2009-08-10 16:11:10

የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመልኣከ እግዚኣብሔር ጉባኤ አስተምህሮ


ቅ.ኣ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ የትናንትናው የመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ከካስተል ጋንዶልፎ ሓዋርያዊ አዳራሽ መምራታቸው ተመለከተ። በተለመደው መንፈሳዊ መልእክታቸው “ፍቅር ሞትን እንድሚያሸንፍ ሰማዕታት ያስተምሩናል’’ ሲሉ ዓመተ ካህንና ቅድስናውን ማእከል ያደረገ በቅዱሳንና ሰማዕታት የሕይወት ምስክርነት የተዋበ አስተምህሮ ሰጥተዋል።

“ዉድ ወንድሞቼና እኅቶቼ፣ ባለፈው እሁድ እንዳደረግነው ዛሬም ከምናስተነትነው ዓመተ ካህን ሳንወጣ በዚሁ ሳምንት ቅድስት ቤተ ክርስትያን የምታከብራቸውን ቅዱሳን ሕይወትና ትምህርት እንመለከታለን። የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅር ገፍቶዋት ሕይወትዋን ሙሉ ለጸሎትና ለማኅበራዊ ሕይወት ከሰዋች የአሲዚዋ ቅድስት ክያራ በስተቀር ሊሎቹ የዚህ ሳምንት ቅዱሳንና ቅዱሳት ሰማዕታት ናቸው። ከእነዚህ ሁለቱ በአውስኪዝ በናዚ የተገደሉ ቅድስት ተረዛ በነደታ ዘመስቀል ማለትም አዲዝ ሽታይን እና ቅዱስ ኣባ ማሲሚልያኖ ኮልበ ናቸው። ቅዱስት አዲዝ ሽታይን ከዕብራውያን ቤተ ሰብ የተወለደችና በወጣትነትዋ ክርስትናን ተቀብላ የካርመላውያት መንኮስ ሆና ጌታን በሁለንታዋ ስታገልግል ነው በሰማዕትነት የሞተችው፣ እንዲሁም ቅዱስ ኣባ ማሲሚልያኖ ኮልበ የፖላንድ ተወላጅና የአሲዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ተከታይና የንጽሕት ድንግል ማርያም ሓዋርያም በናዚ ኮንሰንትረይሽን ካምፕ በሰማዕትነት የአንድ ቤተ ሰብ አባት ምትክ በመሆን በሰማዕትነት ሞቱ። ከዚህ በመቀጠል የሮማ ቤተ ክርስትያን ሰማዕታት እናገኛለን። እነርሱም ቅዱስ ፖንዝያኖ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩ፣ ቅዱስ ሂፖሊቶ ካህንና ቅዱስ ሎረንዞ ዲያቆን ናቸው። እነዚህ አስደናቂ አርአያ የሆኑ ቅዱሳን ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦ ሰዎች በጻፈው በአንደኛ መልእክቱ ምዕራፍ 13 ከቍ.4-8 እስከ መጨረሻ ድረስ በፍቅር ተቃጥለው መጥፎ ነገርን በጥሩ ነገር እየተዋጉ የክርስቶስ ፍቅር ምስክር ናቸው። በተለይ እኛ ካህነት ከእነዚህ የምንማረው ማንንም ሳንፈራ ለነፍሳት ድሕነት ሕይወታችን መሥዋዕት እስከ ማድረግ የሚገፋን የወንጌል ጀግንነትን ነው። ፍቅር ሞትን ያሸንፋል።

ቅዱሳን ሁሉ በተለይ ሰማዕታት እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን ይመሠክራሉ። የናዚ ካምፕ እንደ ማንኛው የህልቂት ካምፕ በዚህ ዓለም የሰው ልጅ እግዚአብሔርን በመርሣት በቦታው ራሱን በመተካት ፈላጭ ቆራጭ በመሆን ሊያደርገው የሚችልውን መጥፎ ነገር፣ የጥላቻ የገሃነም ተምሳሌት ሊሆን ይችላል። ይህን ዓይነት ክፋት በፍቅር በመጋፋጥ ያሸነፉ እላይ የጠቅስናቸው ቅዱሳን በኢአማንያን ሥነ ሰብአውነትና በክርስትያን ሥነ ሰብአውነት ያለውን ልዩነት እንድናስተንትን ይረዱናል። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደ ተቃራኒ ኃይል ሲጋጭ የኖረ አሁኑም በዘመናችን የሁለት ሺህኛው ኢምንትነት ወይም ኒሂሊዝም ይህን ያመለክታል። ይህንን በተመለከተ በአንድ በኩል የሰው ልጅን ነፃነት ሽፋን በማድረግ በማጋነን ሁኔታው የሚያባብሱ የዘመናችን ፈላስፋዎችና ርእዮተ ዓለማውያን ከእግዚአብሔር በመራቅ ሁሉንም እንደተዛማጅ በመመልከት ሰው ራሱ የእግዚአብሔርን ቦታ በመተካት የሚገኝበት የተሳሳተና የጥፋት መንገድ የሚያራምዱ ሰዎች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በወንጌል ትምህርትና ፍቅር ሕይውታቸውን እየመሩ የተስፋቸው ምክንያት የሆነውን የእግዚአብሔር የፍቅር ገጽታ እያንጸባረቁ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን የሚገልጹና እውነተኛውን የሰው ገጽታ የሚያሳዩ ማለትም በመለኮታዊዉ እግዚአብሔር አርአያና አምሳያ የተፈጠረውን ክቡር የሰው ልጅ እውነተኛ መልክ የሚያሳዩ ቅዱሳን ናቸው’’ ብለዋል።

በትምህርታቸው ፍጻሜ ላይ ቅዱስነታቸው የቅዱሳን ሁሉ አርአያ ወደ ሆነቸው እመቤታችን በመመለስ፣ እንትድረዳን ድንግል ማርያምን እንለምናት፣ በተለይ እኛ ካህናት እንደ ቅዱሳኑ ጀግኖች የእምነት ምሥክሮች እንድንሆንና እስከ ሰማዕትነት ሕይወታችን መሥዋዕት እንድናደርግ ተረዳን ዘንድ እንለምናት። ለሰው ልጆች ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ሕይወትን መሥዋዕት የማድረግ ልዩ ትርጉም ይህ ነው፣ ይህም ለወቅቱ የዓለማችን ጥልቅ የሆነ ቀውስ ተጨባጭና ታማኝ መልስ ሊሆን ይችላል፣ በሓቅ ላይ የተመሠረተች ፍቅር መልእክትም ይህ ነው ካሉ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳረጉ።

የመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ካሳርጉ በኋላ፡ ከጣልያን አገርና ከተለያዩ ክፍለ ዓለም ከቅዱስነታቸው አብረው ለመጸለይና ትምህርታቸውን ለመስማት በካስተል ጋንዶልፎ ሓዋርያዊ አዳራሽ ግቢ ለተሰበሰቡት ምእመናን በተለያዩ ቋንቋዎች አመስግነው ሓዋርያው ቡራኬ በመስጠት የዕለቱን ጉባኤ አስተምህሮ ደመደሙ።








All the contents on this site are copyrighted ©.