2009-10-05 18:06:39

የአፍሪቃ ጳጳሳት ሲኖዶስ ተጀመረ


የአፍሪቃ ጳጳሳት ሲኖዶስ የሚከናወነው ዕርቅ ፍትሕና ሰላም በሚመለከቱ የአህጉሩ ጉዳዮች ላይ በማትኮር ሲሆን፣ ቅድመ ዝግጅቱ ኣልቆ ትናንት እሁድ ጥዋት በሮም ሰዓት አቆጣጠር ልክ ዘጠኝ ሰዓት ተኵል ቅ.ኣ.ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባሳረጉትና በመሩት ደማቅ የመሥዋዕተ ቅዳሴ ሥርዓት በይፋ ተጀመረ።

ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ከበጋው ዕረፍት ካስተንጋደልፎ ሓዋርያዊ አደራሻቸው ወደ ቫቲካን የተመለሱት ባለፈው ቅዳሜ ጥዋት ሲሆን፣ የቫቲካን ረድዮና ተለቪዥን የአፍሪቃ ጳጳሳት ልዩ ሁለተኛ ሲኖዶስ መክፈቻ ቅዳሴ ሥርዓት ከቦታው በቀጥታ ለዓለም ሕዝብ አስተላልፈዋል።

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ.በነዲክቶስ 16ኛ ትናንት እሁድ የልዩ ሁለተኛ አፍሪቃ ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤ በይፋ ለመክፈት ባሳረጉት መሥዋዕተ ቅዳሴ ያሰሙት ስብከት እንደሚከተል ነው።

“በጵጵስናና በክህነት ወንድሞቼ ለሆናችሁ ውድ ጓደኞቼ እንዲሁም ክቡራትና ክቡራን ወንድሞቼና እህቶቼ፤ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን። ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት በሚያዝያ 10 ቀን 1994 ዓ.ም. የእግዚአብሔር አገልጋዩ ር.ሊ.ጳ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አንደኛ ልዩ የአፍሪቃ ጳጳሳት ሲኖዶስ በከፈተበት ቦታ እዚህ በቫቲካን ባዚሊካ ውስጥ ለተሰበሰባችሁ ሁሉ በዚህ ሊጡርጊያዊ ሥርዓት ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

ሁለተኛ ሲኖዶስ ለምክፈት እዚህ የምንገኝበት ምክንያት የመጀመርያ ሲኖዶስ በእውነት ታሪካዊ መኖሩንና ከዚሁ ከአሁኑ የተለየና የተነጠለ አለመሆኑን ያመለክታል። እግዚአብሔር ለዚህ ዕለት ስላበቃን እናመሰግነዋለን። ይህንን መሥዋዕተ ቅዳሴ ብኁባሬ ከኔ ጋር ለሚያቀርቡት ለሲኖዶሱ ጉባኤ አባላት ምሁራንና አዘጋጆች፣ በተለይ ደግሞ ከአፍሪቃ ምድር ለመጡት እንኳን ደህና መጣችሁ ስል ልባዊ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ለሲኖዶሱ ጠቅላይ ዋና ጸሓፊና ለረዳቶቻቸው ከልዩ ምስጋና ጋር ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

በመካከላችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በመገኘታቸው በእጅጉ ስደሰት ለእርሳቸውና ለተቀሩት እህት አብያተ ክርስትያናት እና ቤተ ክርስትያናዊ ማኅበራት ወካዮች ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እንዲሁም በዚህ አጋጣሚ መሳተፍ እና መገኘት የቻሉትን የሕዝብና የመንግሥታት ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም አምባሳደራት እንኳን ደህና መጣችሁ ማለትን እወዳለሁ።

ለካህናት ለመንፈሳውያን ማኅበራት አባላት ሴቶችና ወንዶች ለማኅበራት ተወካዮች ለክርትያን እንቅስቃሴ ማኅበራት እና ከሲስቲን ቤተ ጸሎት መዘመራን ጋር በመተባበር የቅዳሴው ሥርዓት ለሚያደምቁት የኮንጎ መዘመራን ቡድን ደማቅ የፍቅር ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

የዕለቱ ሊጡርጊያ የመጽሓፍ ቅዱስ ንባብ ስለ ቃል ኪዳን ይገልጻል። በመሠረቱ ግን ስለ ፍጥረት ዕቅድና ስለ ጥንተ ሕይወት ስለሚገልጽ ስለ እግዚአብሔር ይናገራል። ከመልእክተ ዕብራውያን የተነበበው ሁለተኛ መልእክትም “ሰዎችን ቅዱሳን የሚያደርጋቸውና በእርሱ ቅዱሳን የሆኑትም ሰዎች የአንድ አባት ልጆች ናቸው፣ በዚህ ምክንያት ኢየሱስ እነርሱን “ወንድሞቼ” ብሎ ለመጥራት አያፍርም” (ዕብራውያን 2:11) ሲል የሚቀድሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚቀደሰው ደግሞ ሰው መሆኑን ስለሚያረጋግጥ መልእክቱ ከመጀመርያው ምንባብ ጋር ይስማማል።

በሁለቱም ንባባት የፈጣሪ እግዚአብሔር ቀዳሚነት እና ጌትነት ግልጽ በሆነ መንገድ ተመልክቶአል። ይህንን የእግዚአብሔር ቀዳሚነትና ጌትነት ከአዋቂዎች ይልቅ ሕፃናት በተሻለ አኳኋን ስለሚቀበሉት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡ እነርሱ መሆናቸውን “በእውነት እላችኋለሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን ሆኖ የማይቀበላት ከቶ አይገባባትም” ሲል ያረጋግጣል፣ (ማርቆስ 10:15) ተመልከት።

አሁን መግለጥ የምፈልገው በአፍሪቃው ባህል የእግዚአብሔር ፍጹም ጌትነትና ታላቅነት ዋና አስተባባሪ ጉዳይና ገጽታ መሆኑን ነው። በአፍሪቃ ብዙ የተለያዩ ባህሎች አሉ፣ ነገር ግን ይህን ጉዳይ በተመለከተ ሁላቸው ይስማማሉ። በተለያዩ ባህሎች እግዚአብሔር ፈጣሪና የሕይወት ምንጭ ነው፣ ጥሩ አድርገን እንደምናውቀው ከሁሉም በፊት ሕይወት ራሱን የሚገልጠው በባልና ሚስት መካከል ባለው ውህደትና በልጆች መወለድ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እንግዲህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው” (ማርቆስ 10:9) ብሎ በመናገሩ በባህርይ ውስጥ የተጻፈው መለኮታዊ ሕግ ከማንኛውም ዓይነት ሰብአዊ ሕግ የሚቀድምና መከበር ያለበት ነው። ከሁሉ አስቀድሞ ይህ አስተሳሰብ ሞራላዊ አይደለም፣ መጀመርያ ሰውንና በፍጥረት የተቀረጸውን ነገር ስለሚመለከት ግዴታ ወይም ሓላፊነት ነው። እንዲህ ከተረዳነው ታድያ የዕለቱ ሊጡርጊያ የአፍሪቃ ሲኖዶስ ጉባኤ መክፈቻ እንዲሆን ተገቢነት ያለው ነው።

በመቀጠል በሲኖዶሱ ጉባኤ ከሚጠብቁን ሥራዎች አንዳንዶቹን መጥቀስ እፈልጋለሁ።

የመጀመርያው ድሮ የጠቀስኩት የፈጣሪ እግዚአብሔር ቀዳሚነትና ጌትነት ነው።

ሁለተኛው ቃል ኪዳን ሶስተኛው ደግሞ ሕፃናት ናቸው።

የመጀመርያውን በሚመለከት አፍሪቃ ለመላው ዓለም የተከማቸ ሃብት ጐተራ ወይም ሚዘዩም ናት። አፍሪቃ ስለ እግዚአብሔር ያላት ጥብቅ ግንዛቤ ለሐዋርያዉ ጉብኝት ወደ ቫቲካን ከሚመጡ የአፍሪቃ ጳጳሳት እና በአካል በቅርቡ ወደ ኣፍሪቃ አህጉር ማለት ወደ ካመሩንና አንጎላ ካደረግኩት ሓዋርያዊ ጉዞ ለመረዳት ችያለሁኝ። የአፍሪቃ ጉብኝቴን እማስታውሰው በልዩ የፍቅር ስሜት ነው፣ በአሳብም የሲኖዶሱ ጉባኤ መምርያ ሰነዱን ለአፍሪቃ ጳጳሳት ምክር ቤቶች ሊቃነ መናብርት በማስረከብ የከፈትኩት በዛን ወቅት ነው።

ስለ አፍሪቃ ሃብት ስንናገር በቀጣታ በኣእምሮኣችን የሚደቀነው የአህጉሩ የተፈጥሮ ጸጋና ሃብት ነው። ያሳዝናል! ይህ ሃብት አብዛኛውን ጊዜ የብዝበዛ የግጭትና የሙስና መንሥኤ ምክንያት ሆኖ ቀጥሎዋል፣ ነገር ግን ቃለ እግዚአብሔር ሌላ ሃብተ-ውርሻ እንዳለም ያስገነዝበናል፤ እሱም መንፈሳዊና ባህላዊ ሃብት ሲሆን ለሰው ዘር ከግዙፍ ሃብት ይልቅ የበለጠ ከፍተኛ አስፈላጊነት ያለው ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ለማስገንዘብ ሰው “የዓለምን ሃብት ሁሉ አግኝቶ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋ?” (ማርቆስ 8:36) ሲል ይጠይቀናል። ከዚህ ጎን ካየነው አፍሪቃ ለሰው ዘር ማገልገል የሚችል አንድ ትልቅ መንፈሳዊ ሳንባ አላት። ይህ ሳንባ በዓለም በወቅቱ በእምነትና በተስፋ ማነስ ቀውስ ችግር ውስጥ ገብቶ ይገኛል። ይህ መንፈሳዊ ሳንባ ሊታመም ይችላል፤ በወቅቱ ሁለት ገዳይ በሽታዎች እየተጠናወቱት ነው።

አንደኛው በምዕራቡ ዓለም ተስፋፍቶ ያለው ሁሉም ነገር ንጽጽራዊ እንጂ ተጨባጭ ሓቅ የለም፣ እንዲሁም ሁሉ ኢምንት ነው እንጂ እግዚአብሔር የለም በማለት ከሚክደው አስተሳሰብ ጋር የተደባለቀ ማተርያሊዝም ወይም ንዋታዊነት ነው። ምዕራቡ ዓለም የቀረውን ዓለም በዚህ በሽታ መርዝ እየለከፈ ነው። በተለይ የአፍሪቃ አህጉርን መልከፍንና መመረዝን ቀጥሎበታል፣ በዚህ ዐይን ካየነው ኮሎንያሊዝም ወይም የባዕድ አገዛዝ ጨርሶ ተወገደ ማለት ኣይቻልም።

የሁለተኛው ዓይነት በሽታ ቫይረስ ወይም መርዝ ሃይማኖታዊ አክራሪነት ወይም ጽንፈኛነት ሲሆን የሚስፋፋው ከፖሎቲካና ኤኮኖሚ ጥቅም ጋር ተዛምዶ ነው። በአፍሪቃ የተለያዩ እምነት የሚከተሉ ቡድኖች እየተስፋፉ ነው። እንዲህ የሚስፋፉት በእግዚአብሔር ስም ሲሆን የሚሰሩት በእግዚአብሔር አንጻር አካሄድ ነው። ስለ ፍቅርና የነጻነት መክበር በማስተማር ፈንታ አለመቻችልንና አመጽን ያስተምራሉ።

ቃል ኪዳን በተመለከተ ኦሪት ዘፍጥረት (2:24) ላይ “ስለዚህ ሰው አባቱንና እንቱን ይተዋል በሚስቱም ይጣበቃል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ሲል እንዳረጋገጠው፣ ኢየሱስ ራሱም ከዚህ ጋር እንድሚስማማው ለዘላለም መጽናት ያለበት ምሥጢር ነው። የእግዚአብሔር አገልጋዩ ር.ሊ.ጳ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በታላቁ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ላይ እንዳመዘገቡትም፤ ይህ ምሥጢር ማለት ቃል ኪዳን በአፍሪቃው አህጉር ቤተ ክርስትያናዊና ኅብረተሰባዊ መድረክ ከፍተኛ ተቀባይነት ሊቸረው እንደሚገባ ያሳስበናል።

ቅዱስ መጽሓፍ እንደሚገልጠው ቃል ኪዳን ከእግዚአብሔር ግኑኝነትና ውህደት ውጪ ተነጥሎ የሚታይ ነገር አይደለም። ከባልና ሚስት ሕይወት እና ከነርሱ የሚመነጨው ቤተ ሰብ በእግዚአብሔር ውህደት የተገነባ ነው። በአዲስ ኪዳን አመለካከትም የቅድስት ሥላሴ ፍቅርና ክርስቶስ ከቤተ ክርስትያኑ ጋር ያለው አንድነት ተምሳሌት ነው። አፍሪቃ ከመንፈሳዊ ባህልዋ በቃል ኪዳን ላይ ለተመሠረተው ቤተሰብ ብዙ ነገር የመስጠት ዐቅም አላት። ኢየሱስ ስለ ሕፃናት የተናገረውን ከተገነዘብን ደግሞ በአፍሪቃ የሚገኙትን ብዙ ያልታደሉትን ስቃይ ላይ የወደቁትን ሕፃናት ማስታወስ እንችላለን። ኢየሱስ ሕፃናትን ላባረሩት ደቀ መዛሙርቱ በጥብቅ ይቃወማቸዋል። ቤተ ክርስትያን በአፍሪቃም ሆነ በተቀሩት የዓለም ክፍሎች ሕፃናት መንከባከብ ይጠበቅበታል። ሕፃናት ከመወለዳቸውም በፊት ተመሳሳይ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። ቤተ ክርስትያን ለሕፃናት እንደ ኢየሱስ ሙሉ የኅብረተሰብ አባላት ወይም ክፍል አድርጋ ትመለከታቸዋለች፣ ምክንያቱም ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚመራዉን መንገድ የሚያሳዩ እነርሱ ናቸውና። በሙሉ እምነት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ፍቅር የሚሰጡ ሕፃናት ናቸው።

ውድ ወንድሞቼ፣ ሲኖዶሱ ሰለ እነዚህ ጉዳዮች ያስተነትናል፣ ር.ሊ.ጳ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የመጀመርያው ልዩ አፍሪቃዊ ሲኖዶስ ውጤት “በአፍሪቃ ያለችው ቤተ ክርስትያን” በሚል ስያሜ ባሳተሙት ሓዋርያዊ ምዕዳን ላይ አቅርበውታል፣ እዛ እንደተገለጸው የመጀመርያው ቀዳሚነት ያለው ሥራ፣ ስብከተ ወንጌል ነው። የዘመናችን ፈጣን ፖሎቲካዊ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ለውጥ ያገናዘበ አዲስ ስብከተ ወንጌል ያስፈልጋል። ሁለተኛው ማለት አሁን የምናካሄደው የአፍሪቃ ጳጳሳት ሲኖዶስ ርእሰ ጉዳዩን የሚያገኘው “የአፍሪቃ ቤተ ክርስትያን በዕርቅ ፍትሕና ሰላም አገልግሎት” ከሚለው ተጨባጭ ፍሬ ነገር ይሆናል። ይህን ተከትሎ የሚመጣው “እናንተ የምድር ጨው፣ የዓለም ብርሃን ናችሁ” የሚለው በማቴዎስ ወንጌል (5:13-14) ባለው የተጠቀሰ መለኮታዊ መልእክት ነው።

ባለፉት ቅርብ ዓመታት የአፍሪቃ ቤተ ክርስትያን ብዙ ተንቀሳቅሳለች፣ የሲኖዶሱ ጊዜ ለዚህ ጸጋ ምስጋና የሚቀርብበት ጊዜም ይሆናል፣ ስለ ሓዋርያዊ ግብረ ተልእኮና ስብከተ ወንጌልም ዐውደ ጥናት ይካሄዳል። የዓለም ብርሃንና የምድር ጨው ለመሆን ሁሌ በከፍተኛ ደረጃ ለቅድስና መትጋት ያስፈልጋል፣ መንፈሳውያን መሪዎችና ማኅበረ ምእመናን ሁላቸው በቤተ ክርስትያን ቅዱሳን ለመሆን ተጠርተዋል፣ የአፍሪቃ ቤተ ክርስትያን እውነተኛ የክርስቶስ ወለተ መዝሙር መሆን ይቻላት ዘንድ በጎሳዎችና በሕዝቦች መኸከል ያሉት ልዩነቶች የኅብረትና የአንድነት የመንፈሳውያን ጸጋዎች ምክንያት ይሆኑ ዘንድ፣ ድህነት አመጽና ፍትሕ አልቦነት ግጭቶችና ጦርነቶች ተወግደው በሰላም በስምምነትና በኅብረት አብሮ የሚኖር አፍሪቃዊ ማኅበረ ሰብ እንዲመሠረት እንጸልይ። አፍሪቃ ከሙታን በተነሣው ጌታ ኢየሱስ ብርሃን እንድትመራ እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ይስጣት። ሲሉ ለአፍሪቃ መንፈሳዊና ሥጋዊ ብልፅግና ያልቸውን መልካም ምኞት እና ጸሎት ካቀረቡ በኋላ በተለይ በዚሁ ለካህናት በተመደበው ዓመት እያንዳንዱ የሲኖዶስ አባትና ተሳታፊ በሲኖዶሱ ጉባኤ ወቅት ለሚያበርከተው አስተዋፅኦ ከወዲሁ ከልብ አመስግነዋል። የሁሉም ክርስትያን ምእመናን ማኅበረ ሰብ ለሲኖዶሱ ጉባኤ መሳካት በጸሎት እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል። የቅዱስ ፍራንቸስኮስና የአፍሪቃ አህጉር ቅዱሳን እንዲሁም የቤተ ክርስትያን እናትና የአፍሪቃ እመቤት ድንግል ማርያም ልዩ አማላጅነት በማማጠንም ስብከታቸውን ፈጽመዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.