2009-09-02 15:02:50

የቅዱስ አባታችን የመስከረም ወር የጸሎት ሀሳብ


የመስከረም ወር የቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ የጸሎት ሀሳብ በላኦስ ካምቦጅያና ምያንማር ያተኰረ መሆኑን ከቅድስት መንበር የደረሰን ዜና አመልክተዋል።

የጸሎቱ ይዘት እንደሚከተለው ነው። “ዘወትር በትልቅ ችግር የሚገኙ የላኦስ የካምቦጅያና የምያንማር ማኅበረ ክርስትያን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመተማመን ቅዱስ ወንጌልን ለወገኖቻቸው ለመስከብ ተስፋ እንዳይቆርጡ እንለምን።”

ፊደስ የዜና አገልግሎት እንደገለጸው በቤተ ክርስትያን ታሪክ ውስጥ ባለፉት 20 ክፍለዘመናት ከ43 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ክርስትያኖች በሰማዕትነት ክርስቶስን መስክረዋል። ከእነዚህ ግማሹ ባለፈው ክፍለዘመን ብቻ የሞቱ ናቸው። አሁንም ቢሆን በያዝነው ክፍለዘመናችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ክርስትያኖች በክርስትና ለመኖርና ለመመስከር ብዙ ችግር እያጋጠማቸው ነው። እጅግ ከባድ ቍጥጥር ጭቆና በእስር ቤት መማቀቅ እስከ የሕይወት መሥዋዕት እየከፈሉ ናቸው።

የመስከረም ወር የሰባክያነ ወንጌል ጸሎት ሀሳብ በሶስት አገሮች እንድናተኵር ጥሪ ያቀርባል። በላኦስ ካምቦጅያና ምያንማርን ያሉ ማኅበረ ክርስትያን ባለፈው ዘመን በተከሰተው ስደት ሳቢያ በደረሰው ችግር ገና እየተሰቃዩ ናቸው።

የእነዚህን ሥቃይ አስመልክተው ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ‘ለኤስያ ቤተክርስያን በጻፉት ሐዋርያዊ ምዕዳን’ “በእነዚህ እኅቶቻችን አብያተ ክርስትያን እየተሰቃዩ ላሉ ወንድሞችና እኅቶች ሥቃዮቻቸውና ችግራቸውን ከተሰቀለው ክርስቶስ ሥቃይ ጋር በመጨመር ለእርሱ እንደ መሥዋዕት እንዲያቀርቡት በዚህም እኛና እሳቸው የትንሣኤና የአዲስ ሕይወት መንገድ በእምነትና በፍቅር በምንሸከመው መስቀል ብቻ መሆኑን እንረዳለን’’ ብለው ነበር።

የመንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ መውረድ የመስቀል ፍሬ ነው፣ እንዲሁም ይህ መንፈስ ወደ መስቀል ይመራል። ይህ መንፈስ ከእኛ ጋር በመኖር ኃይልና ጽናት በመስጠት ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ ሕይወት እንድንኖር ይረዳናል።

በእምነታቸው ምክንያት ለሚሰደዱትና ለሚሰቃዩት ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ይህን ኃይልና ጽናት እንለምንላቸው። ይህ ስጦታ መልእልተ ባህርያዊ ኃይል በመሆኑ ለነፍሳት በስደት ጊዜ ብች ሳይሆን እስከ ሰማዕትነት ይረዳል።

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ ምዕራፍ 12 ቍ 10 ‘ስለዚህ የክርስቶስ ኅይል በእኔ እንዲሆን ከምን ጊዜውም ይልቅ በደካማነቴ ልመካ እወዳለሁ። ኅይል የማገኘው ደካም በምሆንበት ጊዜ ስለሆነ ስለ ክርስቶስ ስደክም ስሰደብ ስቸገር ስሰደድ ስንገላታ ደስ ይለኛል።’ የሚለውን በብኩላቸው ደግመውት እስኪችሉ ድረስ በሃይማኖት ስለሚሰቃዩት እንጸልይ። ይህ ከስቃይ የሚመጣ ኃይል ክርስቶስ በመንፈሱ የሚሰጠን ኃይል ነው። በስደት በሚሰቃዩ ማኅበረ ክርስትያን መሀከል ይህ የጀግንነትና የታማኝነት ምስክርነት በጣም ሰፊ የስብከተ ወንጌል ተልእኮ አለው።








All the contents on this site are copyrighted ©.