2009-05-04 15:51:45

ር.ሊ.ጳ. ለመንፈሳዊ ጥሪ መበራከት እና ለቅ. መሬቱ ጉብኝታቸው መቃናት ጸሎት እንዲደረግ ጠየቁ።






ቅ.አ.ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ 16ኛ ትላንት እሁድ እኩለ ቀን በመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎተ ሥርዓት ባስተላለፉት መልእክት፣ ስለ መንፈሳውያን ጥሪዎችና በቅርቡ ወደ ቅድስት መሬት ስለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ጸሎት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ቅዱስነታቸው ትናንት ማርያማዊ ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ቃልና ይዞታው እንደሚከተል ነው፥

ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ ለአሥራ ዘጠኝ የሮማ ሰበካ ዲያቆናት መዓርገ ክህነት የሰጠሁበት መስዋዕተ ቅዳሴ አሁን ጨርስኩኝ፣ ይህንን የክህነት መዓርግ በዛሬው በአራተኛው የትንሣኤ እሁድ እንድሰጥ የወሰንኩበት ምክንያት የዕለቱ ቃለ ወንጌል ስለ መልካሙ እረኛ በመሆኑና ለበዓሉ የሚስማማ አጋጣሚና ሁኔታ ስለሚሰጥ ነው።

እንዲሁ በመሆኑም የመንፍሳዊ ጥሪዎች ጸሎት የዓለም ቀን ዛሬ ይከበራል። ቀኑን በማስመልከት ለዘንድሮው አስተንትኖ ያስተላለፍኩት መልእክት ርእሰ ጉዳይ “መጀመሪያ እግዚአብሔር እንደሚጠራ አምኖ ሰው የሚሰጠው መልስ” የሚል ነው፣ በጸሎቱ በቀጣይ ለቅድስና ላንዳንዶቹም ለልዩ ቅድስና በሚጠራው እግዚአብሔር ስለ ማመን ተገልጦአል። በግልና በማኅበር የእግዚአብሔር ታላቅነትና የፍቅሩ ውበት ብዙዎችን በክህነት ጐዳናና በልዩ መንፈሳዊ ጥሪ ክርስቶስን እንዲከተሉ እንዲመስጣቸው ለመንፈሳውያን ጥሪዎች አብዝተን መጸለይ ይገባናል። እንዲሁም ልጆቻቸውን በነጻነታቸው እንዲከተሉ ከሁሉም በላይ በአርአያነታቸው ሊያሳይዋቸው የሚችሉ ቅዱስ ቤተሰቦች እንዲገኙ ጸሎት ማድረግ ያስፈልጋል። ቤተ ክርስትያን እንዲያከብሩና በነርሱ በኩል አማላጅነት እንዲቀርብ ከምእመናን ወስዳ የምትጠራቸው ቅዱሳን ወንዶችና ሴቶች በመለኮታዊ ጥሪና በሰው ልጅ መልስ መካከል ስላለው ውህደት በሳል ምስክሮች ናቸው፣ ለመንፈሳውያን ጥሪዎች የምናደርገውን ጸሎት በእነርሱ አደራነት በኩል እናድርገው።

ዛሬ ስለ ሌላው አሳብም እንድትጸልዩ እጋብዛችሁአለሁኝ፣ ይህም እ.ኤ.አ. ከፊታችን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን ጀምሮ እስከ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ቅድስት መሬት ስለ ማደርገው ሐዋርያዊ ጉዞ ነው። ከኔ በፊት የነበሩትና የተከበሩት አርእስተ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛና ዮሓንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ፈለግ በመከተል የእምነታችን ዋና ዋና ቦታዎችን ለመጐብኘት ወደ ቅድስት መሬት መንፈሳዊ ንግደት አደርጋለሁ፣ በጉብኝቴ በየቀኑ ብዙ ችግሮች በማሳለፍ ላይ ያሉትን የቅድስት መሬት ክርስትያን ለማጽናናት አስባለሁ፣ እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ተከታይ የመላው ቤተ ክርስትያን ቅርበትና ድጋፍ አሳያለሁ፣ ከዚህም በተጨማሪ የሁሉም አባት በሆነው እግዚአብሔር ስም የሰላም መንፍሳዊ ጎብኚ እሆናለሁ፣ በጽኑ ዘላቂ ሰላም ፍትሕና የእርስ በእርስ መከባበር ላይ ለመድረስ ውይይትና ምህረት ለሚያስቀድሙት ባለ በጎ ፈቃድ ሰዎች ሁሉ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን የምትሰጠውን ድጋፍ እመሰክራለሁ።

በመጨረሻም ይህ ጉዞ የክርስትያናዊ አንድነትና የሃይማኖቶች የርስ በርስ ግኑኝነት ትርጉምና አስፈላጊነት ያለው ይሆናል። ከዚሁ አኳያ ኢየሩሳሌም ከፍተኛ ምሳሌነት ያላት ከተማ ናት እዛ የተበተኑትን የእግዚአብሔር ልጆች እንደገና ለመሰብሰብ ክርስቶስ ሞቶአል፣ ዮሓንስ ወንጌላዊ በአሥራ አንደኛው ምዕራፉ ቍጥር አምሳ ሁለት ላይ “የሞተው ስለ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን የተበተኑትንም የእግዚአብሔር ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው” በማለት ይህንን ሓቅ አረጋግጦልናል።

አሁን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ፊታችን ስናዞር የደጉ እረኛ እናት መሆኑዋን በማስታወስ ዛሬ ክህነት የተበቀበሉትን የሮማ ሰበካ ካህናትን እንድትጠብቅልን እና በመላው ዓለም የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲስፋፋ ብዙ መንፈሳውያን ጥሪዎች እንድትሰጠን እንለምናት ብለው ማርያማዊ ጸሎትን አሳረጉ።









All the contents on this site are copyrighted ©.