2009-04-29 15:50:06

ቅዱስ ኣባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ አሥራ ስድስተኛ በአብሩጾ በመሬት መንቀጥቀጥ ለተጐዱ ወገኖች ጐብኝተዋል


ቅዱስ አባታችን ትናንት ረፋድ በተያዝነው ወር መጀመርያ ላይ በኃይለኛ የመሬት መናወጥ የተጐዳውን የአብሩጾ ክፍለ ሃገር ሕዝብ ጐበኙ። በመጀመርያ የጐበኝዋት የኦና ከተማ ስትሆን፣ የላ’አኲላ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጁሰፐ ሞሊናሪና የሕዝብ ጥበቃ (ፕሮተስዮነ ቺቪለ) ሓላፊ ሲኞር በርቶላሶን፣ እንዲሁም የክፍለሃገሩ የቤተ ክርስትያንና የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሕዝቡ ጋር ተቀበልዋቸዋል።

ቅዱስነታቸው አደጋው ከተከሰተበት እስካሁን በብርድና ብዝናም ሥር በተንዳ የሚኖሩ ሕዝብ ሁኔታ እጅጉ እንዳሳዘናቸው ገልጸው “አይዞአችሁ፣ ብቻችሁ አትሆኑም፣ እያንዳንዳችሁን የጋለ ሰላምታዬን አቀርብላችዋለሁ” ሲሉ የአደጋውን ዜና ከሰሙ ጀምሮ ዘወትር በመንፈስ እጐናቸው መሆናቸውን አረጋገጡላቸዋል።

በመርሓ ግብሩ መሠረት፣ የተጐዳውን ወገን በሄሊክፕተር እንዲያዩ ታቅዶ የነበረ በዕለቱ በተከሰተው የአየር ጠባይ ስላልተቻለ፣ የተቻለውን በመኪና ተዘዋውረው ታዝበዋል። በኦና ከተማ ሕዝቡን አጽናንተው ከሕዝቡ አብረው በተለይም በአደጋው ስለሞቱት የሚከተለውን ጸሎት ኣሳርገዋል፣

“ጌታ ሆይ በሞት የምእመናንህን ሕይወት እንደምትለውጥ በማወቅ በዚህ አደጋ ለሞቱትን ሁሉ ላንተ እናማጥናቸዋለን፣ ለጊዜው ነጋድያን ሆነን በምንኖርበት ዓለም መኖሪያዎቻችን በወደመበት ጊዜ ዘለዓለማዊና የማይበርስ በመንግሥተ ሰማያት እንደምታዘጋጅልን እናምናለን፣ የሰማይና የምድር ጌታ ቅዱሱ ኣባታችን ሆይ፣ ከዚህች በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተፈተነች ማኅበር የምናቀርብልህን የሥቃይና የተስፋ እሮሮአችን ስማ፣ ይህ እሮሮ የእናቶች የአባቶችና የወጣቶች እንዲሁም የንጹሓን ህጻናት የሆድ ውስጥ እሮሮ ሆኖ ከምድር ወዳንተ ወደ ሰማይ የሚያርግ ጩኸት ነው፣” ሲሉ ስለሁሉም ረዘም ያለ ጸሎት ኣሳርገው ከሕዝቡ አብረው በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ደግመው ሓዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት በጸሎት አብርዋቸው መሆናቸውና ጌታ እንደሚረዳቸው አረጋግጠው ሁላቸውንም ስለ ብርታታቸው ስለእነታቸውና ስለ ተስፋቸው አመስግነዋል።

ከዚህ በኋላ የወደመውን በመኪና ተዘዋውረው ተመለከቱና በላ’ኲላ ሲጠብቅዋቸው የነበሩትን ከሓምሳ ሺ በላይ ለሚሆኑ ሕዝብ፦ “የተከበራችሁ ውንድሞቼና እኅቶቼ ባደረገላችሁኝ ስሜትን የሚቀስቀስ አቀባበል አመስግናለሁ፣ ሁላችሁንም ተስፋችን በሆነ ከሞት ተለይቶ በተነሣ ክርስቶስ እጆቼን ዘርግቼ እቀበላችህዋለሁ፣ አደጋው ካጋጠመ ዕለት ጀምረው በመሀከላችሁ ሁነው ሁሉንም ከእናንተ የሚሳተፉ እረኛችሁ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጁሰፐ ሞሊናሪን በልብ አመሰግናለሁ፣ እንዲሁም ከእናንተ ጎን በመሰለፍ አስፈላጊውን እርዳታ እያደረገና ሁሉንም እያዋቀረ ላለው የላ’ኲላ ከንቲባ ሲኞር ማሲሞ ቻለንተ ማመስገን እወዳለሁ፣” በማለት በቡድንና በግል በዚሁ አስቸጋሪ የአደጋ ግዜ የተቻላቸውን የሚያበርክቱትን ሁሉ አመስገንው በጸሎታቸውም እንደሚያስብዋቸው አመለተው፣ “እየውላችሁ በዚሁ የፋይናንስ ጥበቃ ትምህርት ቤት ኣደባባይ እማሀከላችሁ እገኛለሁ። ይህ አደባባይ ችግሩ ከተከሠተበት ጊዜ ጀምሮ፣ የእርዳታና የመልሶ መቋቋም መህከል ሆነዋል። በጸሎትና በልቅሶ የተቀደስው ይህ ቦታ የእናንተን ለሚገጥምዋችሁ ችግሮች እጅን ያለመስጠት የጽናት ምልክት ነው። በአመድ እንደተዳፈነ እሳት እያየለ የሚመጣው የአጋርነት መንፈስም እዚህ ጎልቶ ይታያል።’ ሲሉ ዘወትር በመንፈስ እጎናቸው መሆናቸውና በቤተ ክርስትያን ስም እሳቸውን ወክለው፣ ወደ ሶስት መቶ የሚጠጉ ሙታን ሥርዓተ ቀብር የተገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሓፊ፣ ብፁዕ ካርዲናል ታርቺዝዮ በርቶነ እንዲሁም የኢጣልያ ጉባኤ ጳጳሳት ሊቀ መንበር፣ ብፁዕ ካርዲናል ኣንጀሎ ባኛስኮ ያደርጉትን አገልግሎት ጉብኝትና ያደረጉት እርዳታን ጠቅሰዋል።

በመጨረሻም አጋጣሚው እንደ ማንም ኣጋጣሚ በዝምታ የሚታለፍ ሳይሆን እንደ ክርስትያን መጠን፣ ከዚህ አደጋ በመነሣት “እግዚአብሔር እኛን እንደ ክርስትያን መጠን በዚህ አደጋ ምን መልእክት ለማስተላለፍ ይፈልጋል ብለን ማስተንተን እንዳለብን በበለጠም ፍጻሜው በሕማማትና በትንሣኤ ዘመን መክሰቱ ሊያስተሳስበን ይገባል። እንደ ክርስትያን ሞራላችን ከፍ አድርገን በአዲስ መንፈስ መንሣት አለብን እንዲሁም በበለጠ አጋርነት መንፈስ መረዳዳት አለብን” ካሉ በኋላ የንግሥተ ሰማያት ጸሎትን ኣሳርገው በሰላም ወደ መንበራቸው ተመለሱ።








All the contents on this site are copyrighted ©.