2009-12-12 10:06:28

ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በቅድስት መንበር የክዩባ ኣምባሳደር ሆነው ለተሾሙ አዲስ አምባሳደር ኤድዋርዶ ደልጋዶ በርሙደዝን ተቀብለው አነጋገሩ።


ቅዱስነታቸው በንግግራቸው በአሜሪካና በክዩባ የነበረው የሻከረ ግኑኝነት መሻሻል ለሃይማኖት ነጻነትና ከምጣኔ ሃብት ቀውስ ለመውጣት የሚረዳ መሆኑን አመለከቱ። እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም. አብዮታዊ የክዩባ ሠራዊት ሃቫናን ከተቆጣጠረ ማግሥት የጀመረው የተባበሩት መንግሥታት አመሪካና ክዩባ ንትርክ በ1962 ዓ.ም. የኤኮኖሚና የፖሎቲካ አጠቃላይ ማዕቀብ በመጣል ተደምድሞ ነበር። ለግማሽ ክፍለ ዘመን የቆየው ማዕቀብ ክዩባን ብዙ ችግር ውስጥ ከተታት።
ባለፈው ዓመት የባራክ ኦባማ መንግሥት እጁን ለሰላም በመዘርጋትና የማዕቀቡ ጫናን በማላላት የጐረቤት አገሮቹ ግኑኝነት እንዲሻሻል ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
የዛሬ 12 ዓመት ገደማ ዝክረ ጥዑም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ክዩባን በተመለከተ “ክዩባ አስደናቂ ችሎታዎችዋን ለዓለም ትክፈት ዓለምም በበኩሉ ለክዩባ ክፍት ይሁን” ብለው ነበር። ቅዱስ ኣባታቸን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ይህ ከአሥር ዓመታት በፊት የተገለጸው መልካም ምኞት በብዙ ጥረትና ችግር የተደረሰ ቢሆንም ቅሉ ተፈጽመዋል ለማለት እንደሚቻል ካብራሩ በኋላ “ክዩባ በካሪብያን ደሴቶችና በላቲን አሜሪካ አገሮች ብዙ ነገር ታበርክታለች፣ በተለይ በምጣኔ ሃብትና ፖሎቲካ ዘርፍ ወሳኝ ሚና ለማበርክት እንደምትችል እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል። “አሁን እንድምንታዘበው በክዩባና በጐረቤት የተባበሩት መንግሥታት አመሪካ ቀዝቅዞ የነበረው ግንኙነት እየሞቀ ነው፣ ይህም የያንዳንዱን ልዑላውነት መንግሥትና ሕዝብ እግምት ውስጥ በማስገባት ለሁለቱም አገራት ጥቅም የሚውል አዲስ ዕድል እንደሚከፍት እርግጠኛ ነኝ፣” ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል።

ክዩባ ለዓለም የምታበርክተውን ሲያብራሩም፦ “ዛሬ ክዩባ ከብዙ አገሮች ጋር መሃይምነት በማጥፋትና በጤና ጥበቃ ዘርፎች በመተባበርዋ ትታወቃለች፣ እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃም መተባበርና አጋርነትን ታራምዳለች። ይህም የእያንዳንዱ ዜጋ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ሳታጓድል በዓለማችን በምጣኔ ሃብት ቀውስ ለተከሰቱ ችግሮች መፍትሔ ልታገኝ እንደምትችል ያመልክታል። እንደ ሌሎቹ ብዙ አገሮች ክዩባም ተጥሎባት በነበረው አጠቃላይ ማዕቀብና አምና በተከሰተው የምጣኔ ሃብት ቀውስ እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋ ባጋጠምዋት አደጋዎች፣ በተለይም የኅብረተሰቡ ድኃ ወገንና ቤተ ሰቦች እንደሚቸግሩ እርግጥ ነው። አሁንም በዚሁ የችግሮች ውስብስብ በበዙበት ጊዜ በሰብአዊ ግብረ ገብነት የተመሠረቱ የሰው ልጅና መብቶቹን የሚያስቀድሙ የምጣኔ ሃብት ደንቦች በመደንገግ ለሰው ልጅ ሥጋዊና መንፈሳዊ መልካም ኑሮ እርካታ መሥራት የግድ ያስፈልጋል፣”ብለዋል።
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው እ.አ.አ. በ2012 ዓ.ም. የፍቅርት እም ድንግል ማርያም የተባረከው ሓውልት የተገኘበት 400ኛ ዓመት ለማክበር ብዝግጅት ለምትገኘው የክዩባ ቤተ ክርስትያን መልካም ምኞታቸውን ከገለጹና ካበረታቱ ብኋላ፣ “የምንታዘባቸው የእምነት ነጻነት የመጠበቅ ምልክቶች እንዲበዙ፣ ማለትም በመጨረሻ ዓመታት በወህኒ ቤት መሥዋዕተ ቅዳሴ ለማሳረግ መፍቀድ፣ በክርስትያን በዓላትና ነግሥ ሥርዓተ ዑደት ለማድረግ መተባበር፣ አንዳንድ ቤተ መቅደሶችን ለማሳደስ መፍቀድና ቀድሞ የተወረሱትን ቤተ ጸሎቶች ለቤተ ክርስትያን መልሶ መስጠት እንዲሁም ኣዲስ ገዳማት ለመክፈት ፍቃድ መስጠትና ካህናትና ገዳማውያን ሰብአዊ እርዳታ እንዲያገኙ መፍቀድ እጅግ የሚመሰገን ነው፣ በዚህም የካቶሊክ ማኅበር ሓዋርያዊ ግብረ ተልእኮዋን በነጻነት ለማበርክት ትችላለች። ክዩባ ጥንታዊ የክርስትና መሠረት ስላላት ለሕዝብዋ ትልቅ መንፈሳዊ ግብረ ገባዊ ሃብት ለማስወረስ በቅታለች፣ በክዩባ በቫቲካን ያለው ግኑኝነት ቅኑና አቋርጦ የማያውቅ ነው። በዚህም ረገድ ለክዩባ ቤተ ክርስትያን የምናበረክተው ዋነኛው ኣገልግሎት ኢየሱስ ክርስቶስንና የምሕረትና የእውነተኛ ዕርቅ የሆነው የፍቅር መልእክቱን ማብሠር ነው፣ በዚሁ የአንድነት ጐደና የሚጓዝ ሕዝብ የብሩህ መጻኢ ተስፋን የሚመግብ ነው።” ብለዋል







All the contents on this site are copyrighted ©.