2009-05-06 14:32:25

የካቶሊክ ሃይማኖት ትምህርት በኤውሮጳ፡


የኤውሮጳ ጳጳሳት ጉባኤ ምክር ቤት እና የጣልያን ረኪበ ጳጳሳት በጋራ በቀሰቀሱት መሰረት፡ በፈረንሳ ስትራስበርግ በሚገኘው የኤውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት በብዙሀ-ሃይማኖት አቀፍ ኤውሮጳ የካቶሊክ ሃይማኖት ትምህርት የተሰኘ ርእስ፣ ለውይይት መቅረቡ ከዚሁ ቦታ የመጣ ዜና አስታውቀዋል።

የኤውሮጳ ምክር ቤት አባላት የኤውሮጳ ጳጳሳት ጉባኤ ምክር ቤት ሊቀመንበር ብፁዕ ካርዲናል ፐተር ኤርዶ እና የጣልያን ረኪበ ጳጳሳት ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ማርያኖ ክሮችያታ እንዲሁም ከመላ ኤውሮጳ የተዋጡ የተለያዩ ሃይምኖቶች ተከታዮች በዚሁ ውይይት ተሳታፊ መሆናቸው ዜናው አስገንዝበዋል።

ምዕራቡ እና ምሥራቁ ኤውሮጳ በመዋዕለ ንዋይ ብቻ ከማተኰር ክርስትያናዊ እሴቱ አጥብቆ መያዝ እንደሚጠበቅበት በኤውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት የቅድስት መንበር ቀዋሚ ታዛቢ ብፁዕ አቡነ አልዶ ጂዮርዳኖ ለተሳታፊዎች መግለጣቸው ከስትራስበርግ የመጣ ዜና አመልክተዋል።

የኤውሮጳ ምክር ቤት አባላት በመላ ጐደል ትምህርተ-ሃይማኖት ለኤውሮጳዊ ሕብረተሰብ ሥነ ምግባራዊ ሀብት መሆኑ እና ጤናማ ኅብረተሰብ እውን ለማድረግ ሁነኛ ሚና እንደሚጫወት በንግግራቸው ላይ መግለጣቸው በምክር - ቤቱ ተገኝተው ውይይቱ የተከታተሉ መገናኛ ብዙኀን ያመለክታሉ።

በሕይወት የመኖር ትርጉም ግልጥ እና ገሀድ የሚሆነው በትምህርተ ሃይማኖት እንጂ በገንዘብ ብዛት እንዳልሆነ እና የኤውሮጳ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የሃይማኖት ትምህርት እንዲሰጡም የአብያተክርስትያን ወኪሎች አፅንኦት ሰጥተው መጠየቃቸው ተያይዞ የደረሰ ዜና ገልጠዋል።

የሃይማኖት ታሪክ የሃይማኖት ማኅበራዊ ትምህርት የሃይማኖት ፍልስፍና እንዲሁም ነገረ መለኮት መሠረታውያን ትምህርቶች እንደሆኑ ስትራስበርግ ላይ በሚገኘው የኤውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት የተገኙ ልኡካን እንደተስማሙበትም ተነግረዋል።

የኤውሮጳ ጳጳሳት ጉባኤ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ፐተር ኤርዶ እንዳመለከቱት ከረጂም ግዜ በፊት የተለያዩ የኤውሮጳ መንግሥታት፤ ሕጻናት የመንግሥት ርዕዮተ ዓለም ብቻ እንዲማሩ በማስገደድ ትርምስ ፈጥረው ነበር። አሁን ይህ ሁሉ የለም። የሃይማኖት ትምህርት አስፈላጊነት መሰረታዊ መሆኑ ለማንኛውም ግልጽ ሁነዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.