2009-07-01 18:14:30

የቅዱስ ጳወሎስ ዓመት የተፈጸመ ቢሆንም ቅሉ በረከቱና ጸጋው ግን ቀጣይነት አለው


የቅዱስ ጳውሎስ የኢዮቤል ዓመት እ.ኤ.አ. ባለፈው ሰኔ 28 ቀን 2009 በተለያዩ የጸሎትና የቅዳሴ ሥነ ስርዓቶች መጠናቀቁ የሚዘከር ሲሆን፣ ለዚህ ዓብይ ዓመተ ኢዮቤል መዝጊያ ከትላትና በስቲያ እዚህ ሮማ ፎሪ ለ ሙራ በሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ባሲሊካ፣ ሊቀ ካህናት ብፁዕ ካርዲናል አንድረያ ኮርዴሮ ላንዛ ዲ ሞንተዘሞሎ የመሩት ሁለተኛው የሠርክ ጸሎት እና መሥዋዕተ ቅዳሴ መቅረቡ ለማወቅ ተችለዋል።

ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ የዚህ ዓብይ የአሕዛብ ሓዋርያ ቅዱስ ዓመት ኢዮቤል መዝጊያ በዓለ ቅዱሳን ሓዋርያት ጴጥሮስ ወጳውሎስ ምክንያት አንደኛውን የሠርክ ጸሎት መምራታቸው ተገለጠ። በዓሉ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስ በሰበከባቸው አገሮች በቱርክ በግሪክ በስርያ በሊባኖስ እና በማልታ ደምቆ እንዲከበር ያቀረቡት ጥሪ ገቢራዊ መሆኑ ለማወቅ ተችለዋል።

ሰኔ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ፣ የቁስጥንጥንያ አንድነታዊ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ በርጠሎሚዮስ አንደኛ በተገኙበት በይፋ ያስጀመሩት የቅዱስ ጳውሎስ ዓመት፣ ብፁዕ ካርዲናል አንድረያ ኮርደሮ ላንዛ ዲ ሞንተዘሞሎ የቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል ምክንያት በቅዱስ ጳውሎስ ባሲሊካ በመሩት ሁለተኛው የሠርክ ሥርዓተ ጸሎት ተጠናቀዋል። ብፁዕነታቸው ሁለተኛው የሰርክ ጸሎት በመምራት ባሰሙት ስብከት፣ የቅዱስ ጳውሎስ ዓመተ ኢዮቤል ተጠናቀዋል ስንል በዚህ ዓመት ምክንያት የተገኘው የእምነት የፍቅር የተስፋ ጸጋ እና በአማኞች ዘንድ ያለው እምነት ከፍ ማድረጉ ገልጠዋል። ይህ ቅዱስ ለክርስትያን አንድነት መረጋገጥ ያነቃቃ፣ መከፋፈልን መሠረታዊ ተሎጊያዊና ሥነ ቤተ ክርስትያናዊ ምክንያቶች በማቅረብ ያወገዘ መሆኑ ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ የቅዱስ ጳውሎስ ዓመተ ኢዮቤል ምክንያት በተለያየ ወቅት በሰጡት ሥልጣናዊ ትምህርት መጥቀሳቸው ብፁዕ ካርዲናል አንድረያ ኮርደሮ ላንዛ ዲ ሞንተዘሞሎ በማስታወስ፣ በመጨረሻም የዚህ የቅዱስ ጳውሎስ ዓመት ጸጋና በረከት በሁሉም ዘንድ ሕያው እንዲሆንና የክርስትያኖች አንድነትም እንዲረጋገጥ ቅድስት ድንግል ማርያም ታማልድልን ዘንድ ጸልየዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.