስና በሌሎች የኤስያ አገሮች የዕርቅና የሰላም እርሾ በመሆን ትሠራለች። እንዲሁም በአፍሪቃ አህጉር ያለችው ቤተ ክርስትያን በዲሞክራቲክ ኮንጎ ያለው ዓመጽ እንዲወገድ ድምጽዋን ወደ እግዚአብሔር ከፍ ታሳርጋለች፣ የጊኒና የኒጀር ዜጎች የሰው ልጅ መብቶችን በመጠበቅ ለድርድር እንዲቀርቡ ጥሪ ታቀርባለች፣ ማዳጋስካርን በውስጥዋ ያሉትን ክፍፍሎች በማርገብ እንዲወያዩ ትለምናለች፣ የሚያሰቃይዋችሁ መከራ ፈተናና ችግር ቢኖሩም የሰው ልጅ ዘር ሁሉ ለተስፋ የተጠራ መሆኑን ታስታውሳለች።

ቤተ ክርስትያን የኤውሮጳና የሰሜን አመሪካ ሕዝብ ራስ ወዳድነትና የተክኖሎጂ ጥገኝነትን ትተው ለጋራ በጎና እንዲሠሩ ለደካማና ተከላካይ ለሌለው መብት እንዲጠብቁ አደራ ትላለች።

ቤተ ክርስትያን በሆንዱራስ ዳግመ ሕንፀት ሂደት እየረዳች ናት፣ በመላው ደቡብ አመሪካ ቤተ ክርስትያን ማንኛውም ርእዮተ ዓለም ሊተካው የማይችል የሐቅና የፍቅር የእያንዳንዱ መብት የሚያስጠብቅ የፍትሕና የወንድማማችነትና የአንድነት መሠረት በመሆን የምእመናንዋ መለያና ማንነት ምንጭ ናት።

ቤተ ክርስትያን መሥራችዋ ለሰጣት ተልእኮ ታማኝ በመሆን ሃብታም በሆኑ ሃገሮችም ሳይቀር፣ በተፈጥሮ አደጋና በድህነት ለተጠቁ ወገኖች አጋርነትዋን ታሳያለች።

በረሃብ ባለመቻቻል ወይም በአከባቢ ችግር አገር ቤታቸውን ለቀው ለስደት ከታደረጉ ጐን በመቆም ሊሎቹ እንዲቀበልዋቸው ጥሪ ታቀርባለች። በሌላው አነጋገር ቤተ ክርስትያን በስደት በዘረኝነትና በግድ የለሽነት ብትጠቃም በሁሉም ቦታ የክርስቶስን ወንጌል ትሰብካለች። ይህም የመምህርዋና የጌታዋ ዕጣ እንድትካፈል ያደርጋታል።

ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፣ ለሁሉም ክፍት በሆነው የዚሁ ማኅበር አባል መሆን ምንኛ ያህል መታደል ነው! ከመህከሉ አማኑኤል “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ከመሃከሉ ወደ ዓለም የመጣበት የቅድስ ሥላሴ ማኅበር ነው። እንደ ቤተልሔሙ እረኞች በመገረምና በምስጋና ተሞልተን ይህን የፍቅርና የብርሃን ምሥጢርን እናስተንትን! መልካም ልደት ለሁላችሁ!” ካሉ በኋላ በ65 ቋንቋዎች የመልካም ልደት ምኞታቸውን ገልጠዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.