2009-08-07 19:59:28

በዓለ ደብረ ታቦር / የኢየሱስ መልክ የተለወጠበት ተራራ


ትናንት የላቲን ሥርዓት የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን በዓለ ደብረ ታቦርን አከበረች፣ ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ፣ ‘ዛሬ ቤተ ክርስትያን የኢየሱስ መልክ የተለወጠበት የደብረ ታቦር በዓል ታከብራለች፣ ይህ አጋጣሚ የጨለማን ኃይል በሚያሸንፍ የእግዚአብሔር ምሥጢረ ብርሃን የልባችንን ዓይኖች በመክፈት ኢየሱስን በፍኖተ መስቀል እንድንከተለው ያሳስበናል’’ ሲሉ እንደወትሮው ዕለቱን የሚመለከት ስብከት አሰሙ፣፣

 ቅዱስነታቸው እአአ በመጋቢት 12 ቀን 2006 ዓም በመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ ይህንን በተመለከተ፣ በመቀጠል ‘ሁላችን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ከእርሱ ጋር በደብረ ታቦር እንድንኖር ለመጠየቅ በፈለግን ነበር። የእግዚአብሔርን ጣዕም ለመቅመስ ጸጋ ያገኝን እንደሆነ ልክ ሐዋርያት በደብረ ታቦር የተሰማቸውን ዓይነት ስሜት ሊሰማን ይችላል። ይህ ዓይነት ጸጋና የሕይወት ገጠመኝ ኣንዳንዴ እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች  በተለይ በመከራና በፈተና ጊዜ፣ የሚሰጥ ቢሆንም ቅሉ በዚህ ዓለም እስካለን በደብረ ታቦር ሊኖር የሚችል ማንም የለም። የሰው ልጅ ሕይወት በዚህ ዓለም ውስጥ የእምነት ንግደት ወይም ጉዞ ነው። ይህ ጉዞ የዓለም ብርሃን በሆነው ክርስቶስ ብርሃን ጭላንጭል ይመራል ኣንዳንዴም ሊጨልም ይጭላል።  በዚህ ዓለም እስካለን ሕይወታችን የሚመራው በማየት ሳይሆን እግዚኣብሔርን በመስማት ነው። ይህ ዓይነት አስተንትኖ ዓይንን ጨፍኖ በእግዚአብሔር ቃል በልባችን ባለው ብርሃን ተመርተን ልንሞክረው እንችላለን።’’ ብለው ነበር።

 እንዲሁም እአአ  በየካቲት 17 ቀን 2008 ዓም በመልአከ እግዚአብሔር ጉባኤ አስተምህሮ ቅዱሳን ጴጥሮስ ያዕቆብና ዮሓንስ የእግዚአብሔር ልጅ ክብር ያስተነተኑትን ኣመልክተው፣ ‘የደብረ ታቦር ዋና መልእክት የኢየሱስ መልክ መለወጥ የትንሣኤ ዋዜማ ነው ይህ ግን መጀመርያ መሞት እንዳለ ይገልጻል። ኢየሱስ ሓዋርያት የመስቀልን ዕንቅፋት አሸንፈው እንዲችሉ ኃይል እንዲያገኙና መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት በብርቱ ፈተና ተፈትኖ ማለፍ እንዳለ እንዲገነዘቡ ክብሩን አሳያቸው’’ ሲሉ የደብረ ታቦርን ትርጉም ገልጸው እንደነበር የሚታወስ ነው።



በሌላ በኩል በፍልስጥኤም የሚግኙ የገሊላ ምእመናን ትናንትና ጥዋት በደብረ ታቦር ባለው ቤተ መቅደስ የደብረ ታቦርን በዓል አከበሩ። የደብረ ታቦር ኮረብታ 580 ሜትር ከፍታ ያለውና ከናዝሬት ከተማ ጥቂት ኪሎሜትር ርቆ የሚገኝ ቅዱስ ኮረብታ ነው።

የበዓሉ መሥዋዕተ ቅዳሴን ያሳረጉ የቅድስት መሬት ጠባቂ ኣባ ፒየርባቲስታ ፒጻባላ ነበሩ። ቅዳሴን ተከተሎ ሥርዓተ ዑደት እንደተካሄደ ከቦታው የደረሰን ዜና ያመለክታል።

በቅዱስ መጽሓፍ በመጽሓፈ መሳፍንት እንደተመለከተው ደብረ ታቦር ከጥንት ጀምሮ እስካሁን የብዙ ውጉያዎችና ግጭቶች ቦታ መሆኑ ቢገለጽም ቅሉ ቦታው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የእስልምና ሃይማኖት በሚከተሉ ምእመናንም የተቀደሰ ነው። ቅድስት እለኒ በ4ኛው ክፍለ ዘመን ለበዓለ ደብረ ታቦር ክብር ኣንድ ትልቅ ቤተ ክርስትያን እና ለሁለቱ ትላልቅ ነቢያተ እስራኤል የሆኑ ሙሴና ኤልያስ ሁለት ቤተ ጸሎቶች አሠርታ ነበር። በግዜ ርዝመትና ሁከት ቢወድምም እንደ ቅድስትዋ ዕቅድ በ1924 ባርሉጺ በተባለ አርኪትክት ታንጾ የተባረከ ባዚሊካ ሁሉን ያካተተ ነው።








All the contents on this site are copyrighted ©.