2009-08-31 17:18:53

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ


ቅ.ኣ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትናንትና ከካስተል ጋንዶልፎ ሓዋርያዊ አዳራሽ የመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት ስለ ቅድስት ሞኒካ የሚከተለውን ትምህርት ሰጥተዋል።

“ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፦ ከሦስት ቀናት በፊት እአአ ነሐሴ 27 ቀን የክርስትያን እናቶች አርአያና ጠበቃ የሆኑና የቅዱስ አጎስጢኖስ እናት የቅድስት ሞኒካ በዓል አክብረናል። ልጅዋ ቅዱስ አጎስጢኖስ ኑዛዜ በሚለው መጽሓፉ ስለ እርስዋ ብዙ ይናገራል። ቅዱስ አጎስጢኖስ ከእናቱ ወተት ጋር የኢየሱስን ትምህርት በመመገብ ከእናቱ ክርስትናን ተማረ፣ ይህ ትምህርት ከክርስትና መስመር ወጥቶ ኢሞራላዊ ሕይወት በመራበት ጊዜም ሳይቀር በአእምሮው ተቀርጾ ቀረ። ቅድስት ሞኒካ ለልጅዋ መለወጥ መጸለይን አቋርጣ አታውቅም። በመጨረሻም ጸሎትዋ ተሰምቶ ወደ ክርስትና ገብቶ ምሥጢረ ጥምቀት በተቀበለ ጊዜ እጅግ ተጽናናች። እግዚአብሔር የዚህች ቅድስት እናት ጸሎት እንደተቀበለው የታጋስተ ጳጳስ ‘እናት ይህን ያህል እንባ ያፈሰሰችለት ልጅ እንዲሁ በከንቱ ሊጠፋ አይችልም’ በማለት ይገልጹታል። እውነትም ቅዱስ አጎስጢኖስ ክርስትናን ብቻ አልተቀበለም የምኩስና ሕይወትን በመቀበል ወደ አፍሪቃ ተመልሶ የመነኮሳን ገዳም አቋቋመ። ወደ ኣፍሪቃ ለመሄድ ሲዘጋጅ በኦስትያ በእርሱና በእናቱ ቅድስት ሞኒካ የተደረገው መንፈሳዊ ንግግር እጅግ የሚመስጥና የሚያንጽ ነበር፣ ቅድስት ሞኒካ ለቅዱስ አጎስጢኖስ ከእናትነት በላይ የክርስትናው ምንጭ ሆነች፣ የእርስዋ ዋነኛ ፍላጎት የቅዱስ አጎስጢኖስ መለወጥ ነበር፣ ወደ ክርስትና ገብቶ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ሁለንተናውን ሰጥቶ የእግዚአብሔር ሰው መሆኑን ለማየት በቃች። በደስታ ልትሞት ነበር፣ በ56 ዓመትዋ ነሐሰ 27 ቀን 387 ዓም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ከመሞትዋ በፊት ለልጆችዋ ስለቀብርዋ እንዳይቸገሩ ሁል ጊዜ እንዲያስታውስዋት በተቻላቸው እንዲያስቀድሱላት አደራ ብላቸው ነበር። ቅዱስ አጎስጢኖስ ደጋግሞ እናቱ ሁለት ጊዜ እንደወለደችው ይናገር ነበር።

የክርስትና ታሪክ የብዙ ልበ ርኅሩኅ ካህናትንና የቤተ ክርስትያን እረኞች ሕይወት በሸኙ በብዙ ቅዱሳንና አብነታውያን ወላጆችና እውነተኛ የክርስትያን ቤተ ሰቦች ያሸብረቀ ነው። ቅዱስ ባስሊዮስ ዓቢይና ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ሁለቱም ከቅዱሳን ቤተ ሰብ የመጡ ናቸው። በጊዜ ወደ ዘመናችን ቅርበት ያላቸው ብፁዕ ልዊጂ በልትራመ ኳትሮኦኪ እና ባለቤታቸው ብፅዕት ማርያ ኮርሲኒ በ19ኛው ክፍለዘመን የኖሩ ከእኔ በፊት በነበሩ ዝክረ ጥዑም የእግዚአብሔር አገልጋል ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋሚልያሪስ ኮንሶርስዮ የሚለውን ሐዋርያዊ ምዕዳን 20ኛ ዓመት አጋጣሚ በማድረግ እአአ በጥቅምት ወር 2001 ዓም ብፅዕናቸውን አውጀውላቸዋል። ሐዋርያዊ ምዕዳኑ የቃል ኪዳን ዕሴትና የቤተ ሰብ ኃላፊነትን ከመግለጽ አልፎ ሚስትና ባለቤትን ቅዱስ ሕይወት በመኖር የምሥጢረ ተክሊል ጸጋና ኃይልን እንዲጠቀሙ ጥሪ ያቀርባል። ሚስትና ባለቤት በለጋስነት ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ የእግዚአብሔር ፍቅር ዕቅድ ለመረዳት እንዲመርዋቸውና አቅጣጫ እንዲያሳይዋቸው ያስፈልጋል። የክህነትና የምንኩስና ጥሪ እንዲሰማቸውና በዚሁ እንዲታነጹ የልጆቻቸውን መንፈሳዊውን ህይወታቸው በጥሩ ማዘጋጀት አለባቸው። ቃል ኪዳንና ድንግልና የተዋሃዱና አንዱ ሌላውን እንደሚያብራራ ሁለቱም በክርስቶስ ፍቅር የተመሠርቱ መሆንቸው በዚህ ይገለጻል።

ውድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፦ በዚሁ የካህናት ዓመት፣ በአርሱ ቆሞስ ቅዱስ ዮሓንስ አማላጅነት የክርስትያን ቤተሰቦች ትናንሽ አብያተ ክርትያናት እንዲሆኑና ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጡን ጥሪዎችና ሥጦታዎች ሁሉ ተቀብያነት እንዲያገኙና ተገቢ ክብራቸው እንዲጠበቅ እንጸልይ። እመቤታችን ድንግል ማርያም ይህንን ጸጋ እንድታስገኝልን አብረን እንለምናት” ብለው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳረጉ።

ጸሎቱን ካሳረጉ በኋላ ነገ ማክሰኞ ተከብሮ ለሚውለው የፍጥረት ጥበቃ ቀን በማስታወስ ለዘንድሮ ያለው መሪ ሐሳብ የአየር አስፈላጊነት መሆኑን ጠቅሰው ባለፈው ሮብ እንዳስተማሩት የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን ፍጥረት እንድንንከባከብ አደራ ብለዋል፣ በተለይ በኢንዳስተሪ የበለጸጉ አገሮች የዓለማችን የወደፊት ሁኔታን እግምት ውስጥ በማግባት በተፈጥሮና አከባቢ ብከላ ለሚመጣው ችግር ድኃ ሕዝቦች ባለዕዳ እንዳይሆኑ በኃላፊነት እንዲተባበሩ አበረታትተዋል። በመጨረሻም ከጣልያን አገርና ከተለያዩ ክፍለ ዓለም ከቅዱስነታቸው አብረው ለመጸለይና ትምህርታቸውን ለመስማት በካስተል ጋንዶልፎ ሓዋርያዊ አዳራሽ ግቢ ለተሰበሰቡት ምእመናን በተለያዩ ቋንቋዎች አመስግነው ሓዋርያው ቡራኬ በመስጠት የዕለቱን ጉባኤ አስተምህሮ ደመደሙ።








All the contents on this site are copyrighted ©.