2009-12-14 17:22:05

ዜና ዕረፍት ዘጥቀ ክቡር አባ ዑቍባእግዚእ መንግሥቱ ክፍላት


ጥቀ ክቡር አባ ዑቍባእግዚእ መንግሥቱ ክፍላት የአሥመራ ካቶሊካዊ ኤጳርቅና አባል በ95 ዓመት ዕድሜአቸው ትናንትና ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ነፍሰኄር ጥቀ ክቡር አባ ዑቍባእግዚእ በአሥመራ በሰገነቲና በከረን የሚያስፈልገው ቀለማዊና መንፈሳዊ ትምህርት ቀምሰው ታሕሣሥ 12 ቀን 1932 ዓም በብፁዕ አቡነ ኪዳነማርያም ካሳ እጅ በከረን ከተማ ክህነት ተቀበሉ፣ ለአጭር ጊዜ በከረን ከተማ አከባቢ በደብረ ቅዱስ ጊዮርጊስ መጋርሕና በደብረ ኪዳነ ምሕረት ጀንገረን አገለግሉ፣ ለሁለት ዓመት ተኩል የደብረ ማርያም ጽዮን ማይሓራሳት ቆሞስ ሆኑ፣ እንዲሁም ለ6 ወራት በዓገመዳ ለአንድ ዓመት ተኩል በተኸላቢ በትጋት አገልግለዋል።

ከዛ ብኋላ በብፁዕ አቡነ ኪዳነ ማርያም ወደ ኢትዮጵያ ተልከው ባለፈው ሳምንት ወደ ሓዋርያዊ መንበር ከፍ ያለው ቦንጋ ለ8 ዓመት ተኵል በትጋት አገለገሉ።

ተልእኮአቸውን ፈጽመው ወደ ኤርትራ ተመልሰው በልደታ ለማርያም ዓዲ ዘይኑ ለ9 ዓመታት፣ በደብረ መድኃኔ ዓለም አኽሩር ለ20 ዓመታት ከሕዝቡ ጋር እየተንቀሳቀሱ በትጋት አገልግለዋል።

የምሥራቃዊ ዕቅብና ሊቀ ካህናትና የሠገነይቲ ቆምስ በመሆን በአስቸጋሪ ግዜ ለ13 ዓመታትና 4 ወራት ያህል አገልግለዋል፣ እንደገና የአኽሩር ቆሞስ በመሆን ለአንድ ዓመትና 3 ወር፣ የደብረ ኪዳነ ምሕረት ደቀ መሓረ ቆሞስ በመሆን ለሁለት ዓመት አገልግለዋል።

ብ1987 ዓም ወደ ሰገነይቲ በተጀመረው ንኡስ ዘርአ ክህነት አበነፍስና የገዳሙ አለቃ ረዳት በመሆን ለ13 ዓመታ አገልግለዋል፣ ባለፈው ዓመት ሕመም ስለጠናባቸው በእንገላ ሆስፒታል ታክመዋል፣ በያዝነው ዓመት በአሥመራ በሚገኘው የአረጋውያን ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው ትናንት በዕረፍተ ጻድቃን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የጥቀ ክቡር አባ ዑቍባእግዚእ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ በሰገነይቲ ከተማ ይፈጸማል። ቸሩ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር፣ ለቤተ ሰብና ለቤተ ክርስትያን ጽናቱን እንዲሰጥ እንጸልያለን፣ ሃቦ እግዚኦ ዕረፍተ ዘለዓለም ወአብርህ ሎቱ ብርሃን ዘለዓለም ወይኩን ዕረፍቱ በሰላም አሜን።








All the contents on this site are copyrighted ©.