2009-12-27 18:42:25

የር.ሊ.ጳጳሳት የዕለተ ሮቡዕ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ 23.12.2009


ቅ.አ.ር.ሊ.ጳጳሳት በነዲክቶስ 16 ዛሬ ሮብ በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ አጠቃላይ ሳምንታዊው የዕለተ ሮቡዕ ትምህርተ ክርስቶስ ሰጡ። ጉባኤ አስተምህሮውን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ የሚከተለው ቃለ እግዚአብሔር ከትንቢት ኢሳያስ ምዕራፍ አሥራ አንድ በተለያዩ ቋንቋዎች ተነበበ።

የኢሳይያስ ትንቢት ምዕራፍ አሥራ አንድ 1፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል። 2፤ የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።

ቅዱስነታቸው በጣልያንኛ ቋንቋ በስፋት ያቀረቡትን ትምህርት ጨምቀው በሌሎችም የኤውሮጳ ቋንቋዎች አቅርበዋል፣ ለዛሬ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያስተማሩትን እናቀርባለን። "ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፣ በዚሁ ልደትን ለማክበር በምንዘጋጅበት የመጨርሻ ቀናት ቤተ ክርስትያን የክርስቶስን ልደት እንድናስተንትንና ሕፃኑ መድኃኔ ዓለም ለዓለም የሚሰጠውን ደስታና ተስፋ እንድናጣጥም ትጠራናለች፣ በበረት በከብት መመገብያ ግርግም የሚተኛውን ኢየሱስ ሕጻንን ስንመልከት በልቦቻችንና በዓለማችን እንድንቀበለው በትሕትና የሚጠይቀንን የእግዚአብሔር ፍቅር እናስተንትናለን። ረዳት እንደሌለው ሕጻን ሆኖ በመምጣት እግዚአብሔር በኃይል ሳይሆን በፍቅር ልቦቻችንን ይማርካል፣ በዚህም ለእውነተኛ ነጻነት ሰላምና ፍጻሜ የሚመራ መንገድን ያስተምረናል። በዘንድሮው ልደት ወደ ቤቶቻችን ስንመለስ እንደ እረኞቹ ልቦቻችን በትልቅ ደስታና ፍሥሐ እንዲመሉ እግዚአብሔር በትሑቱ የቤተልሔም ሕፃን የልብ የዋህነት እንዲሰጠን ዘንድ እንለምነው"። ካሉ ብኋላ ትምህርታቸውን ለመስማት ለተሰበሰቡት ምእመናን በተለያዩ ቋንቋዎች አመሰገኑ፣ ለሁሉም መልካም ልደትን በመምኘትና ሓዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት ትምህርታቸውን ደምደምዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.