2009-06-15 15:03:12

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ ከመቶኛ ዓመት ማኅበር አባላት ጋር ተገናኝተዋል፡


ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ መቶኛ ዓመት የተሰየመ ማኅበር አባላት ተቀብለው ማነጋገራቸው ከቫቲካን የተገኘ ዜና አስታውቀዋል። ማኅበሩ እኤአ 1993ዓ.ም በነፍሰኄር ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተመሠረተ ሲሆን ዋነኛ ዓላማው የዓለም አቀፍ አሠሪዎች እና የኤኮኖሚ ባለጠጋዎች የቤተክርስትያን ማኅበራዊ ትምህርት መርኆዎች ለማወቅ ለማሰራጨት የቆመ መሆኑ የሚታወስ ነው።

ቅዱስ አባታችን ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እኤአ ብ1991ዓ.ም ‘ቸንተሲሙስ አኑስ’ መቶኛ ዓመት የተሠየመ ሐዋርያዊ መልእክት ለዓለም ሕዝቦች ማሰራጨታቸውም የማይዘነጋ ነው ።

ቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት፡ የማኅበሩ አባላት ተቀብለው ባነጋገሩበት ግዜ እንዳሉት ፡ ዓለም አቀፋዊ የኤኮኖሚ እና ፋይናንስ ቀውሶች ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት የሕዝቦች እና የደካማ ማኅበረሰቦች መብቶች ማክበር በሥነ ምግባር እና ትብብር የተመረኮሰ ኤኮኖሚ መቀየስ ያስፈልጋል። ንግግራቸው በማያያዝ የማኅበሩ አባላት ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ኤኮኖምያዊ ሁኔታ በተመለከተ ሲወያዩ መሰንበታቸው የሚታወስ ሲሆን፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ እንደገለጡት፡ የብልጽግና አዲስ ዘይቤዎችን ተፈልገው መገኘት አለባቸው።

የሰው ልጅ ማእከል ያላደረገ እና ከትብብር የራቀ ማንኛውም የኤኮኖሚ መዋቅር ዘላቂ ሊሆን እንደማይችል ያመለከቱ፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሰው ክብር እሴቶች መጠበቅ እና አዲስ የኤኮኖሚ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ማስገንዘባቸው ተነግረዋል። በዚሁ ከቫቲካን በተገኘ ዜና መሠረት፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ ከየመቶኛ ዓመት ማኅበር አባላት ጋር በተገናኙበት ግዜ፡ በሚቀጥለው ቅርብ ግዜ ይፋ የሚሆነውን ሐዋርያዊ መልእክታቸው ኤኮኖሚ እና ሥራ እንደሚመለከት ማውሳታቸው እና ማኅበራዊ እና ነፃ ሰብአዊ ኑሮ እውን ለማድረግ ክርስትያኖች መከተል ያለባቸው ክርስትያናዊ እሴቶች የሚያሳይ ሐዋርያዊ መልእክት መሆኑ ከወዲሁ አመልክተዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.