2009-06-05 15:56:21

የብፁዕ አቡነ ኪዳነማርያም ፀሎተ ፍታት ተከናወነ


የብፁዕ አቡነ ኪዳነማርያም ፀሎተ ፍታት ሀሙስ ግንቦት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በ11፡30 በአዲስ አበባ ልደታ ማርያም(ካቴድራል) ቤተክርስቲያን ወዳጅ ቤተዘመዶቻቸው በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

የፍታት ስነስርዓቱን የመሩት ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሲሆኑ በስነስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት፣ ብፁዕ ሊቀጳጳሳት ጆርጅ ፓኒኩለም በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ተወካይ፣ ክቡር አቶ ስዩም መስፍን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ሌሎች የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተወካዮች፣ ቤተዘመዶቻቸው፣ በርካታ ካህናት፣ ደናግልና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

ብፁዕ ሊቀጳጳሳት ብርሃነየሱስ የብፁዕነታቸውን የህይወት ዘመን አገልግሎት የገለፁ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ጳጳስ ከብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ የተላከውን የሃዘን መግለጫ በንባብ አሰምተዋል፡፡

የብፁዕነታቸው ስርዓተ ቀብር ቅዳሜ ግንቦት 29 ቀን 2001 ዓ.ም. በአዲግራት እንደሚፈጸም ተገልጿል፡፡

ብፁዕ አቡነ ኪዳነ ማርያም ባደረባቸው ህመም ከሁለት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በአዲስ አበባና በሮማ ከተማ ህክምና ሲደረግላቸው የቆየ መሆኑ ይታወሳል፡፡



የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት

ማህበራዊና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ








All the contents on this site are copyrighted ©.