2009-05-09 19:26:27

የቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. አሥራ ሁለተኛው አገራት አቀፍ ሐዋርያዊ ጉዞ ተጀመረ


ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ዛሬ ጥዋት ወደ ቅድስት መሬት የሚያደርጉትን አሥራ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጉብኝት መጀመራቸው ተመለከተ።

ቅዱስነታቸው እ.አ.አ. በያዝነው ወር ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ማርያማዊ ሥርዓተ ጸሎት በመሩበት ለምእመናን ባስተላለፉት መልእክት፤ “ከእኔ በፊት የነበሩትን የብፁዓን አርእስተ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛና ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ዱካን ተከትዬ፤ የእምነታችን ታላላቅ ቅዱስ ሥፍራዎች እጐበኛለሁ። በመንፈሳዊ ጉብኝቴ በየቀኑ ብዙ ችግር የሚያሳልፉትን የቅድስት መሬት ክርስትያንን ለማጽናናትና ለማበረታታት አስባለሁ እንደ ጴጥሮስ ተከታይም የመላዋ ቤተ ክርስትያን ቅርበትና ድጋፍ እንደማይለያቸው አረጋግጥላቸዋለሁ። ከዚህም ሌላ የሁሉም አባት በሆነው በእግዚአብሔር ስም የሰላም ጐብኚ እሆናለሁ። ፍትህ የእርስ በእርስ መከባበርን ውይይትና የምሕረት ተግባርን በመፈጸም ቀዋሚና ዘላቂ ሰላም ላይ ለመድረስ ለሚተጉ ሁሉ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን የምትሰጠው ድጋፍና ታዋቂነት እመሰክራለሁ። በመጨረሻም ጉብኝቴ ለክርስትያን አንድነትና ለሃማኖቶች የእርስ በእርስ ግኑኝነት መጐልበት የሚሰጠው ጥቅም ይኖራል ብዬ አምናለሁ፣ በዚህ ዓይን ከተመለከትነው የተበተኑትን የእግዚአብሔር ልጆችን ሁሉ በአንድነት ለመሰብሰብ ክርስቶስ የሞተው እዛ ስለሆነ የኢይሩሳሌም ከተማ ልዩ ተምሳሌት ናት”። ሲሉ የቅድስት መሬት መንፈሳዊ ንግደታቸው ዓላማና ትርጉም ምን እንደሆነ ገልጠው ነበር።

ታዲያ ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ እንደ መንፈሳዊ ጉብኝቱ መርኀ ግብር መሠረት ዛሬ ጥዋት ከሮማው የፊዩሚቺኖ ዓለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ በሮማ ሰዓት አቆጣጠር ልክ ዘጠኛ ሰዓት ተኩል ተነስተው በአሊታሊያ A321 የአራት ሰዓት የበረራ ጉዞ ካደረጉ በኋላ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ አማን ዮርዳኖስ ርእሰ ከተማ ንግሥት አሊያ ዓለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ በሰላም ገብተዋል።

ቅዱስነታቸው በበረራው ጉዞ ውስጥ በአየር ክልላቸው ያለፉባቸው መንግሥታት ኢጣልያ፤ ግሪክ፤ ቆጵሮስ፤ ሊባኖስና ሶርያ ናቸው። ለመንግሥታቱ መሪዎችና ሕዝቦች የመልካም ምኞት ሰላምታና ሓዋርያዊ ቡራኬ የያዘ ተለግራም ልከዋል።

በር.ሊ.ጳ. ፕዮስ አሥራ ሁለተኛ ፍላጐትና ፈቃድ እ.አ.አ. ከ1948 ዓ.ም. ወዲህ በቅድስት መንበርና በቅድስት ሃገር መካከል ጉዳይ አስፈጻሚ ሐዋርያዊ ልኡክ እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን፤ ሐዋርያዊ መልእክተኛው እስራኤል ዮርዳኖስና የቆጵሮስ ደሴትን የሚወክል ነበር። በ1994 ዓ.ም. በቅድስት መንበር በእስራኤልና በዮርዳኖስ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት ከተደረገ በኋላ ግን ሐዋርያዊ ውክልናው ለየብቻው ኢዮርሳሌምንና የጳለስጢና ነፃ ግዛቶችን ማለት ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ያሉትን ግዛቶችና የጋዛ ሰርጥን እንዲሁም ዮርዳኖስን ያጠቃልላል። በመሆኑም በቅድስት መሬት ሁለት ሐዋርያውያን መልእክተኞች ሲገኙ፤ አንዱ ዮርዳኖስ አማን ውስጥ፣ ሌላው እስራኤል ተልአቪቭ ከተማ ውስጥ አንድ ሌላ ሐዋርያዊ ወኪል ደግሞ ለብቻው በኢየሩሳሌም ከተማ ይቀመጣል።

ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ከክብር ተከታዮቻቸው ጋር በንግሥት አሊያ ዘአማን አይሮፕላን ማረፊያ እንደደረሱ፤ የዮርዳኖስ ሐዋርያዊ ወኪል ብፁዕ አቡነ ፍራንሲስ ኣሲዚ እና የአስተናጋጆች ፕሮቶኮል ሓላፊ አይሮፕላን ውስጥ ገብተው ሰላምታ አቅርበውላቸዋል። ከአይሮፕላኑ እንደወረዱም የተከበሩ የዮርዳኖስ ንጉሥና ንግሥት፣ የመንግሥትና የፖሎቲካ በለሥልጣናት፣ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት፣ ልኡካነ መንግሥታት፣ የቅድስት መሬት ካህናትና መንፈሳውያን መሪዎች፣ ፓትርያርኮች አቡናትና አንድ የዓለማውያን ምእመናን ቡድን፣ እጅግ ደማቅ የክብር አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በአቀባበሉ ሥርዓት ላይ የክብር ዘብ ሰልፍ ታይቶአል። የሁለቱ መንግሥታት ብሔራዊ መዝሙሮች ተዘምሮአል። የዮርዳኖስ ንጉሥ ክቡር ዓብደላ ሁለተኛ ቢን አልሑሰን የእንኳን ደኅና መጡ ንግግር አሰምተዋል። ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ለንጉሥ ዓብደላ የአስረኛው ዘመነ ንግሥናቸው መታሰቢያ ዓመት የመልካም ምኞት መልእክት ያስተላለፉበት፣ ንጉሡ ለሚሰጡት ለዘብተኛና ጭምት እስላማዊ አስተዳደደር ያሞገሱበት፣ የዮርዳኖስ መንግሥትና ሕዝብ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም በማስፈን በሃይማኖቶች የእርስ በእርስ ውይይቶች፣ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት፣ ስደተኞችን በማስተናገድና ጽንፈኛ አክራሪነትን በማስወገድ ረገድ ያለውን ሚና በማድነቅ ያስረዱበት የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዓላማና ትርጉም ገልጠው፣ ስለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ያመሰገኑበት የመጀመርያ ንግግራቸውን አሰምተዋል።

ቅዱሱ አባታችን ከአማን አይሮፕላን ማረፊያ ጉብኝታቸውን ለመቀጠል በመኪና በሃያ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ረጂና ፓቺስ - ንግሥተ ሰላም በመባል ወደ ሚታወቀው የአካለ ስንኩላን የመልሶ ማቋቋምና የወጣቶች መልሶ ማዋሃድ ማእከል ሄደዋል። እዛም የማእከሉ መስራች ብፁዕ አቡነ ሳሊም ሳገ የዮርዳኖስ ላቲናዊ መንበረ ጵጵስና ህየንተ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በአካለ ስንኩላን መልሶ ማቋቋም ማእከል ባሰሙት ሁለተኛ ንግግራቸው፣ በንግሥተ ሰላም ማእከል ከእያንዳንዳቸው ጋር መገናኘታቸው እጅግ እንደሚያስደስታቸው ገልጠው፣ ለሁላቸው የሰላምታ ቃል አቅርበዋል።

ማእከሉን ላቋቋሙት ብፁዕ አቡነ ሰሊም ሳገ በማድነቅ አመሰግነዋል፣ ልሂቀ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ሚኸኤል ሳባሕም ለቤተ ክርስትያን ላበረከቱት አገልግሎት አመስግነዋል። በማእከሉ ውስጥ አገልግሎት ለሚሰጡት ደናግልና ሠራተኞችም አበራርተዋል። ለወጣቶቹም እምነት ከራሳችን ባሻገር እግአብሔር ለሕይወት የሚሰጠውን ትርጉም ለመገንዘብ ያስችለናል ብለው በእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር አምነው በተስፋ እንዲበረቱ መክረዋቸዋል በጸሎት እንዲበረቱም አሳስበው፣ እግዚአብሔር ለቅድስት መሬት ሰላም እንዲያወርድ ተመኝተዋል፣ ለሁላቸው እና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለማእከሉ ለሚረዱት ግብረ ሠናያን የሰላም ንግሥት የሆነችው እመቤታችን እንድትባርካቸው ተመኝተው ሓዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት ተሰናብተው፣ አማን ውስጥ ወደሚገኘው የቅድስት መንበር ሓዋርያዊ ልኡክ አደራሽ ሄደዋል፣ ከቀትር በኋላ አራት ሰዓት ተኩል ወደ ቤተ መንግሥቱ በመሄድ ለዮርዳኖስ ንጉሥና ንግሥት የክብር ጉብኝት አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው የዮርዳኖስ ቤተ መንግሥት ጉብኝት ከፈጸሙ በኋላ ወደ ዮርዳኖሱ ሐዋርያዊ ልኡክ መኖሪያ ሓዋርያዊ አደራሽ ማምሻውን በመኪና ተመልሰዋል። እዛም ከምሽቱ ሰባት ሰዓት ላይ የእራት ግብዣ ተደርጐላቸው ለዕለቱ ያሉትን የመንፈሳዊ ጉብኝት ፕሮግራም በማታ ጸሎትና ዕረፍት ደምድመዋል።







All the contents on this site are copyrighted ©.