2009-07-07 08:49:53

“ካሪታስ ኢን ቨሪታተ-ፍቅር በሐቅ”


RealAudioMP3 ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16 በቤተክርስትያን በኤኮኖሚ እና በሥነ ምግባር መካከል ያለውን ግኑኝነት የምትዳስሰው “ካሪታስ ኢን ቨሪታተ” ማለትም ፍቅር በሐቅ በሚል ርዕስ ሥር የደረስዋት አዋዲት መልእክት ነገ በይፋ ለንባብ እንደምትቀርብ ተገልጠዋል።

ቤተክርስትያን እና ኤኮኖሚ፣ ለመጪው የዓለም ኤኮኖሚያዊ ትስስር ያለው ኃላፊነት በልዩ የሚያብራራ፣ ቅዱስነታቸው እ.ኤ.አ. ታህሳስ 23 ቀን 1985 ዓ.ም. ር.ሊ.ጳ. ሆነው ከመሾማቸው በፊት እዚህ ሮማ በሚገኘው ጳጳሳዊ ኡርባኒያኑም መንበረ ጥበብ ተገኝተው የሰጡት አስተምህሮ እ.ኤ.አ. በ 1986 ዓ.ም. በተባበሩት የአመሪካ መንግሥታት ኮሙኒዮ ዩኤስኤ በተሰየመው መጽሔት ታትሞ በኢጣሊያ በ 2009 ዓ.ም. ዳግም የታተመውን የሚያንጸባርቅ ስነ አመለካከት ዋቢ ያደረገ መሆኑም ተገልጠዋል።

አዋዲ መልእክቱም ቤተ ክርስትያን እና ኤኮኖሚ በሚል ርእስ ሥር፣ ለዓለም ማኅበረሰብ እጅግ አስጊ የሆነው እና ለአደጋ የሚያጋልጠው በሰሜንና በደቡብ ያለማችን ክፍል ያለው ያልተስተካከለ የእድገት ልዩነት ምንኛ አደገኛና ህልውናን የሚቀናቀን መሆኑ በስፋት ተብራርቶ መፍትሔውም ገቢራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ መስሎ የሚታየውን የግብረ ገባዊ ተሃድሶ ወሳኝ መሆኑ ያበክራል። ምናልባት ቤተ ክርስትያን እና ኤኮኖሚ ምን ያገናኛቸዋል የሚል ተገቢ ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፣ ሆኖም ግን ቤተ ክርስትያን በዚህ ምድር የምትጓዝ በማኅበራዊ ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጨባጭ ጉዳዮች ሓቅን መሠረት የሚያደርግ ግኑኝነት እንዳላት መገንዘቡ አስፈላጊ ነው።

አጥጋቢነት እና ግብረ ገብነት፣ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ኤኮኖሚ የገዛ ራሱ ሥርዓት እንዳለው እና ነጻና እራሱን ችሎ የሚተዳደር መሆኑ በማብራራት፣ በራሱ መመሪያ የሚተዳደር እጅግ ጣልቃ ገብ በሆነው ውጫዊ የግብረ ገብ ሥርዓት የሚመራ እንዳልሆነ ቢያብራራም፣ ከ1723 እስከ 1790 ዓ.ም. የኖረው የኤኮኖሚ ሊቅ እና ፈላስፋ አዳም ስሚዝ የንግዱ ዓለም ወይንም የገበያው ዓለም ከስነ ምግባር ጋር የማይስማማ ምንም ዓይነት ተምሳይነትም ይሁን ግኑኝነትም የለውም ይላል፣ ስለዚህ ግብረ ገብ መሠረት ያደረገ የገበያ ሂደት ከዓለም ንግድ ውጭ ነው የሚል አመለካከት በማሳድሩ ረገድ፣ በሚሰጠው ውጤት እና አጥጋቢነቱ እንጂ በግብረ ገብ እንደማይለካ በማሳመኑ፣ ይህ ዓይነት አመለካከትም ቁጠባ ወይንም ኤኮኖሚ በግብረ ገብ ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሌለበት ለማሳመን ችለዋል። ስለዚህ ይህ ዓይነት የኤኮኖሚ ሂደት በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን የሚታየው የኑሮ ልዩነት እያስፋፋ በሰሜኑ እና በድሃው ዓለም ዓቢይ ልዩነት አስከትለዋል። ትርፍ ማካበት እንጂ ተገቢነት ወይንም ግብረ ገብ ግድ የማይሰጠው የኤኮኖሚ ሂደት በዓለማችን እንዲስፋፋ አደረገ።

መዋቅራዊ ኢፍትኅዊነት፣ በኤኮኖሚ እና በግብረ ገብ በተመለከተ ያለው ችግር በአሁኑ ሰዓት ፅንሰ ሐሳብ ወይንም ኅልዮ ብቻ ሳይሆን ገቢራዊ እየሆነ፣ እየጎላ መሄድ የጀመረው የኤኮኖሚ ልዩነት እ.ኤ.አ. ከ 1950 ዓ.ም. መፍትሔ እንዲያገኝ ሁሉንም አነቃቃ፣ የሁሉም ፍላጎት ሆነ። ይህ ደግሞ የኤኮኖሚው ሚዛን ልማት መሆኑ ታምኖበት፣ ጥረት መደረግ ተጀመረ፣ ሆኖም ግን ጥረቱ የተከተለው መንገድ የተሳሳተ መሆኑ፣ ለሁሉም የተሰወረ አይደለም፣ እንዲያውም የኑሮ የልማት ልዩነት እጅግ እየባሰ በድሃውና በሃብታሙ መካከል ያለው ልዩነት እያደገ እንዲሄድ አድርጎአል። በተለይ ደግሞ ድሃ አገሮች የሚባሉት ተስፋ ያደረጉበት የኤኮኖሚና የድጋፍ ሂደት የመበዝበዣ መሣሪያ ሆኖ፣ ይባስም መዋቅራዊነት እየለበሰ መጥተዋል።

ስለዚህ ይህ ሁሉ ችግር በኤኮኖሚው ዓለም ግብረ ገብነት ምንኛ አስፈላጊ መሆኑ እያጎላ፣ ራስ ወዳድነት እኔነትን ማእከል ያደረገው ኤኮኖሚ ያስከተለውና እያስከተለው ያለው ቀውስ ለሁሉም ግልጽ ነው፣ ኤኮኖሚና ግብረ ገብነት ለማጣመር በተለይ ደግሞ የኤኮኖሚው አጥጋቢነቱ በሚከተለው ግብረ ገብ የሚለካ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥተዋል።

ርሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ እ.ኤ.አ. ሰኔ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በኤኮኖሚና በነጻነት መካከል ያለው ግኑኝነት በኃላፊነት ላይ የጸና መሆን እንደሚገባው፣ እርሱም ሃይማኖታዊ ስነ ምግባር ማእከል ያደረገ መሆን እንዳለበት አስታውሰው እንደነበር የሚዘከር ነው። የኤኮኖሚው ሥርዓት ስነ ምግባር መሠረት ማድረግ እንዳለበት በዚህች ፍቅር በሐቅ በተሰኘችው አዋዲት መልእክት የሚሰጡት መሪ ትምህርት በቤተክርስትያን ብቻ ሳይሆን፣ ከቤተክርስትያን ውጭ የኤኮኖሚ እና የፍልስፍና ሊቃውንት የሚያምኑበት፣ ለወቅታዊው ያለማችን የኤኮኖሚው ሂደት መሠረት መሆን እንደሚገባው የታመነበት ነው።

በላተራነንሰ ጳጳሳዊ መንበረ ጥበብ የኤኮኖሚ የፖለቲካ መሠረታዊ ትምህርት እና የኤኮኖሚ ፍልስፍና መምህር ፍላቪዮ ፈሊቸ “ካሪታስ ኢን ቨሪታተ” ማለትም ፍቅር በሐቅ በሚል ርእስ ሥር የደረስዋት አዋዲት መልእክት በማስመልከት ከቫቲካን ረድዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፣ “ግብረ ገብና ኤኮኖሚ ጉዳይ በተመለከተ ጥናትና ውይይት ከተጀመረ 40 ዓመት ሆኖታል፣ ኤኮኖሚ ምን ማለት ነው፣ ስነ ምግባርስ ምን ማለት ነው፣ ኤኮኖሚ የሚከተለው ወይንም ሊከተለው የሚገባው ስነ ምግባር ሲባል ምን ማለት ነው? ኤኮኖሚ በሚሰጠው ፈጣን ጥቅም እየተለካ በመምጣቱም፣ የኤኮኖሚው ሚዛን ስነ ምግባር ሳይሆን የሚሰጠው የአስቸካይ ጥቅም እየሆነ፣ ሁሉም በሚሰጠው ጥቅም አንጻር ብቻ የሚለካ ባህል በማስፋፋቱም፣ ከዚህ ጋር የሚስማማ ስነ ምግባር ተፈጠረ፣ ስለዚህ በዚህ ጥቅም አንጻር ማህበራዊ ፖለቲካው እየተገነባ መጣ፣ ይኸንን እግምት ውስጥ ያስገባው የቤተክርስትያን የማኅበራዊ ጉዳይ ትምህርት ግን ለየት ባለ መልኩ ሰው በእግዚአብሔር አርኣያና አምሳያ ተፈጠረ ከሚለው ክርስትያናዊ ስነ ሰብአዊ ትምህርተ መሠረት ያደረገ ስነ ምግባር የሚያብራራና ይኸንን ስነ ምግባር ር.ሊ.ጳጳሳት በተለያየ ወቅት በሚደርሷዋቸው አዋዲ መልእክቶች በተለያየ አቅጣጫ የሚተነትኑት ጉዳይ መሆኑ ገልጠዋል”።








All the contents on this site are copyrighted ©.