2009-08-07 20:01:02

በማርያም ወደ ኢየሱስ


ዛሬ የፍልሠታ ምህለላና ጾም ጀምረናል። አባቶቻችን እና እናቶቻችን በተለይም ገዳማውያንና ገዳማውያት ስለሃገር ስለሕዝብ እና ስለሰላም በእመቤታችን አማላጅነት ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚቀርብ የሁለት ሱባኤ ማለትም የሁለት ሳምንት ጾምና ጸሎት ነው።

“ሰአሊ ለነ ማርያም ኀበ ወልድኪ ኄር ወመድኃኔ ዓለም” እያሉ ሊቃነ መላእክቱ ቅዱሳኑ ሰማዕታቱ ሓዋርያቱ ሁሉም ስለኛ እንዲጸልዩ ለየት ባለ መንፈሳውነትና ተጋድሎ የሚቀርብ ጸሎት ስለሆነ በልማድ ችግር በሚያገጥምበት ጊዜ ሌላ ጊዜም የምንጠቀምበት ሃብታም ጸሎት ነው።

በየዘመኑ አዲስ አስተሳሰብ ብሎም ክህደት ብቅ ይላል፣ በዘመናችንም ምናልባት ለምን በቀጥታ ኢየሱስን ራሴ ኣልምንም- አማላጅ ለምን አስፈለገ የሚል አይጠፋም ይሆናል፣፣

ይህ ችግር ቤተ ክርስትያን ከምትመሠረት የነበረ ነው፣ እንደ መልስና መፍትሔ ብዙ ትምህርት ቀርበዋል፣ የበለጠውኑ አበው በኤፌውሶን ጉባኤ ያቀረቡት ተዮቶኮስ፣ የአምላክ እናት፣ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ የሆነ ክርስቶስ እናት ብለው ያቀረቡት፣ በዮሓንስ ወንጌል ምዕራፍ 19 ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተንጠልጥሎ እያለ እናቱን ‘እናቴ ሆይ እነሆ ልጅሽ’ ደቀ መዝሙሩን ‘ይህችውልህ እናትህ’ ብሎ አደራ ያለውንና በዮሓንስ ወንጌል ምዕ 2 እናታችን ማርያም ልጅዋ ኢየሱስን ‘የወይን ጠጅ የላቸውም እኮ’ ብላ ስለተቸገሩ ማማልድዋን የሚገልጸው ትምህርት ማስታወስ ይበቃል።

ስለዚህ እምነታችን በማደስና ንስሓ በመግባት እንለምናት፣ ሰማያዊት እናታቸን በመሆንዋ የጐደለንን ነገር እንድምታስገኝልን እርግጠኛ ነኝ።








All the contents on this site are copyrighted ©.